የቁንጫ ቆዳ መግፈፍ
ተራኪው የማይታወቅ
አንድ ሰው አህያ ሊገዛ ወደ ገበያ ሄዶ የሚፈልገውን አህያ ስላላገኘ ሰባ ቁንጫዎች ገዝቶ ተመለሰ፡፡ እቤትም በደረሰ ጊዜ አንዷ ቁንጫ በበሩ ሳይሆን በመስኮቱ ለመብረር ስትሞክር ተሰበረች፡፡ ሰውየውም ቁንጫዋን ለመግፈፍ ፈልጎ ሰባት ሰዎችን እንዲረዱት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ቁንጫዋን ለመግፈፍ ተረዳድተው ሰባት ሰአታት ፈጀባቸው፡፡
ሰውየውም በቁንጫዋ ቆዳ ከበሮ ሰርቶ ፀሐይ ላይ እንዲደርቅ ውጪ አስቀመጠው፡፡ በዚህ ጊዜ አንዲት ከሩቅ ቦታ የመጣች ዝንብ ከበሮው ላይ ስታርፍ ከበሮው ከፍተኛ ድምፅ ስላወጣ በሩቅ ስፍራ ያሉ ሴቶች ድምፁን ሰምተው እልልታቸውን ሲያቀልጡ በሌላ ከተማ ያሉ ሌሎች ሴቶችም እልልታውን ሰምተው መጨፈር ሲጀምሩ አገሬው ሁሉ አብሮ ጨፈረ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|