ተረቶቹ
ሥነ ቃል በኢትዮጵያ ትልቅ ስፍራ ያለው ባህላዊ እሴት ነው፡፡ የጥንት ታሪክ፣ እምነት፣ አፈ ታሪክና ባህላዊ አስተሳሰቦች የብዙ መቶ ዓመታት ዕድሜ ባለጸጋ በሆኑት ተረቶች ተገልጸዋል፡፡ ሆኖም ይህ ልዩ የሥነ ቃል ክምችት አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ዘመናዊ ትምህርት፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የመሳሰሉት የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች መስፋፋትና እንዲሁም ባህላዊው የሰዎች አኗኗር እየቀረ መምጣት ጥንታዊ ታሪኮችን የመተረትም ሆነ ለእነርሱ የሚሰጠው ዋጋ እንዲቀንስ ምክንያት ሆነዋል፡፡ በዚህ ምክንያት እነዚህ ታሪኮች በአንድ ትውልድ ዕድሜ ሊጠፉ ይችላሉ፡፡ መልካሟ ሚስት (አፋር) በሚለው ታሪክ ላይ ተመስርቶ በዮሴፍ ከበደ የተሳለ በዓለም ላይ እጅግ ተራርቀው በሚገኙ ክልሎች ውስጥ የሚነገሩ ጥንታዊ ታሪኮች አስገራሚ ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ በዚህ ድረ-ገጽ ውስጥ ያሉትም ታሪኮች ከኤዞፕ ተረቶች፣ ከአንድ ሺህ አንድ ሌሊቶችና ከሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ጥንታዊ ተረቶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ቢሆንም ሁሉም ተረቶች በታሪክ አወቃቀራቸውና በባህላዊ እሴቶቻቸው ኢትዮጵያዊ ለዛ ያላቸውና ብዙዎቹም የሃገሪቱ ልዩ ሃብቶች ናቸው፡፡ የእነዚህን ታረኮች እድሜ በትክክል ማወቅ ባይቻልም አባዛኛዎቹ በጣም ጥንታዊ መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ እንደ መኪናና አውቶቡስ የመሳሰሉት የዘመናዊው ዓለም መገለጫዎች በአንዳንዶቹ ተረቶች ውስጥ መገኘት የሚያመለክተው ተረቶቹ በመላው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እንደየጊዜው ሁኔታ ራሱን እያመሳሰለ የሚሄደው ባህላችን አካል መሆናቸውን ብቻ ነው፡፡ የተለያዩ ታሪኮችን ለመተንተን በሥነ-ተረት መሰልጠንን ይጠይቃል፡፡ እናም የሚከተለው ዝርዝር የተረቶቹን ዓይነቶች በግርድፉ ለማስቀመጥ የተደረገ ሙከራ ነው፡፡
ተረቶቹ በእርዝመትና በአጓጊነታቸው የተለያዩ ሲሆኑ በአንዳንዶቹ ክልሎች ውስጥ ጥቂት በጣም ረጃጅም ተረቶች አሉ፡፡ በሌሎች ክልሎች ደግሞ ከብጥስጣሽነት ብዙም የዘለሉ የማይመስሉ በርካታ ተረቶች አሉ፡፡ ሆኖም ሁሉም እዚህ ስብስብ ውስጥ ተካተዋል፡፡ |
||||
|