ተረቶቹን የማሰባሰቡ ሥራ
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ባልደረባው መርጋ ደበሎ (በስተግራ) ከቦንሳሞ ሚኤሶ ጋር ባሌ በተደረገው የተረት ማሰባሰብ ሥራ ላይ የኢትዮጵያን ተረቶች በቅጂ መልክ ማሰባሰብ የፕሮጀክቱ ቀዳሚ ዓላማ አልነበረም፡፡ ተረቶቹ የተሰባሰቡባቸውም ዘዴዎች ተራና ሙያዊ ችሎታን በማይጠይቅ አኳኋን ነበር፡፡ የተረቶቹ አሰባሳቢ ኤልሳቤት ላየርድም የሥነ ተረትም ሆነ የሥነ ህዝብ ባለሙያ ሳይሆኑ ጸሃፊና መምህርት ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ክልል የነበረው ቆይታ ለጥቂት ቀናት ብቻ ሲሆን ትርጉሞችም አንዳንድ ጊዜ የተዥጎረጎሩ ነበሩ፡፡ ተጨማሪ ብዙ ተረቶች ሊሰበሰቡ እንደሚችሉ ጥርጥር ባይኖርም ተረቶቹ ሊታወሱ የሚችሉባቸው የቀሩት ጥቂት አመታት ብቻ በመሆናቸው ሥራው በአስቸኳይ መሰራት ነበረበት፡፡ ኤልሳቤት ላየርድና ተርጓሚዎቹ በእያነዳንዱ የክልል ባህል ወይም ትምህርት ቢሮ ከሚገኙ የትምህርት ባለሥልጣናት ጋር ሥራቸውን በቅርበት ሰርተዋል፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች የክልሉ ባለሥልጣን ከቡድኑ ጋር ለቀናት ያሳለፈ ሲሆን በዚህም ምክንያት ተረቶቹ ለመሰብሰብ የበቁት በእነርሱ ቁርጠኝነትና ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ቡድኑ በክልላዊው ማዕከል ከደረሰ በኋላ ተረት ተናጋሪዎቹ በክልሉ ባለሥልጣን ይሰባሰባሉ፡፡ ከዚያም አመቺና ተስማሚ ቦታ ተፈልጎ ተረቶቹ በቅድሚያ በካሴት ላይ ይቀዳሉ፡፡ ተረት ተናጋሪው ጥሩ አማርኛ ተናጋሪ ከሆነ ተረቱም በዚያው ቋንቋ ይነገራል፤ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ተረቶቹ የተቀዱት በክልል ቋንቋ ሆኖ ከዚያም ወደ አማርኛና እንግሊዝኛ ሲተረጎሙ ኤልሳቤት ላየርድ ማስታወሻ ይይዙ ነበር፡፡ ስለዚህ ከማስታወሻው የወጣው ጽሁፍ የዋና ተረት ተራኪዎቹን ድምጽ ሳይሆን በጥሩ አኳኋን ከአማርኛ ወደ እንግሊዝኛ የተመለሰውን ንግግርና የአነጋገር ዘይቤ የሚወክል ይሆናል፡፡ የጋምቤላ ትምህርትና ባህል ቢሮ ባልደረባው ኦጎታ አጊው የአኙዋክ ተረቶችን ከኤልሳቤት ላያርድ ጋር በመተርጎም ሥራ ላይ በአጠቃላይ ወደ 289 የሚሆኑ ተረቶች የተሰበሰቡ ሲሆን 34 ካሴቶች ተቀድተዋል፡፡ ከተረቶቹ መካከል በኢትዮጵያ ሩቅ ስፍራዎች ከሚገኙ ትንንሽ ማኅበረሰቦች የተሰበሰቡ ብዙ ተረቶች ይገኙባቸዋል፡፡ ለምሳሌ፤ በጋምቤላ ክልል ከሚገኙት ከአኙዋክ፣ ኑዌር፣ኦፖ፣መዠንግርና ኮሞ ከተባሉ ማኅበረሰቦች የተገኙ ተረቶች ተቀድተው ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉመዋል፡፡ ከኦሞ ክልልም አሪ፣ ማሊ፣ ቤናና ፀማይ ከተባሉ ማኅበረሰቦች የተገኙ ተረቶችም አሉ፡፡ ከቤሊሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጉሙዘ፣ በርታና ሺናሻ ህዝቦች ተረቶችም ተካተዋል፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ተረቶች የተሰበሰቡት ተመሳሳይ አኗኗር ካላቸው ከትግራይ፣ ከአማራ፣ከሶማሊ፣ ከሃረር፣ ከኦሮሚያና ከአፋር ክልሎች ነው፡፡ ከእነዚህ ተረቶች አንዳንዶቹ የተቀረጹት በራሳቸው ቋንቋ ሲሆን በዚሁ ድረ-ገጽ ላይ ማዳመጥ ይቻላል፡፡ ሌሎቹ ተረቶች የተቀረጹት በአማርኛና ቀሪዎቹም በእንግሊዝኛ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ክልል ተረቶችን ከሴቶችና ከወንዶች ለመሰብሰብ ጥረት ተደርጓል፡፡ ሆኖም ይህ አስቸጋሪ ስለነበረ ከሴቶቹ የተሰበሰቡት ተረቶች ቁጥራቸው አናሳ ነው፡፡ በሴቶች የሚነገሩ ተረቶችም በጣም ማራኪና ወጥነት ያላቸው በመሆኑ የዚህ አለመሳካት የሚያስቆጭ ነገር ነው፡፡ የትምህርት መስፋፋት ለአፈ ታሪክ መዳከም አንዱ ምክንያት መሆኑ አሳዛኝ እውነታ ሲሆን በተጨማሪም በኢትዮጵያ የተማሩ ሴቶች ቁጥር ከወንዶቹ ማነሱ ሌላው እውነታ ነው፡፡ ለወደፊት የሚከናወን የተረቶች ማሰባሰብ ሥራ ሴቶችን ያማከለ ቢሆን የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል፡፡
|
||||