ዘይ ተሃሰበና ንጉሱ
ተራኪው የማይታወቅ
በአንድ ወቅት አንድ ንጉስ ነበረ፡፡ ንጉሱም አንድ ትንሽ ልጅ ሁልጊዜ ወደ እርሱ ቤት እየመጣ ሲጫወት ያየው ነበር፡፡ ንጉሱም ልጁን ወደ አንድ ጠንቋይ ዘንድ ይዞት ሄዶ ጠንቋዩን “ይህ ልጅ ሲያድግ እጣ ፈንታው ምንድነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ጠንቋዩም “ዙፋንህን ይወርሳል፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሱ ልጁን በትልቅ ሳጥን ውስጥ ከቶት ባህር ውስጥ ጣለው፡፡
ታዲያ አንድ ባልና ሚስት ልጁን አግኝተውት ወደ ቤታቸው ወሰዱት፡፡ ስሙንም “ዘይ ተሃሰበ” ማለትም (“ያልተጠበቀ”) ብለው ሰየሙት፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ንጉሱ አንድን የፀጥታ ችግር ሊፈታ ልጁ ይኖር ወደነበረበት ስፍራ ሄደ፡፡ ንጉሱም እንዳጋጣሚ ልጁ ከሚኖርበት ቤት ያርፍና የንጉሱ ቤተሰብ ምግብ ሲበላ ልጁ የንጉሱንና የአሳዳጊዎቹን እጆች ያስታጥባል፡፡
ንጉሱም የልጁን ታታሪነት በማየት ይወደውና ሰዎቹን የራሳቸው ልጅ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል፡፡
እነርሱም “ልጃችን አይደለም፡፡ አሳድገነው ነው፡፡” በማለት እንዴት እንዳገኙት ነገሩት፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሱ በጣም ተገርሞ ልጁን ወደቤተመንግስቱ እንዲልኩት ለመናቸው፡፡ እነርሱም በሃሳቡ ተስማምተው ሲሰጡት ንጉሱ ግን ለልጁ ወታደሮቹ ልጁ ቤተመንግስት እንደደረሰ እንዲገድሉትና በቤተመንግስቱ ፊት ለፊት እንዲቀብሩት ያዘዘበትን ደብዳቤ ፅፎ ሰጠው፡፡ ልጁም ወደቤተመንግስቱ እየሄደ ሳለ አንድ ጭልፊት መጥቶ ደብዳቤውን እንዲሰጠው ጠየቀው፡፡ ልጁም እሺ ብሎ ወረቀቱን ሲሰጠው ጭልፊቱ በምትኩ ሌላ “ልጁ እናንተ ዘንድ በደረሰ ግዜ ሴት ልጄን ዳሩለት፡፡” የሚል ደብዳቤ ሰጠው፡፡
እናም ልጁ ቤተመንግስት ደርሶ ወረቀቱን ለልጅቷ ቤተሰቦች ሲሰጥ እነርሱም ልጅቷን ድረውለት አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ ንጉሱም ወደ ቤቱ ሲመለስ የሰርጉ ድግስ ስላላለቀ አንድ ትልቅ ድንኳን አየ፡፡
“ይህ ምንድነው?” ብሎም ጠየቀ፡፡
እነርሱም “አንተ ራስህ ልጄን ዳሩለት የሚል ደብዳቤ ልጁን አስይዘህ አላከውም እንዴ? ይህ ታዲያ የሰርጉ ድንኳን ነዋ!” አሉት፡፡
ይህን ሲሰማ ንጉሱ በድንጋጤ ከፈረሱ ላይ ወድቆ ራሱን ሲስት ሳንጃው ጎኑን ወግቶ ገደለው፡፡ ልጁም ዙፋኑን ወረሰ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|