ያናፋው አህያ
ተራኪው የማይታወቅ
አንድ ቀን አንድ አህያ ከቤቱ ወጥቶ እየሄደ ሳለ በመንገዱ ላይ አንድ ውሻ አገኘ፡፡
ውሻውም “የት እየሄድክ ነው” ብሎ ሲጠይቀው አህያው “ከቤቴ ስለተባረርኩ ወደ ጫካ ገብቼ ለመኖር እየሄድኩ ነው፡፡” አለው፡፡
ውሻውም “እኔም ስለተባረርኩ እንግዲያው አብረን እንሂድ፡፡” አለው፡፡
አህያውም በደስታ “እሺ” ብሎ ተያይዘው ሲሄዱ ቀኑ በመምሸቱ እዚያው ከጎዳናው አጠገብ ተኙ፡፡ ውሻው ርቦት ስለነበረ ወዲያው እንቅልፍ ሲጥለው አህያው ግን ብዙ በልቶ ስለነበረ መሬት ላይ መንከባለል ጀመረ፡፡
ውሻውንም “እባክህ ላናፋ” ብሎ ሲጠይቀው ውሻው “አፍህን ዝጋ፡፡ ካናፋህ ጅቡ መጥቶ ይበላሃል፡፡” አለው፡፡
አህያው ግን “አንድ ጊዜ ብቻ”” እያለ መማፀኑን ቀጠለ፡፡ ወዲያውም አንዴ ሲያናፋ ጅቡ ከሩቅ ስለሰማው አህያው ወዳለበት አቅጣጫ ተጠጋ፡፡ ሆኖም አህያውና ውሻው ያሉበትን ትክክለኛ ቦታ ስላላወቀ አህያው ደግሞ እንደሚያናፋ ተስፋ በማድረግ ፀጥ ብሎ ጠበቀ፡፡
በዚህ ጊዜ አህያው ውሻውን “አንድ ጊዜ ደግሜ ላናፋ፡፡” አለው፡፡ ውሻውም “ተው ይቅርብህ፡፡ ጅቡ ሰምቶህ ሊሆን ስለሚችል ደግመህ ካናፋህ መጥቶ ይበላሃል፡፡” አለው፡፡
አህያው ግን “ሃ!ሃ!ሃ!” እያለ ሲያናፋ ጅቡ አህያው ያለበትን ስላወቀ መጥቶ ገደለው፡፡
አህያውም ሞተ፡፡ ጅቡ ውሻውን አይቶት “አንተ ደግሞ ማነህ?” ብሎ ሲጠይቀው ውሻው “እኔ የተራብኩ ፍጡር ነኝ፡፡” አለው፡፡ ጅቡም “እንግዲያው አህያውን አርደህ ልቡን ስጠኝ፡፡” ብሎ ውሻውን አዘዘው፡፡
ውሻው ግን የአህያውን ልብ ለራሱ ስለበላው ጅቡ “ልቡ የታለ?” ብሎ ሲጠይቀው “ይህ አህያማ ልብ የለውም፡፡ ልብ ቢኖረው ኖሮ አይሞትም ነበር፡፡”በተለምዶ ልብ እንደማሰቢያ አካል ስለሚቆጠር ውሻውም በቀልድ አስመስሎ የአህያውን ደደብነት ተናገረ፡፡ አለው
ጅቡም የቀረውን የአህያ ስጋ ብቻውን በላው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|