ሰባት ቀንዶች ያሉት ሰው
ተራኪው የማይታወቅ
በአንድ ወቅት ሰባት ሴቶች ነበሩ፡፡ ሰባተኛዋም አካለ ስንኩል ነበረች፡፡ ታዲያ ሰባቱም ሴቶች ወልደው ከአርባ ወይም ከሰማንያ ቀናት በኋላ ሰባቱም ልጆቻቸውን ይዘው የማገዶ እንጨት ሊሰበስቡ ሄዱ፡፡ አካለ ስንኩሏ ልጇን ከዛፉ ስር ስታስቀምጠው ሌሎቹ ልጆቻቸውን ከዛፍ ላይ አኖሯቸው፡፡
ጅቡም በመጣ ጊዜ አንዲቷ እናት “ልጆቻችን ዛፉ ላይ ናቸውና አትንካብን፡፡ ነገር ግን የአካለ ስንኩሏ ልጅ ዛፉ ስር ስለሆነ እሱን ልትበላው ትችላለህ፡፡” አለችው፡፡
ጅቡም “እሺ” አለ፡፡
አካለ ስንኩሏ ሴት ስታለቅስ፣ ስታለቅስ ሌሎቹ ግን እየተሳሳቁ ይጫወቱ ነበር፡፡ ታዲያ የማገዶውን እንጨት ይዘው ሲመለሱ የአካለ ስንኩሏ ሴት ልጅ ደህና ሆኖ ሌሎቹ ልጆች ተበልተው ቆዩአቸው፡፡ አካለ ሰንኩሏም ሴት በጣም ስትደሰት ሌሎቹ ማልቀስ ጀመሩ፡፡
ከሴቶቹ አንዷ ልጁን “የሁላችንም ወተት ጠብተህ ሰባት ቀንዶች ይኑሩህ ወይስ ከአንዳችን ብቻ ጠብተህ አንድ ቀንድ ይኑርህ?” ብላ ስትጠይቀው እሱም ሰባት ወተትና ሰባት ቀንዶች እንዲኖረው መረጠ፡፡
ከእለታት አንድ ቀን በሰባት ቀንዶቹ መሬቱን ሲቆፍር ውሃ አወጣ፡፡
በዚህ ጊዜ አንዲት ጥንቸል መጥታ “ውሃውን ልጠጣ?” ብላ ስትጠይቀው እሱም “እሺ፣ ነገር ግን መጀመሪያ እኔ ሄጄ ምሳዬን በልቼ እስክመጣ ውሃውን ጠብቂልኝ፡፡” አላት፡፡
ይህንንም ብሏት ሲሄድ አንድ ቀበሮ ወደ ጥንቸሏ መጥቶ ውሃውን መጠጣት ይችል እንደሆነ ሲጠይቃት “አይሆንም፡፡ ባለ ሰባት ቀንዶቹ ሰው መጥቶ ይገድልሃል፡፡” አለችው፡፡
ከዚያም ቀበሮው ሄዶ በምትኩ አንበሳ መጣ፡፡
እርሱም “ጥንቸል ሆይ! ውሃውን ልጠጣ?” ብሎ ጠየቃት፡፡
ጥንቸሏም “አይሆንም፣ ባለ ሰባት ቆንዶቹ ሰው መጥቶ ይገድልሃል፡፡” አለችው፡፡
አንበሳውም “ታዲያ እኔ ምን አገባኝ” ብሎ ጥንቸሏን በርግጫ ብሏት ውሃውን ጠጣ፡፡
ጥንቸሏም በግጥም እንዲህ ብላ ዘፈነች፤
“ሰባት ቀንዶች ያሉህ አያ እገሌ፣
ውሃው እየተጠጣብህ ነው፡፡”
በዚህ ጊዜ አንበሳው “ምን እያልሸ ነው?” ሲላት እርሷም “ኧረ ምንም አላልኩ፣ እየዘፈንኩ ነው፡፡” አለችው፡፡
ከዚያም ባለ ሰባት ቀንዶቹ ሰው መጥቶ ከአንበሳው ጋር ትግል ገጠሙ፡፡ ታዲያ በትግሉ ወቅት የሰውየው አንድ ቀንድ እና የአንበሳው አንድ ጥርስ ተሰበሩ፡፡ ጥንቸሏም “ፀባችሁን አቁሙና ወደ ቤት ሄደን እኔ ላስታርቃችሁ፡፡” አለች፡፡
እነርሱም በዚህ ተስማምተው አብረዋት ሄዱ፡፡ ባለ ስድስቱ ቀንዶች ሰው አልጋው ላይ ተቀምጦ ጠላናጠላ ቢራ መሰል ባህላዊ መጠጥ ነው፡፡ ጥሩ ቆሎ ይበላ ጀመር፡፡ አንበሳውም ይጠጣ ነበር ነገር ግን የጠላውን አተላ እየጠጣ የገብስ ቆሎ ነበር የሚበላው፡፡
በኋላም አንበሳው ወደ ቤቱ ሄዶ ለጥንቸሏ “አሞኛል፣ መጥተሽ ብታስታምሚኝ ይሻላል፡፡” ብሎ ላከባት፡፡
ጥንቸሏም እንጀራእንጀራ በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ከሚበቅለው ጤፍ የተባለ ሰብል የሚሰራ ጠፍጣፋ፣ ስስና ክብ ምግብ ነው፡፡ ይዛ አንበሳውን ልትጠይቅ ሄደች፡፡ አንበሳውም የገብስ ቆሎ እንድትበላ ቢጋብዛት እምቢ አለች፡፡ ቆሎውንና የጠላውን አተላ አልፈልግም ስትል በዱላ መታት፡፡
ጥንቸሏም “ይህ እኔን አይጎዳኝም፡፡” ስትለው እርሱም “ታዲያ የሚጎዳሽ ምንድነው?” አላት፡፡ በአካባቢው ከሚገኘው ተራራ ለየት ያለ ዱላ ቆርጦ እንደሚመጣ ነግሯት በገመድ አስሯት ሄደ፡፡
በዚህ ጊዜ በአንበሳው ቤት አጠገብ ታልፍ የነበረች አንዲት ቀበሮ ጥንቸሏ ታስራ ስታያት “እዚህ ምን እያደረግሽ ነው?” አለቻት፡፡
ጥንቸሏም “አያ አንበሳ ቆሎ እንድበላና ጠላ እንድጠጣ ቢጠይቀኝ እምቢ ስላልኩት እዚህ አስሮኝ ሄደ፡፡” አለቻት፡፡
ቀበሮዋም “እንግዲያውማ እኔ ልፍታሽና በምትክሽ እኔን እሰሪኝ፡፡ እኔ መብላትም ሆነ መጠጣት እችላለሁ፡፡” አለቻት፡፡
ከዚያም አንበሳው ተመልሶ መጥቶ ቀበሮዋን ባመጣው ልዩ ዱላ ሲደበድባት እሷም “ኧረ እኔ እበላለሁ፣ እጠጣለሁም” አለች፡፡ እርሱም “ምንድነው የምትቀባጥሪው?” እያለ ድብደባውን ሲቀጥል ጥንቸሏ ግን አመለጠች፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|