ሰውና እባብ
ተራኪው የማይታወቅ
ከእለታት አንድ ቀን አንድ ሰው በጉዞ ላይ እያለ ከአንድ ወንዝ ዳርቻ ላይ ከአንድ እባብ ጋር ተገናኘ፡፡ እባቡም ሰውየው ወንዙን እንዲያሻግረው ጠየቀው፡፡
ሰውየውም “እንዴት አድርጌ?” ብሎ ሲጠይቀው እባቡም “አንገትህ ላይ አድርገኝ፡፡” አለው፡፡
ሰውየው እባቡን ቢፈራውም አንገቱ ላይ አድርጎ አሻገረው፡፡
ወንዙን ከተሻገሩም በኋላ ሰውየው እባቡን “በል አሁን ከአንገቴ ላይ ውረድልኝ፡፡” ሲለው እባቡ ግን አልወርድም፣ እንዲያውም ወደ ዳኛ እንሂድ አለው፡፡”
ሰውየውም በዚህ ተስማምቶ ወደ ዳኛ ሲሄድ ዳኛው ጅብ ነበርና ጅቡ ጉዳያቸውን ካዳመጠ በኋላ እባቡን ስለፈራው “እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ፍርድ መስጠት አልችልምና ወደ ጦጣዋ ሂዱ፡፡” አላቸው፡፡ ከዚያም ወደ ጦጣዋ ዘንድ ሄደው ጉዳያቸውን ሲያቀርቡ ጦጣዋ “እሺ፣ መጀመሪያ ግን ዛፍ ላይ ልውጣ፡፡” ስትላቸው እነርሱም “እሺ” አሏት፡፡
ከዚያም ጦጣዋ “በሉ አሁን ሁለታችሁም መጀመሪያ መሬት ላይ መሆን አለባችሁ፡፡” አለቻቸው፡፡
እናም እባቡ መሬት ወረደ፡፡
በዚህ ጊዜ ጦጣዋ ሰውየውን “ታዲያ አሁን ምን ትጠብቃለህ? በእጅህ ቢላዋ ይዘሃል፡፡ እባቡም መሬት ላይ ነው፡፡” አለችው፡፡ ሰውየውም የጦጣዋ ንግግር ስለገባው እባቡን ገደለው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|