ትንሿ ወፍና ዝሆኑ
ተራኪው የማይታወቅ
በአንድ ወቅት አንድ ዝሆንና አንዲት ዛፍ ላይ ባለው ጎጆዋ ውስጥ እንቁላሎቿን ታቅፋ የምትኖር ትንሽ ወፍ ነበሩ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የወፏ እንቁላሎች ተፈለፈሉ፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ወፏ ለልጆቿ ምግብ ልታመጣ በርራ ሄዳ ስትመለስ ጫጩቶቿ በሙሉ በዝሆኑ ተገድለው አገኘቻቸው፡፡ ዝሆኑ ሁልጊዜ ውሃ ሊጠጣ ወደ ዛፉ ስር ይመጣ ስለነበረ በዚህ ጊዜ ዛፉን ሲታከከው ጫጩቶቿ ስለወደቁ በድንገት ጨፈላልቆ ገደላቸው፡፡
ወፏም ከሄደችበት ተመልሳ ስትመጣና ጫጩቶቿ ተገድለው ስታይ የዝሆኑን የእግር አሻራ ስላገኘች የገደላቸው ዝሆኑ መሆኑን አወቀች፡፡
ወፏም ወደዝሆኑ ሄዳ “ጫጩቶቼን ለምን ገደልካቸው?” ብላ ጠየቀችው፡፡
ዝሆኑም በትእቢት “ታዲያ ምን ትሆኚ?” ሲላት ወፏ “ጫጩቶቼን ስለገደልካቸው ይቅርታ መጠየቅ ሲገባህ ይህንን አላደረክም፡፡” አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ ዝሆኑ ሳቀባት፡፡ በዚህ የተናደደችው ወፍም “አሳይሃለሁ” ስትለው ዝሆኑ እንደገና “ሃ!ሃ!ሃ!” ብሎ ሳቀባት፡፡
ትንሿም ወፍ ወደ ጓደኞቿ ሄዳ አሳዛኙን ታሪክ ስትነግራቸው እነርሱም “እንዴት ልንረዳሽ እንችላለን?” አሏት፡፡
እሷም “ልትረዱኝ የምትችሉት የዝሆኑን ዓይኖች ጠቅጥቃችሁ እውር እንዲሆን በማድረግ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ማየት ስለማይችል መንቀሳቀስም አይችልም፡፡” አለቻቸው፡፡
ጓደኞቿም በሃሳቡ ተስማሙ፡፡
ከዚያም ዝሆኑ ወደ ወንዙ እንደተለመደው ሲሄድ ወፎቹ ሁሉ ዓይኖቹ ላይ አርፈው ሲጠቀጥቁት አይነ ስውር ሆነ፡፡
ትንንሾቹ ወፎች ወደ ወንዙም ሄደው እንቁራሪቷን እንድትረዳቸው ለመኗት፡፡
“እባክሽ ከውሃው ወጥተሸ ጩሂና ዝሆኑ ውሃ አለ ብሎ እንዲመጣ አድርጊ፡፡” አሏት፡፡
እንቁራሪቶቹም ከአንድ ትልቅ ጉድባ አፋፍ ላይ ሆነው ሲጮሁ ዝሆኑ የእንቁራሪቶቹን ድምፅ ሰምቶ ውሃ ሊጠጣ ሲመጣ ጉድባው ውስጥ ወደቀ፡፡
ዝሆኑም እያላዘነ ሲጮህ ወፏ ጭንቅላቱ ላይ ተቀምጣ “ልጆቼን ስለገደልክብኝ ተበቅዬሃለሁ፡፡” አለችው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|