የፋፈን አንበሳ ልጅ
በአብዱልሃኪም አብዱላሂ ጅብሪል የተተረከ
በአንድ ወቅት በፋፈን አካባቢ የሚኖር የታወቀ ሰው በላ አንበሳ ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን አንበሳው ወደ መንደሩ መጥቶ የአራት ወይም የአምስት ዓመት እድሜ ልጅ ይዞ ሄደ፡፡ ልጁንም ወደ ጫካው ይዞት ምንም ጉዳት ሳያደርስበት ዋሻው አጠገብ ሲያስቀምጠው ልጁ ከአንበሳው ሸሽቶ ሲሮጥ የአንበሳው ግልገሎች ይኖሩበት የነበረው ዋሻ ውስጥ ገባ፡፡
የአንበሳውም ግልገሎች ልጁን ከመጉዳት ይልቅ አብረውት ይጫወቱ ጀመር፡፡ ሴቷ አንበሳም አልነካችውም ነበር፡፡ ከዚያም አንበሳውና ሴቷ አንበሳ ለግልገሎቹ ስጋ ይዘው ሲመጡ ልጁም ስጋውን አብሯቸው ይበላ ጀመር፡፡
ከብዙ ቀናት በኋላ ሴቷ አንበሳ ስለራባት ልጁን ገድላ ልትበላው ስትሞክር አንበሳው ከልክሎ አስጣላት፡፡ ከዚያ በኋላ ስላላመናት ሰዎችን ወይም ከብቶችን ሊያድን በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ ሴቷ አንበሳ ይዛ ትበላዋለች ብሎ ስለሰጋ ልጁን በጀርባው አዝሎት ልጁም አንበሳውን ተሳፍሮ በጫካው ውስጥ ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡አንበሳውም ቤተሰቡን ሊፈልግ ሲሰማራ ልጁን ከላዩ ላይ አውርዶ ያስቀምጠውና ተመልሶ ሲመጣ ልጁ እንደገና ተሣፍሮት አብረው ይሄዳሉ፡፡ አንበሳው ሴቷን አንበሳ ስላላመናት ሁልጊዜ ልጁን በጀርባው አዝሎ ይዞር ነበር፡፡
የአንበሳው ግልገሎች ልጁን በፍፁም ሊጎዱት ሞክረው አያውቁም ነበር፡፡ ይልቁንም ጓደኛው ነበሩ፡፡
ልጁም በዚህ ዓይነት ከአንበሶቹ ጋር ለሁለት ዓመታት ኖረ፡፡ ይህ የሆነው ፋፈን የሚባል አካባቢ ሲሆን እኔ ራሴ ልጁን ያዩትን ሰዎች አናግሬያቸው ነበር፡፡
ለማንኛውም አንበሳው ሌሎቹን አንበሶችም ሆነ የራሱን ሚስት ስለማያምናቸው ልጁ ይህ አንበሳ የአንበሶች ንጉስ ነው ብሎ ይናገር ነበር፡፡
ልጁም እንዲህ ይላል፤ “ሁልጊዜ ከጎኑ ነበር የምቀመጠው፡፡ ሌሎቹ አንበሶች ሁሉ ወደርሱ ቤት ለስብሰባ መጥተው በክብ ቅርፅ ይቀመጡና በአንበሳ ቋንቋ ይወያዩ ነበር፡፡ ታዲያ ሌሎቹ አንበሶች ሁሉ ወደ አንበሳው ከመመልከት ይልቅ ወደ እኔ ሲመለከቱ አንበሳው ሰላማዊ እንዲሆኑ ምልክት ይሰጣቸውና እኔን በረሃብ አይን ከመመልከት ታቅበው የመጉዳት ሙከራ አያደርጉብኝም ነበር፡፡”
እናም ልጁ በዚህ ዓይነት ካደገ በኋላ ከሁለት ዓመታት በኋላ አንበሶቹ በመንጋ አደን መሄድ ስለፈለጉ አለቃቸው አንበሳ ሌሎቹን “አንድ ጊዜ ጠብቁኝ፡፡” ብሏቸው ልጁን ወደ ትውልድ መንደሩ ይዞ ሄደ፡፡ ከዚያም በመንደሩ አቅራቢያ አስቀምጦት “አሁን ወደቤትህ ሂድ፡፡” አለው፡፡
ልጁም እንደተባለው አደረገ፡፡ አንበሳውም ልጁ ወደ መንደሩ መግባሩን ሲያረጋግጥ ወደ ጫካው ተመልሶ ሄደ፡፡
የመንደሩም ሰዎች ልጁን ባዩት ጊዜ “እንዴ! ልጁ በአንበሳው ተበልቷል ብለን አስበን ነበር፡፡ ነገር ግን ድኗል፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?” መባባል ጀመሩ፡፡
ልጁም የሆነውን ነገር ሁሉ በዝርዝር ነገራቸው፡፡ ያ ትንሽ ልጅ ታዲያ አሁን ትልቅ ሰው ሆኖ ታሪኩን ለሁሉም ሰው ይነገራል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|