ኤጋል ሺዳ
ተራኪው የማይታወቅ
ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ ኤጋል ሺዳ የሚባል ሰው ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን የእርሱ በሬ ሄዶ የአንድ ጎረቤቱን ሰብል ሲበላበት ጎረቤቱ ወደ ኤጋል ሺዳ ቤት መጥቶ አምርሮ ተናገረ፡፡ ኤጋል ሺዳም ይህ ዳግም እንዳማይከሰት ቃል ቢገባም በማግስቱ በሬው እንደገና ሄዶ የጎረቤቱን ሰብል በላ፡፡
ስለዚህ ጎረቤቱ እጅግ በመበሳጨት ወደ ኤጋል ሺዳ በቁጣ መጥቶ “በሬህ ሁለተኛ ሰብሌን እንደማይበላ ቃል ገብተህ ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬም ደግሞ ሰብሌን በላብኝ፡፡” ብሎ ጮኸበት፡፡
በዚህ ጊዜ ኤልጋ ሺዳ “እንደምትመለከተው በሬውን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ ማድረግ ያለብህ ብቸኛው ምርጫ በሬውን ማረድ ነው፡፡” አለው፡፡
ሰውየውም በሬውን አርዶ ሥጋውን ለኤጋል ሺዳ አመጣለት፡፡ ኤጋል ሺዳም ሥጋውን ወደ ገበያ ወስዶ ከሸጠው በኋላ ወደ ቤቱ ሲመለስ ለጎረቤቶቹ ከበሬው ያገኘውን ሥጋ ሸጦ ብዙ ገንዘብ እንዳገኘ ነገራቸው፡፡
ጎረቤቶቹም በዚህ ተገርመው “እኛም በሬዎቻችንን ብናርዳቸውና ሥጋውን ብንሸጠው እንደ ኤጋል ሺዳ ብዙ ገንዘብ እናገኛለን፡፡” ብለው አሰቡ፡፡ ከዚያም በሬዎቻቸውን በሙሉ አርደው ስጋውን ወደ ገበያ ይዞው ሄዱ፡፡ ነገር ግን የዚያን እለት ማንኛቸውም ሥጋውን መሸጥ አልቻሉም፡፡
ጎረቤቶቹም “ኤጋል ሺዳ አታሎናልና ምን ብናደርገው ይሻላል?”ብለው ተነጋገሩ፡፡
በመጨረሻም ከረጢት ውስጥ ጨምረውት ወደ ወንዝ በመወርወር ሊገድሉት ወሰኑ፡፡ ስለዚህ ወደ ኤጋል ሺዳ ቤት ሄደው ከያዙት በኋላ ከረጢት ውስጥ ጨመሩት፡፡ ሆኖም ወንዙ ውስጥ ከመወርወራቸው በፊት ለአምላክ ፀሎት ለማድረስ ሁሉም ጎረቤቶች ወደ ፀሎት ቦታ ሄዱ፡፡
በዚህ ጊዜ በአካባቢው ያልፍ የነበረ አንድ ገበሬ ከወንዙ አጠገብ የተቀመጠውን ከረጢት አይቶ ጠጋ ብሎ ሲመለከት ከረጢቱ ውስጥ አንድ ሰው ተቋጥሮ እንዳለ አወቀ፡፡
እናም ገበሬው “እዚህ ከረጢት ውስጥ ምን እየሰራህ ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ኤጋል ሺዳ “ወደ ወንዙ ውስጥ ተወርውሬ ለከተማው ሰው ወርቅ ይዤ ልወጣ ነው፡፡” አለ ፡፡
ገበሬውም ሃብታም መሆን ይፈልግ ነበርና “እኔ ተወርውሬ ወርቁን ይዤ ልምጣ፡፡” አለ፡፡ ኤጋል ሺዳም በዚህ ተስማምቶ ከከረጢቱ ውስጥ ከወጣ በኋላ በምትኩ ገበሬውን ከረጢቱ ውስጥ አስገብቶ ቋጥሮት የገበሬውን በርካታ በጎችና ከብቶች ይዞ ሄደ፡፡
ጎረቤቶቹም ፀሎታቸውን ካደረሱ በኋላ ኤጋል ሺዳ አሁንም ከረጢቱ ውስጥ እንዳለ በማሰብ ወደ ወንዙ ተመልሰው መጥተው ከረጢቱን ወደ ወንዙ ውስጥ ወረወሩት፡፡ ከዚያም ወደቤታቸው ተመልሰው ሲሄዱ ኤጋል ሺዳን ከብዙ በጎችና ከብቶች ጋር ቤት ተቀምጦ ሲያገኙት በጣም ተደናገጡ፡፡ “ከወንዙ ውስጥ እንዴት ልትወጣ ቻልክ? ከየት ነው የመጣኸው? እነዚህስ ሁሉ በጎችና ከብቶች ከየት መጡ?” ብለው፡፡ ጠየቁት፡፡
ኤጋል ሺዳም “ወንዙ ውስጥ ስትወረውሩኝ በጣም ብዙ ወርቅ ስላገኘሁ ይዤው ከወንዙ ወጥቼ በመሸጥ እነዚህን ሁሉ በጎችና ከብቶች መግዛት ቻልኩ፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም “እንደዚያማ ከሆነ እኛም በከረጢት ሆነን ወደ ወንዙ እንወርወርና እንዳንተ ሃብታም እንሁን፡፡” አሉ፡፡
ስለዚህ ከረጢት ውስጥ ጨምሯቸው ወደ ወንዙ ውስጥ ሲወረውራቸው ሁሉም ስለሞቱ እርሱ ንብረቻቸውን በሙሉ ወረሰ፡፡
ታሪኩም ይኸው ነው፡፡
< ወደኋላ |
---|