ዴግደር
በኢክራን አህመድ ኡመር የተተረከ
በአንድ ወቅት ወንድማማች የነበሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው አምስት ወንድ ልጆች ሲኖሩት ሌላኛው ደግሞ አምስት ሴት ልጆች ነበሩት፡፡ የሁለቱም ሚስቶች ሲሞቱ ሁለቱም እንደገና አግብተዋል፡፡ ሆኖም የአምስት ሴት ልጆች አባት የሆነው ሰው ሚስት ከእርሱ ጋር ትጣላና ልጆቹንም ትጠላቸው ነበር፡፡
ሰውየውም ከሄደበት ሲመለስ ሚስቱ “አድምጠኝ! አንተ ባል ተብዬ ሰው! ከሁለቱ አንዱን መምረጥ አለብህ፤ ወይ እኔን ፍታኝ ወይም ልጆቹን ከዚህ አጥፋልኝ፡፡” አለችው፡፡
ሰውየውም “ከልጆቼ በስተቀር ሌላ ዘመድ የለኝምና ምን ማድረግ እችላለሁ?” ሲላት እርሷም “እኔን ከፈለከኝ እነዚህን ትንንሽ ልጆችህን አባርልኝ፡፡ አለበለዚያ እኔ ሚስትህ መሆን አልችልም፡፡” አለችው፡፡
ሰውየውም ይህንኑ በመቀበል ከወንድሙ ጋር “ምን ባደርግ ይሻላል? እሷ ይህ መሆን አለበት ነው የምትለው፡፡” ብሎ ተማከረ፡፡
ወንድሙም “እንግዲያው አንዷን አስቀርተህ ሌሎቹን እንኳን ብትጥላቸው አንዷን ደግሞ ለእኔ ስጠኝና የቀሩትን ሶስት ልጆች ጣላቸው፡፡” አለው፡፡
ከዚያም ሰውየው ወደ ሚስቱ ሄዶ ይህንኑ ሲነግራት እርሷ “ይህ በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡ ሁሉንም ካልጣልካቸው የእኔ ባል መሆን አትችልም፡፡” አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ ትዕዛዟን በመቀበል አምስቱንም ልጆች ወደ ጫካ ወስዶ እዚያው ትቷቸው ሊሄድ ሲል “አባታችን!” ብለው ጠሩት፡፡
እርሱም “አቤት” አላቸው፡፡
እንደገና “አባባ!” ብለው ሲጠሩት ግመል የሚያወጣውን ድምፅ ማውጣት ጀመረ (ግመሎች በጫካ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን ያሉበትንም አካባቢ በሚያወጡት ድምፅ ማወቅ ይቻላል፡፡)
እናም አባታቸው እንደግመል ሲጮህ ልጆቹ “አሃ! አባታችን አሁንም እዚህ ነው ያለው፡፡” አሉ፡፡
ከዚያ በኋላ ቀስ ብሎ ሾልኮ ሮጦ ሄደ፡፡ ልጆቹም “አባባ!” እያሉ ቢጣሩ የሚሰሙት የግመል ድምፅ ብቻ ሆነ፡፡
በመቀጠልም ግመሉ ታስሮበት የነበረውን የዛፍ ቅርንጫፍ ለማየት ሲሄዱ የታሰረበት ገመድ ብቻ ሲገኝ ግመሉም ሆነ አባታቸው እዚያ አልነበሩም፡፡
ታዲያ ልጆቹ ትንሽ አሰብ አድርገው “አባባ፣ ገመዱን ብቻ በማየት እዚህ ሰው እንዳለ ገምተን ነበር፡፡ ነገር ግን ከአንበሶችና ከሌሎች የዱር እንስሳት በስተቀር ማንም ሰው የለም፡፡” አሉ፡፡ ስለዚህ በሚያሳዝን ሁኔታ “ወይኔ ብቻችንን ሆንን!” እያሉ ማልቀስ ጀመሩ፡፡
በኋላም ጀንበሯ ስትጥልቅ አንዲት ሴት ልጅ በጎች እየነዳች ወደ ቤቷ ስትመለስ አይተው “አንቺ! ወደ አባታችን ተመልሰን መሄድ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን አባታችን ጠፍቶብናልና ወደ ቤትሽ ልትወስጅን ትችያለሽ?” ብለው ተማፀኗት፡፡
ልጅቷም “በጣም አዝናለሁ፡፡ እናታችን ዴግደር ናት፡፡ ይህም ማለት ረጅም ጆሮ ያላት ማለት ነው፡፡ ከእኔ በስተቀር ሌሎችን ሰዎች ትበላለች፡፡ ሁልጊዜ ማታ ማታ የምትበላው የሰው ስጋ ስለሆነ ወደ ቤታችን ከወሰድኳችሁ እናንተንም ትበላችኋለች፡፡” አለቻቸው፡፡
ልጆቹ ግን “እባክሽ፣ እኛ ምንም ስለሌለን የዱር እንስሳቱ ሊበሉን ይችላሉና ብቸኛ ተስፋችን አንቺ ብቻ ነሽ፡፡ ለአንዲት ሌሊት ብቻ ተቸገሪልንና ነጋ ማታ ሌላ ዘዴ እንፈልጋለን፡፡” አሏት፡፡
በመጨረሻም ልጅቷ “እንግዲያው እባካችሁ በፍፁም ለእናቴ እንዳትታዩዋት፡፡ ፍየሎቹ እቤት ሲደርሱ አቧራውን እየጫሩ ስለሚያቦኑት ከፍየሎቹ ጋር ሆናችሁ በአቧራው በመከለል ፍየሎቹ የሚገቡበት አንድ ጉድጓድ አጥሩ ሥር ስላለ እዚያ ጉድጓድ አጠገብ አድራችሁ ነገ በጠዋት ፈጥናችሁ አምልጡ፡፡” አለቻቸው፡፡
ልጆቹም ይህንኑ አደረጉ፡፡ በመሸ ጊዜም ዴግደር አየሩን በማነፍነፍ “ሰዎች ይሸቱኛል፡፡” አለች፡፡
ልጇም “የሚሸትሽ የእኔ ጡት ነው፡፡ እኔ ነኝና የምሸትሽ ልትበይኝ ትፈልጊያለሽ?” አለቻት፡፡
እናትየውም “አይደለም! እኔ እኮ እናትሽ ነኝ፡፡ ነገር ግን ሌላ ሰው እዚህ አካባቢ አለ፡፡” አለች፡፡
ልጅቷም “እባክሽ የምታሸቺው ልጅሽን ነው፡፡ ጡቴ ነው የሚሸትሽ፡፡” አለቻት፡፡
ታዲያ ዴግደር “የሆነ ነገር መብላት አለብኝ፡፡” አለቻት፡፡ ስለዚህ ልጇ አንዲት ወፍራም ፍየል አምጥታላት በላች፡፡ ከዚያም ዴግደር “የበጓን ላት ቁረጪና አብረን እንበላለን፡፡ ጠብሰሺውም ጆሮዬ ውስጥ ጨምሪልኝ፡፡ ጆሮዬን አሞኛል፡፡” አለቻት፡፡
ነገር ግን ልጅቷ የበጓን ላት አቅልጣ ዴግደር ጆሮ ውስጥ እንደጨመረችው ሞተች፡፡ ዴግደር እንደሞተችም ልጇና እሷ ልትበላቸው የነበሩት ሰዎች ሁሉ እንዲህ እያሉ ይዘፍኑ ጀመር፤
“እንግዲህ ዴግደር ሞተች!
ምድሪቱም አሁን ሰላም ሆነች፡፡”
ልጆቹም እንዲህ እያሉ ይዘፍኑ ጀመር፤
“ውይ! ዴግደር ሞተች!
ምድሪቱም እንግዲህ ሰላም ሆነች፡፡”
አንዳንዶቹ እድሜዋ ለጋብቻ የደረሰችውን ትልቅ ልጅ “ልናገባሽ እንፈልጋለን፡፡” ይሏት ነበር፡፡ እርሷ ግን “ምንም የሌላቸው አራት ታናናሽ እህቶች ስላሉኝ እኔ ማግባት አልችልም፡፡ እስኪያድጉ ድረስ እነርሱን መንከባከብ አለብኝ፡፡” አለቻቸው፡፡
ስለዚህ ሰዎቹ የዴግደርን ልጅ ማግባት ፈለጉ፡፡ እሷ ግን “እኔ ለማግባት ዝግጁ ነኝ፡፡ ሆኖም ስድስት ልጆችን ስወልድ እንደ እናቴ ዴግደር እሆናሁ፡፡ እናቴም ስድስት ልጆች ከወለደች በኋላ ነው ዴግደር የሆነችው፡፡ ስለዚህ በዚያን ጊዜ ላትወዱኝ ትችላላችሁ፡፡” አለቻቸው፡፡
ነገር ግን እነርሱ “ምንም ብትሆኚ እኛ ልናገባሽ እንፈልጋለን፡፡” እያሉ ስለገፋፏት አግብታ ሄደች፡፡
አምስቱም እህቶች ወደ ከተማ ሄደው ስራ በመያዝ በጣም ሃብታም ሆኑ፡፡ ብዙ ገንዘብም አግኝተው ደስተኛ ሆኑ፡፡
አባታቸውና የእንጀራ እናታቸው ልጆች በጋራ ሳያፈሩ በማርጀት ደሃ ሆኑ፡፡ ወደ ልጆቻቸው ቤት መጥተው መለመን ጀመሩ፡፡ እየለመኑ ሳለም የመጨረሻዋ ትንሽ ልጅ አባቷን አወቀችው፡፡ “እንዴ! ይህ እኮ አባታችን ነው! አንተ አባታችን አይደለህም?” አለችው፡፡
እርሱም “አዎ ነኝ፡፡” አላት፡፡
“ታዲያ ና ወደቤት ግባ፡፡” አለችው፡፡
ከዚያም ሰውነቱን አጥበው አዲስ ልብስ ካለበሱት በኋላ በምቾት አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ ሁለቱም ችግረኛ ስለነበሩ ልጆቹ ይቅር አሏቸው፡፡
ልጆቹ ሃብታም የሆኑት ታላቅ እህታቸው እንጀራ ስትጋግር ትንንሾቹ ወደተለያዩ ገበያዎች ይዘው እየሄዱ በመሸጥ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት አብረው እየኖሩ ሳለ በሚኖሩባት ከተማ ያሉ ሰዎች ሁሉ ውሃ ይቀዱበት የነበረ የውሃ ጉድጓድ ያለ ሲሆን ጉድጓዱም ውስጥ ዘንዶ ነበር፡፡ ዘንዶው ወደ ጉድጓዱ ሲገባ ሰዎች ሄደው ውሃ ይቀዱ ነበር፡፡ ሆኖም ዘንዶውን ካዩት ወደዚያ ድርሽ አይሉም ነበር፡፡
በጉድጓዱም ውስጥ ዘንዶው ይጠብቀው የነበረ ብዙ ወርቅ ነበር፡፡ ሰዎች ውሃ ሊቀዱ ወደ ጉድጓዱ ሲቀርቡ ዘንዶው ይወጣና እንዲሸሹ ያደርግ ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ትንሿ ልጅ ወደ ጉድጓዱ ሄዳ ውሃ ልትቀዳ ስታጎነብስ ዘንዶው ይዟት ወደ ውሃው ውስጥ ካስገባት በኋላ ሳሙና (ኦሞ) በውሃ በመበጥበጥ እንዲያዳልጣትና መውጣት እንዳትችል አደረገ፡፡ ትንሿ ልጅ ወደቤት ሳትመለስ በመቅረቷ ታላቅ እህታቸው በጣም ተጨነቀች፡፡
ከዚያም “የት አለች? ለምንድነው የቆየችው? ዘንዶው ይዟት ወደ ጉድጓድ ጎትቶ አስገብቷት ይሆን እንዴ?” እያለች ትረበሽ ጀመር፡፡
ከዚያም ወደ ውሃው ጉድጓድ ሮጣ ስትሄድ ትንሿ እህቷ ከጉድጓዱ ልትወጣ ስትሞክር እየተንሸራተተች ስትወድቅ አየቻት፡፡ በዚህ ጊዜ ዘንዶው ልጅቷ እስክትሞት ድረስ ጠብቆ ሊበላት ይጠባበቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ትልቋ እህቷ እጇን ይዛ በመጎተት ከጉድጓዱ አውጥታት ወደቤት ይዛት በመሄድ ትንሿን እህቷን አረጋጋቻት፡፡
ሌሊቱን ሙሉ ትልቋ እህታቸው ዘንዶውን እንዴት ልትገድለው እንደምትችል ስታሰላስል አድራ ሲነጋ አንድ ወጥመድ አዘጋጅታ ሳንጃ ይዛ ሄደች፡፡
ከዚያም ዘንዶው እስካሁን ትንሿ ልጅ የሞተችና ውሃው ውስጥ ያለች መስሎት ሊበላት ከነበረበት ሲወጣ ሳንጃው ቆራርጦ እዚያው ገደለው፡፡
በመጨረሻም ትልቋ እህት ወጥመዷን ልታይ ወደ ጉድጓድ ስትመጣ ዘንዶውን ሞቶ አየችው፡፡ የሞተውን ዘንዶ ከጉድጓዱ አውጥታ ወርቁን ሁሉ በመውሰድ ሃብታም ሊሆኑ ቻሉ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|