የወንድ ልጆች እናት
በሻሚስ ሃቢብ ፋራህ የተተረከ
በአንድ ወቅት ፑንትላንድበጥንት የግብፃውያን የታሪክ ምንጭ መሠረት ፑንትላንድ የሚለው ስያሜ የመጣው “የፑንት ምድር” ከሚለው ሃረግ ነው፡፡ ይህ ስያሜ የሚያካልለው መልክአ ምድር አሁንም አከራካሪ ቢሆንም በሱማሊያ ውስጥ የሚገኝ ስፍራ ሊሆን ይችላል፡፡ ውስጥ የሚኖር ሁለት ሚስቶች ያሉት ሰው ነበር፡፡ የመጀመሪያዋ ሚስቱ ሴት ልጆች ብቻ ሲኖሯት ሁለተኛዋ ሚስቱ ግን ወንድ ልጆች ብቻ ነበሯት፡፡ ሁለተኛዋ ሚስቱ ወንዶች ስለነበራት ባሏ ይወዳትና “ብዙ ምሰሶዎች” (ጣሪያውን የሚደግፉ) እያለ ይጠራት ነበር፡፡ ሁለቱም ሚስቶች ጎን ለጎን ይኖሩ ነበር፡፡ በባህሉ መሰረት በቀኝ በኩል ያለው ጎጆ የመጀመሪያዋ ሚስት ሲሆን ተፈላጊነቷ አናሳ የሆነው ሚስት ጎጆ በግራ በኩል ያለው ነበር፡፡
ስለዚህ የመጀመሪያዋን ሚስት በር ዘግቶ “የሁለተኛዋን ሚስት በር ተጠቀሚ፡፡” አላት፡፡ ይህንን ያደረገው ሁለተኛዋን ሚስት ለማበረታታትና የመጀመሪያዋን ለማኮሰስ ነበር፡፡
ከዚያ በኋላ የመጀመሪያዋን ከቀኝ አቅጣጫ ወደ ግራ አቅጣጫ ቀየራት፡፡ ቅድሚያም ለሁለተኛዋ ሚስት መስጠት ጀመረ፡፡
ቤተሰቡ ዘላን ስለነበረ የመጀመሪዋ ሚስት ሰባት ሴት ልጆችን ስትወልድና ሁለተኛዋ ሁለት ወንድ ልጆችን ስትወልድ በአካባቢው ዝናብ ባለመኖሩ ለግጦሽ የሚሆን ሣር ስለጠፋ ከዚያ ቦታ ወደ ሌላ ሥፍራ መሄድ ነበረባቸው፡፡ ሰውየውም ፈረሱንና ሁለተኛዋን ሚስት ይዞ ወደተሻለ ቦታ በመሄድ የሰባት ሴት ልጆቹን እናት ግን ብቻዋን ጥሏት ሄደ፡፡ እንዲሞቱም ይፈልግ ስለነበረ ይሙቱ ብሎ ፈረደባቸው፡፡
የመንደሩ ሰዎች ሁሉ ለቀው ስለሄዱ እነርሱ ብቻቸውን ቀሩ፡፡ እንደ እድል ሆኖ ግን ዝናብ መዝነብ ስለጀመረ አካባቢው በሣር በመሸፈኑ የነበሯቸውን ጥቂት ፍየሎችና በጎች ይዘው በአምላክ እርዳታ በደስታ ይኖሩ ጀመር፡፡
በባህሉም መሠረት አባወራው እየተዘዋወረ መልካም ሳር ያለበትን ቦታ በማሰስ ቤተሰቡ ወዳለበት ቦታ ተመልሶ መጥቶ ወደ አዲሱ ስፍራ ይዟቸው ይመጣል፡፡ ታዲያ ይህም ሰው አካባቢውን ሲያስስ ወደ ቀድሞው ስፍራ ተመልሶ ይመጣና ዝናብ በመዝነቡ ውሃና ለምለም ሣር መኖሩን አየ፡፡ ጊዜው መሽቶ ስለነበረ አሁን ያለበት ስፍራ የመጀመሪያ ቤተሰቡን ጥሎ የሄደበት ቦታ መሆኑን አላስተዋለም ነበር፡፡
ከዚያም “እዚህ የሚኖረው ማነው?” ብሎ ሲጣራ አንዷ ሴት ልጁ “እኛ ልጆችህ ነን፡፡ አታውቀንም እንዴ?” አለችው፡፡
“አሃ! እናንተ ናችሁ እንዴ? ዝናብም ዘንቦ ሳር በቅሎላችኋል!” አላቸው፡፡
ልጁቹም “አዎን ሣርና ውሃ አለን፡፡ እባክህ ወደቤት ግባ፡፡ ዝናብ እየዘነበ ስለሆነ እሳት አቀጣጥዬ አሞቅሃለሁ፡፡” አለችው፡፡ ከዚያም አባትየው ከምድጃው አጠገብ ሲቀመጥ ልጅቷ ወደ እናቷ ሄዳ “አባቴ መጥቷል፡፡ ነገር ግን ወደ አንቺ አይደለም የመጣው፡፡ ‘ያቺ ሴት ምንም የሚረባ ነገር አትወልድም፡፡’ ብሏል፡፡ ነገር ግን አምላክ አሁንም ወንድ ልጅ ሊሰጥሽ ይችላልና አሁን አባታችን ብቻውን ስለመጣ ከሁለተኛዋ ሚስቱ ጋር ስላልሆነ ከፈለገሽ አትናደጂበት፡፡ ስለዚህ ገላሽን ታጥበሽ ሽቶሽን ተጠቀሚ፡፡” ብላ መከረቻት፡፡
በዚህ ሁኔታ ሴትየዋ እራሷን አዘጋጅታ ባሏም ወደ እርሷ ቤት ሄዶ አብሯት ስለተኛ አረገዘች፡፡ ነገር ግን በማግስቱ ጠዋት ሰውየው ወደ ሁለተኛ ሚስቱ ተመልሶ ሄዶ የመጀመሪያ ሚስቱ ወዳለችበት ስፍራ ይዟት ተመለሰ፡፡ የመጀመሪያ ሚስቱም ወንድ ልጅ ትወልዳለች ብሎ ስላልጠበቃት የመውለጃዋን ጊዜ በጉጉት አይጠብቅም ነበር፡፡
ነገር ግን ሁለተኛዋ ሚስት የሴትየዋን እርግዝና ባየች ጊዜ የመጀመሪያዋ ሚስት ላይ በማሾፍ “ወንድ ልጅ መውለድ ካለመቻሏም በላይ ይህ እርግዝና ህጋዊ አይደለም፡፡” ብላ የክፋት ንግግር ተናገረች፡፡ ባልየውም ሁለተኛ ሚስቱን ማበሳጨት ስላልፈለገ ከመጀመሪያ ሚስቱ ጋር መተኛቱን ካደ፡፡
ሆኖም የመጀመሪያዋ ሚስት ሴት ልጅ እናቷን “አባቴ እንቅልፍ ሲጥለው ቀለበቱንና የአንድ እግሩን ጫማ ወስደሽ ለማስረጃነት አስቀሪ፡፡” ብላ መክራት ነበር፡፡
በዚህም መሰረት የመንደሩ ሰው ሁሉ “እሱ ርቆ ሄዶ ስለነበረ ሴትየዋ ከሌላ ሰው ጋር ተኝታ ይሆናል፡፡” እያለ ሲያወራ የመጀመሪያ ሚስቱ “አይደለም፣ እኔ ዘንድ መጥቶ ነበር፡፡ ለማስረጃነትም ቀለበቱና የአንድ እግሩ ጫማ ይኸው፡፡” ብላ አሳየች፡፡
በዚህ ዓይነት የባልየው ልጅ መረገዙን ተቀበሉ፡፡
ነገር ግን ባልየው “እርግዝናው የእኔም ቢሆን የተረገዘችው ሴት ልጅ እንደሆነች አውቃለሁ፡፡” አለ፡፡
በዚህ ዓይነት ቆይተው አካባቢ የሚቀይሩበት ወቅት ሲደርስ ሚስቱ ዘጠኝ ወር ስለሞላት መውለጃዋ ተቃርቦ ነበር፡፡ እርዳታ ቢያስፈልጋትም እርሱ ግን እንደገና ፈረሱን፣ ምቾቱንና ሁለተኛ ሚስቱን ይዞ ሄደ፡፡ አሁንም እርጉዟ ሚስቱና ሰባቱ ሴት ልጆች ብቻቸውን በመንደሩ ቀሩ፡፡
የመንደሩ ሰው በሙሉ እንደሄደም ሴትየዋ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ በጣምም ደስ አላት፡፡ ባሏም ከሌላዋ ሚስቱ ያገኛቸውን ወንድ ልጆች በጣም በሚወደው የውርስ ስም ይጠራቸው ስለነበረ ይህችኛዋ ሚስት ያንን ስም ወስዳ ለአዲሱ ወንድ ልጇ ሰጠችው፡፡
ከዚያም ሰዎቹን ተከትላ ስትሄድ፣ስትሄድ ደረሰችባቸው፡፡ ምድጃና ካውያ ይዛ ነበር፡፡ ሰዎቹንም “መሬትም ይናወጥ፣ ሰማዩም ይንቀጥቀጥ እንጂ መሬቱን የሚወርሰውን ዱርባናንቲ የተባለ ወንድ ልጅ ወልጃለሁ፡፡” አለቻቸው፡፡
ባልየውም ይህንን ባየ ጊዜ ወደ ሁለተኛው ሚስቱ ሄዶ “ያንቺ ልጅ ከዚህ በኋላ ዱርባናንቲ አይደለም፡፡ ይህ ስም ለመጀመሪያ ሚስቴ ወንድ ልጅ ነው የሚሰጠው፡፡” ሲላት እርሷም በድንጋጤ ብዛት ወዲያው ሞተች ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|