አንበሳ፣ የእንስሳት ንጉስ
በኡስማን አብዱላሂ አህመድ የተተከ
በአንድ ወቅት አንበሳ፣ጅብ፣ቀበሮና ሌሎች እንስሳት ነበሩ፡፡ በጫካው ውስጥም እየሄዱ ሳለ ይርባቸውና አንድ ወፍራም ግመል ያያሉ፡፡ እናም የእንስሳት ንጉስ እንደመሆኑ መጠን አንበሳው አንድ ጊዜ ዘሎ የግመሉን አንገት ነክሶ ይገድለዋል፡፡ አንበሶች ስጋውን መብላት እንደማይወዱ ይታወቃል፡፡ ደሙን ብቻ ከአንገቱ በመምጠጥ የቀረው የግመል አካል መሬት ላይ ተዘርግቶ ቀረ፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው ወደ ሌሎቹ እንስሳት ሄዶ “እንካፈለው፡፡” አላቸው፡፡
ጅቡም “እኔ ስጋውን እከፋፍለዋለሁ፡፡ ሁለት እኩል ቦታ እንካፈለውና አንዱ መደብ ለአንበሳው ሌላው ደግሞ ለቀሩት እንስሳት ሁሉ ይሁን፡፡” አለ፡፡
አንበሳው በዚህ በጣም ስለተናደደ ጅቡን አንድ ጊዜ በጥፊ ፊቱ ላይ መትቶት ገደለው፡፡ ሌሎቹ ሁሉ እንስሳት ደነገጡ፡፡
ከዚያም አንበሳው ቀበሮውን ጠርቶ “በል አንተ አካፍል፡፡” አለው፡፡ ቀበሮውም ብዙ ካሰበ በኋላ እንደ ጅቡ መመታት ስላልፈለገ “ሁሉንም ውሰደው፡፡ ግመሉን በሙሉ ውሰደው፡፡” አለው፡፡
አንበሳውም በጣም ደስ አለው፡፡ “እንደዚህ ዓይነቱን አከፋፈል ማን ነገረህ? ጥሩ አድርገህ ነው ያካፈልከው፡፡” ሲለው ቀበሮው “ጅቡን ያቀመስከው ጥፊ ነው እንዴት ማካፈል እንዳለብኝ ያስተማረኝ፡፡” አለው፡፡
የቀሩት እንስሳት ሁሉ ግን ተበሳጭተው ነበር፡፡
ቀበሮውንም “አንተ ደደብ ነህ! የማትረባ! እንዴት ሁሉንም ለአንበሳው ትሰጣለህ?” ብለው ጮሁበት፡፡
እርሱም “እናንተ ናችሁ ደደብ! ለራሳችን የሚሆን መድቤ ቢሆን ኖሮ እንደ ጅቡ ሟች ነበርኩ፡፡” አላቸው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|