ውሻ እንዴት የሰው ጓደኛ እንደሆነ
በአብዱልሃኪም አብዱላሂ ጅብሪል የተተረከ
አደም በገነት ውስጥ ቆይቶ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ ሁሉም እንስሳት ተመልክተውት “ይህ ሁለት እግሮች ያሉት አዲስ እንስሳ ደግሞ ማነው?” ብለው ጠየቁ፡፡ ቀጥለውም “ሁለት እግሮች ብቻ ነው ያሉት! እንደ ጦጣ ሁለት እጆች ብቻ ቢኖረውም ከጦጣ ግን ይለያል፡፡” አሉ፡፡
ከዚያም መመራመራቸውን በመቀጠል “ከእኛ ምንድነው የሚፈለገው? ከእኛ ጋር በሰላም አብሮን መኖር ይችላል? እንዴት ነው የሚሆነው?” ማለት ጀመሩ፡፡
ስለዚህ ውሻው ወደ ሰው ሄዶ እንዲያናግረው ሲልኩት ውሻው ትዕዛዙን ተቀብሎ ወደ አደም በመሄድ “አንተ ሰው! አንተ አዲስ እንስሳ! ከእኛ ጋር ሆነህ በምድር ላይ በሰላም አብረን እንድንኖር ከፈለክ ልጠይቅህ ነው የመጣሁት፣ ወይስ ልትጣላን ትፈልጋለህ?” አለው፡፡
ሰውየውም “በሰላም አብሬአችሁ መኖር እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህ ስፍራ አዲስ ነኝ፡፡ ከገነት ነው የመጣሁትና ከእናንተ ጋር መኖር እፈልጋለሁ፡፡” አለው፡፡
“አሃ! ይህ መልካም ዜና ነው፡፡” ካለ በኋላ ውሻው ወደ ሌሎቹ እንስሳት በፍጥነት እየሮጠ ተመልሶ ሊነግራቸው ሄደ፡፡ ነገር ግን ሌሎቹ እንስሳት ውሻው በፍጥነት እየሮጠ በመመለስ ላይ መሆኑን ሲያዩ “ኧረ! አደም ውሻውን እያባረረው ስለሆነ እኛም መሸሽ አለብን፡፡” ብለው ሽሽታቸውን ተያያዙት፡፡
ሁሉም እንስሳት በመሸሽ ላይ እያሉ ውሻው ስለሁኔታው ነግሮ ሊያስቆማቸው በማሰብ “ውፍ!ውፍ!ቁሙ!ቁሙ!” እያለ ይከተላቸው ጀመር፡፡
ነገር ግን ሌሎቹ እንስሳት ስለፈሩ ሩጫቸውን ሲቀጥሉ ውሻው ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስለደከመው ወደ ሰው ተመልሶ ሲሄድ ሌሎቹ እንስሳት ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሰው ሸሽተው ቀሩ፡፡ ውሻው ግን የሰው ጓደኛ በመሆን “ውፍ!ውፍ!ቁም!ቁም!” እያለ መጮሁን ቀጠለ፡፡
አደምም እንስሳቱ የማይፈልጉት መስሎት በጠላትነት ያያቸውና ያድናቸው ጀመር፡፡ ውሻውን ግን አብሮት እየኖረ እንዲጠብቀው ጠየቀው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|