የቆንጆው ልጅ ህልም
በአብዱልሃኪም አብዱላሂ ጅብሪል የተተረከ
በአንድ ወቅት አንድ እጅግ ያማረ ልጅ ነበር፡፡ ሆኖም በጣም ድሃ ስለነበረ ህይወቱን የሚመራው በተሸካሚነት ነበረ፡፡ አንዳንዴ ምግብ ሲያገኝ አንዳንድ ቀናት ደግሞ ምንም የሚበላው ያጣ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን በሚሰራበት የዕቃ መጋዘን የተለመደ የሸክም ሥራውን እየሰራ ሳለ በጣም ስለራበው ትንሽ ገንዘብ ለምኖ ምግብ ለመግዛት መፈለጉን ያየው የመጋዘኑ ጠባቂ “አንተ በጣም ቆንጆ ልጅ ነህ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሥራ መስራት የለብህም፡፡ እኔ ያንተን መልክ መግዛት ብችል ኖሮ! መልክህን ተጠቅመህ ከሴቶች ገንዘብ ማግኘት ትችላለህ እኮ!” አለው፡፡ ልጁም “ምን? እንደዚህ ይቻላል እንዴ?” ሲለው “አዎ በእርግጥ ይቻላል፡፡” አለው፡፡ ጥቂት ከተከራከሩ በኋላ ልጁ “ለማንኛውም አሁን ምግብ የምገዛበት ትንሽ ገንዘብ ስጠኝ፡፡” ብሎ የመጋዘኑን ጠባቂ ቢጠይቀው “አልሰጥህም፣ሄደህ አንዲት ሃብታም ሴት ፈልገህ አብረሃት እደርና በዚህ ዓይነት ገንዘብ አግኝ፡፡” አለው፡፡
ልጁም “እውነት ይህንን አደርግ ዘንድ ነው የምታበረታታኝ?” ብሎ ሲጠይቀው “አዎ በምትችለው ሁሉ ራስህን እርዳ እንጂ እንደዚህ መለመን የለብህም፡፡” አለው፡፡
እናም የዚያን ዕለት ከሰአት በኋላ የመጋዘኑ ጠባቂ ሚስት “ኩሊ! ኪሊ!” ብላ ስትጣራ ልጁ ጋሪውን እየገፋ ወደ እርሷ ሄደ፡፡ ሚስትየውም “በል ይህንን እቃ ወደቤቴ ውሰድልኝ፡፡” ብላው ልጁም እቃውን በጋሪ እየገፋ ወሰደላት፡፡ እቤትም እንደደረሱ “ቆንጆ ልጅ ስለሆንክ ወደድኩህ፡፡ዛሬ ማታ ተመልሰህ ናና ገንዘብ እሰጥሃለሁ፡፡” አለችው፡፡ ከዚያም ልጁ ወደ መጋዘኑ ጠባቂ ሄዶ “እውነትህን ነው፡፡ እነሆ ዛሬ ከሰአት በኋላ አንዲት ሴት “ኩሊ!ኩሊ!” ብላ ጠርታኝ ወደቤቷ ስሄድ ገንዘብ ሰጥታኝ ዛሬ ማታ ተመልሼ እንድሄድ ጠርታኛለች፡፡” አለው፡፡
ሰውየውም “ይህች ሴት ማናት? ቤቷስ የት ነው?” ብሎ ሲጠይቀው ልጁ በዝርዝር ሲነግረው የመጋዘኑ ጠባቂ የራሱ ሚስት መሆኗን ስለተረዳ ምንም ነገር አላለም፡፡
“እንዳለችህ አድርግ፡፡ ወደ ቤቷም ሂድ፡፡” አለው፡፡
እናም ልጁ የዚያን ቀን ምሽት ወደ ሴትየዋ ቤት ሲሄድ ልብስ እየተኮሰች ነበር፡፡ ሆኖም ልጁ ቤት እንደገባ ባልየው በሩን አንኳኳ፡፡ ወዲያው ሴትየዋ ልጁን ልብስ ከምትተኩስበት ሳጥን ስር ደብቃው በሩን ልትከፍት ሄደች፡፡ ባልየውም ልጁ እዚያ ሊሆን እንደሚችል ስለጠረጠረ ቤቱን ሁሉ ቢያስስም አላገኘውም፡፡
ከዚያም “የሆነ ሰው አለ! የሆነ ሰው እዚህ አለ!” ማለት ጀመረ፡፡ ሆኖም ልጁን ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በመጨረሻም ባልየው ከቤት ሲወጣ ልጁ ከተደበቀበት ወጥቶ እየሮጠ ሄደ፡፡
በማግስቱ የመጋዘኑ ጠባቂ ልጁን በጠዋት ጠርቶ “ታዲያ እንዳልከው ወደዚያ ቤት ትናንት ማታ ሄድክ?” አለው፡፡
ልጁም “አዎ! ነገር ግን ገና ከመግባቴና ምንም ከማድረጌ በፊት ባልየው በሩን አንኳኳ፡፡ ወዲያው ታዲያ ሴትየዋ ልብስ ከምትተኩስበት ሳጥን ስር ደብቃኝ በሩን ከፈተችው፡፡ ባልየውም ቢፈልግ፣ቢፈልግ ሊያገኘኝ ስላልቻለ ተመልሶ ሲወጣ ከተደበኩበት ወጥቼ ሮጥኩ፡፡” አለው፡፡
ባልየውም “ተመልሰህ ትሄዳለህ እንዴ ታዲያ?” ብሎ ሲጠይቀው “አዎ” ብሎ መለሰለት፡፡ የሚሄድበትንም ቀን ነገረው፡፡
በዚያንም ዕለት ተመሳሳይ ነገር ሆነ፡፡ ነገር ግን በዚህን ጊዜ ሚስቱ ልጁን የውሃ በርሜል ውስጥ ደብቃው ልብስ ታጥብበት የነበረውን ሳፋ ከደነችበት፡፡ ከዚያም በሩን ስትከፍት ባልየው ቢፈልግ፣ቢፈልግ ልጁን አጣው፡፡
በዚህ ጊዜ ሚስቲቱ ጎረቤቶቿን ሁሉ ሰብስባ “ባለቤቴ አብዷል፡፡ ትናንት ማታ እንደዚህ አደረገ፡፡ ዛሬም ይኸው ደገመ፡፡” አለቻቸው፡፡
ማንም ልጁን በቤቱ ውስጥ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በመጨረሻም ባልየው ከቤት ወጥቶ ሲሄድ ልጁ ወዲያው ከበርሜሉ ውስጥ ወጥቶ አመለጠ፡፡ በማግስቱ ጠዋት ሰውየው ልጁን አገኘው፡፡
“ትናንት ማታም ሄደህ ነበር?”
“አዎ፡፡ እናም ባልየው ሲመጣ ሴትየዋ ጎረቤቶቿን ሰብስባ ስትጮህ ትልቅ ብጥብጥ ነበር፡፡ እኔ ግን በርሜሉ ውስጥ ነበርኩ፡፡” አለ፡፡
“ዛሬ ማታስ ትሄዳለህ?”
“አዎ”
እናም ሲመሽ ልጁ እንደገና ሲሄድ የሴትየዋ እናት የልብስ ሳጥን ውስጥ ተደበቀ፡፡ ሰውየው ሁሉም ቦታ ቢፈትሽም የአማቱን ሳጥን ግን መክፈት አልቻለም፡፡ ከዚያም “ቤቱን በሙሉ አቃጥለዋለሁ፡፡” አለ፡፡
ሚስቱም “ቤቱ ያንተ ስለሆነ ማቃጠል ትችላለህ፡፡ የእናቴን ሳጥን ግን ማቃጠል አትችልም፡፡” ስትለው “ከፍቼ ውስጡን ልመልከት፡፡” አላት፡፡
እሷም “አይቻልም፣ቁልፉም ከእናቴ ዘንድ ነው፡፡” ስትለው
“እንግዲያው እሰብረዋለሁ፡፡” አለ፡፡
“እሰብረዋለሁ? ልትሰብረውማ አትችልም!” ስትለው ከቤት ወጣ፡፡ በዚህ ጊዜ ልጁ ከሳጥኑ ውስጥ ወጥቶ አመለጠ፡፡
በማግስቱም ሰውየው ልጁን “ትናንትና ማታ ሄደህ ነበር?” አለው፡፡ ልጁም “አዎ፡፡ ሳጥን ውስጥ ነበርኩ፡፡ እነርሱም ሲጣሉ ጎረቤቱ ሁሉ ተሰብስቦ ሰውየው ቤቱን ካላቃጠልኩ አለ፡፡” ብሎ ነገረው፡፡
“ዛሬ ማታስ ትሄዳለህ?”
“አልሄድም፡፡ ሴትየዋ በጣም ስለተናደደች ከዚህ ሰው ጋር መኖር አልችልም ብላ ባሏን ጥላ ወደቤተሰቦቿ ዘንድ ሄዳለች፡፡”
በዚህ ጊዜ ባለመጋዘኑ ሰው ልጁን “ተከተለኝ፡፡ አንድ ስራ እሰጥሃለሁ፡፡” ብሎ አስከትሎት ወደ ሚስቱ ቤተሰቦች በመሄድ ሚስቱን ይዞ ሊመለስ ተያይዘው አመሩ፡፡ እዚያም ሲደርሱ ልጁ ከቤቱ ውጪ ሆኖ ከአካባቢው ሰዎች ጋር ይነጋገር ጀመር፡፡ ለሰዎቹም የሆነውን አስደናቂ ነገር ሁሉ በመዘርዘር ሳጥኑ ውስጥ እስከነበረበት ጊዜ ያለውን ሁኔታ ተረከላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ከቤት ውስጥ ስትወጣ ተመለከታት፡፡ እርሷም ልጁ ስለ እርሷ ለሰዎቹ እየነገራቸው መሆኑን ስላስተዋለች ምልክት ሰጠችው፡፡ እርሱም እንዳያት የሰጠችውን ምልክት ስለተረዳ ወዲያው ለሰዎቹ እንዲህ አላቸው፡፡ “በዚህ ቅፅበት እርሷ ሳጥኑን ስትከድነው ከእንቅልፌ ባንኜ ነቃሁ፡፡” ሲላቸው “ምን ማለትህ ነው?” አሉት፡፡
“ህልም እያየሁ ነበር፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም “እውነት? እነዚህን ነገሮች ሁሉ ማለም ይቻላል?” ሲሉት
“አዎ” አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ወደ ሰውየው ሄደው “አዳምጥ፣ ይህ ልጅ ሁሉንም ነገር ነግሮናል፡፡ ሆኖም ነገሩ ሁሉ ህልም ነበር፡፡ እንዴት ይህንን አምርረህ ታየዋለህ? አብደሃል እንዴ?” አሉት ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|