ብልኋ ሴትና ሥህተት የማያጣው ሼኪ
በአብዱልሃኪም አብዱላሂ ጅብሪል የተተረከ
በአንድ መንደር የሚኖርና ለመንደሩ ሰዎች ከጉድጓድ ውሃ እየቀዳ የሚኖር ሼኪ ነበር፡፡ አንዲት በመንደሩ የምትኖር ሴትን ቢያፈቅርም ሴትየዋ ያገባች ነበረች፡፡
ልጇንም ወደ ጉድጓዱ በላከች ጊዜ ሼኪው “አይሆንም፣ አንተ ውሃውን መውሰድ አትችልም፡፡ አንተ በጣም ትንሽ ልጅ ስለሆንክ እናትህ መጥታ ውሃውን ትውሰድ፡፡” አለው፡፡
ከዚያም ሴትየዋ ውሃውን ልትወስድ ስትመጣ ሼኪው ብልህነቷንና ውበቷን ማድነቅ ጀመረ፡፡ በመጨረሻም በፍቅሩ ብትወድቅም ስሜቷን ለማንም ሳትነግር ውስጥ ውስጧን በፀጥታና በሃሳብ ትናጥ ጀመር፡፡ ወደ ቤቷም ተመልሳ ከባሏ ጋር ስለጉዳዩ መወያየት በመፈለግ ባሏን “ይህ ሰው ወዶኛል መሰለኝ በምስጢር እንዳገኘው ይፈልጋል፡፡ የማደርገው ነገር ግራ ስለገባኝና ባለትዳር በመሆኔ ከዚህ ዓይነቱ ጣጣ ያለምንም ፀብና ጭቅጭቅ እንዴት እንደምንወጣ እንድንማከር ፈልጌ ነበር፡፡ ሰውየው ሃሳቡን እንዲተው ማድረግ አለብን፣ ግን እንዴት?” አለችው፡፡ ከዚያም ብዙ ከተወያዩ በኋላ ወደሰውየው ተመልሳ ሄዳ ባሏ እንደሌለና ዛሬ አብረው ማምሸትና ማደር እንደሚችሉ ልትነግረው ተስማሙ፡፡ በእቅዳቸው መሰረት ሼኪው ወደቤቷ እንደመጣ ባሏ ወደ ቤት ተመልሶ የቆለፈችውን በር ያንኳኳል፡፡ ከዚያም ሴትየዋ በአስቸኳይ ሼኪውን የሴት ቀሚስ አልብሳ ሴት እንዲመስል እንድታደርገው ተስማሙ፡፡
ይህንን ካሴሩ በኋላ ሴትየዋ ውሃ ልትቀዳ ስትሄድ ሼኪው እንዳያት ብቻዋን ሊያገኛት እንደሚፈልግ በልመና ነገራት፡፡ ከዚህ በፊት መልስ ሰጥታው ባታውቅም አሁን ግን “ትልቅ ሰው ብዙ ዓይኖች አሉት፡፡ ይህም ማለት ሁሉንም ነገር ይገነዘባል ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ምን እንደምትፈልግ አውቄያለሁ፡፡ እስካሁን ዝም ያልኩህም ባለቤቴ ስላለ ነበር፡፡ አሁን ግን እርሱ ስለሄደ መልካም አጋጣሚ ነውና ወደ ቤቴ መጥተህ መጨዋወትና የፈለግነውን ማድረግ እንችላለን፡፡” አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ ሼኪው በጣም በደስታ ፈነደቀ፡፡
“መቼ መምጣት እችላለሁ?” አላት፡፡
እሷም “የምሽት ፀሎትህን እንዳደረስክ ና፡፡” አለችው፡፡ በሃሳቡ ወዲያው ቢስማማም አንድ ሃሳብ ገባው፡፡ “ሚስቴን ምን እላታለሁ? በምሽት ከቤቴ ወጥቼ አላውቅ! አሳማኝ ምክንያት ካላገኘሁ መጠራጠሯ አይቀርም፡፡” እያለ ማሰብ ጀመረ፡፡
በመጨረሻም የዚያን ዕለት እስከ ምሽቱ አራት ሰአት ድረስ እንደሚያመሽ ሲነግራት እሷም “ለምን? ይህ ያልተለመደ ነው፡፡ በምሽት ውጪ አምሽተህ አታውቅም፡፡” አለችው፡፡ እርሱም “አንድ ለመተርጎም እጅግ አስቸጋሪ የሆነ የቁርዓን ጥቅስ አለ፡፡ እኔ ሼኪ በመሆኔ ሰዎች እንዳስረዳቸው ለስብሰባ ጠርተውኛል፡፡” አላት፡፡
ሚስቱም “አሃ! እንደዚያ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይማ ከሆነ መሄድ አለብህ፡፡” ስትለው እርሱም ወደ ሴትየዋ ቤት ሄደ፡፡ ቤቱ ውስጥ እንደገባም የሚያምረውን ምንጣፍ አንጥፋ ሻይ ሰጠችው፡፡ ሻዩን ጠጥቶ ሳይጨርስም በሩን ቆለፈችው፡፡
ከዚያም ከባሏ ጋር በተስማሙት መሰረት ልክ በሩ እንደተቆለፈ ባሏ በሩን እያንኳኳ “ሚስቴ! ሚስቴ! አውቶብስ ስላላገኘሁ ተመልሼ መጣሁ፡፡” እያለ መጣራት ጀመረ፡፡ ሼኪውም ባሏ ለመሄድ አለመቻሉን እንደሰማ በድንጋጤ ራደ፡፡
ሚስቱም “ጉዳችን ነው! ባለቤቴ ተመልሶ መጣ፡፡” ብላ ለሼኪው በለሆሳስ ነገረችው፡፡
ሼኪውም “ምን ይሻላል?” ሲላት እርሷም “እኔ አንድ መላ አለኝ፡፡ የእኔን ቀሚስ ልበስና እደብቅሃለሁ፡፡ እርሱም ማን ያወራ እንደነበረ ከጠየቀኝ የቤት ሠራተኛዬ ናት እለዋለሁ፡፡” አለችው፡፡
በዚህ ዓይነት ቀሚሷን ሰጥታው ከለበሰ በኋላ በሩን ከፈተችው፡፡ እርሷም የአንገት ልብሷን በፊቷ ላይ ሸፍና አይን አፋር ለመምሰል ሞከረች፡፡
ባልየውም ወደ ቤት ገብቶ “ሚስቴ ሆይ፣ አንድ ከረጢት በቆሎ ይዤልሽ መጥቻለሁ፡፡” አላት፡፡
ሚስቱም “በጣም ጥሩ ነው፡፡” አለችው፡፡
እርሱም “በጣም እድለኛ ነሽ፡፡ በቆሎው ስላልተወቀጠ የቤት ሰራተኛዋ መኖሯ ጥሩ ነው፡፡ በቆሎው ብዙ ነውና በይ ሙቀጫውንና ዘነዘናውን አምጥተሽ መውቀጡን ትጀምር፡፡” አለ፡፡
እናም ሼኪው በቆሎውን መውቀጥ ጀመረ፡፡ ባልየውም ሼኪው አጠገብ ስለተቀመጠ ሼኪው ፊቱን አዙሮ መውቀጡን ቀጠለ፡፡ በቆሎውን ሲወቅጥ፣ ሲወቅጥ ቆይቶ “ይሄ ሰውዬ ለምን ከአጠገቤ አይሄድም፡፡ ይህንን ሁሉ በቆሎ መውቀጥ ደክሞኛል፡፡” ብሎ ያስብ ጀመር፡፡ ሆኖም በቆሎው ሁሉ እስኪያልቅ መውቀጡን ቀጥሎ ልክ እንደጨረሰ ሚስትየው “በጣም ጥሩ፣ ጥሩ ስለሰራሽ አሁን መሄድ ትችያለሽ፡፡” አለችው፡፡
ሼኪውም ወደቤቱ እግሬ አውጪኝ እያለ ሲሄድ ቀሚሱን ማውለቁን ስለረሳው ሚስቱ ስታየው ደንግጣ “እንዴ! የሴት ቀሚስ እኮ ነው የለበስከው፡፡ ቁርዓን ደግሞ ወንድ ልጅ የሴት ልጅ ቀሚስ ከለበሰ ትልቅ ኃጢያት ነው ይላል፡፡” አለችው፡፡
ሼኪውም “ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ ቁርዓን ውስጥ ያለውንና ሰይጣንን የተረገመ እንደሆነ የሚናገረውን ጥቅስ እየተወያየን ሳለ ሰይጣኑ ራሱ መጣ፡፡ ወዲያውም እያንዳንዳችንን መግረፍ ሲጀምር እንዳጋጣሚ አጠገቤ ያገኘሁትን የሴት ቀሚስ ስለለበስኩ ሰይጣን እንኳን ሴት ልጅን መምታት ሃፍረት ሆኖበት ሮጬ እንድሄድ ፈቀደልኝ፡፡” አላት፡፡
ሚስቱም “አሃ! የሴት ቀሚስ ብትለብስም ራስህን ለማትረፍ በመቻልህ ጥሩ አድርገሃል፡፡” አለችው፡፡
በሚቀጥለው ቀን ያፈቀራት ሴት ወደ ውሃው ጉድጓድ መጥታ ሼኪውን “ዛሬ ማታ ባለቤቴ በእርግጠኝነት ስለሚሄድ ወደ ቤት እንድትመጣ፡፡” አለችው፡፡
ሼኪውም “በፍፁም አይሆንም፡፡ ምሽቱን ሙሉ በቆሎ ስወቅጥ ማምሸት አልፈልግም፡፡ ይህንን ማድረግ ከፈለኩ እቤቴ ብዙ በቆሎ አለ፡፡” አላት ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|