ሂርሲና ካባላፍ
በኦስማን አብዱላሂ አህመድ የተተረከ
ክፍል 1
በአንድ ወቅት ሁለት ሂርሲና ካባላፍ የተባሉ ሌቦች ነበሩ፡፡ ሁለቱም በአጎራባች ከተሞች የሚኖሩና በየከተሞቻቸው የታወቁ ሌቦች ሲሆኑ እርስ በርስም ይተዋወቁ ነበር፡፡
ከእለታት አንድ ቀን አንደኛው ወደ ሌላኛው መንድር ሄደው ሰዎችን ለማታለል በመወሰን አንደኛው አንድ ከረጢት አመድ በፈረሱ ላይ ጭኖ ዱቄት ነው ብሎ ለመሸጥ ሲወስን ሌላኛው ደግሞ የፍየል በጠጥ ወስዶ ቡና ነው ብሎ ለመሸጥ ወሰነ፡፡ በመንገዳቸውም ላይ ሁለቱም ሌቦች ተገናኝተው ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ አንደኛው “ወደ ገበያ እየሄድክ ነው?” ብሎ ሌላኛውን ሲጠይቀው “አዎ” ብሎ መለሰለት፡፡
“ምን ይዘሃል?”
“አንድ ከረጢት ዱቄት፡፡”
“በጣም ይገርማል፡፡ እኔም የምፈልገው አንድ ከረጢት ዱቄት እኮ ነው፡፡ እኔ ደግሞ አንድ ከረጢት ቡና አለኝ፡፡”
“ይሄ እጅግ የሚደንቅ ነገር ነው፡፡ እኔ ቡና አይደለም እንዴ የምፈልገው! በል አሁን ገበያ ድረስ መሄድ የለብንም፡፡ መቼም እድለኞች ነን፡፡ በል እንለዋወጥ፡፡”
ይህንን ተባብለው ከተለዋወጡ በኋላ ወደየቤታቸው ሲደርሱ ሁለቱም ከረጢቶቻቸውን ወደ ገበያ ወስደው የያዙትን ሊሸጡ ሲያዩት ሁለቱም መታለላቸውን አወቁ፡፡ ይህ የሚያሳየው አታላዮች ራሳቸው ሊታለሉ እንደሚችሉ ነው፡፡
ክፍል 2
ከእለታት አንድ ቀን ሂርሲና ካባላፍ ተገናኝተው በጋራ አንድ ተንኮል ጠነሰሱ፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ አንዲት ሴት በአንድ እጇ ጭንቅላቷ ላይ የቅቤ እቃ ይዛ በሌላ እጇ ደግሞ ሙክት በግ እየጎተተች ስትሄድ አዩአት፡፡ ሁለቱም እጆቿ መያዛቸውን በማስተዋል አንደኛው ቀድሟት ሄዶ አይነ ስውር በመምሰል ቁጭ ብሎ “እባካችሁ ወደምሄድበት ስፍራ የሚመራኝ ሰው እፈልጋለሁ፡፡” እያለ መለመን ጀመረ፡፡
ሴትየዋም “አይ አንተ ምስኪን አይነ ስውር!” በማለት ወደ እርሱ ጠጋ ብላ “በዓይነ ስውርነትህ አዝናለሁ፤፤ ልረዳህም እፈልግ ነበር ነገር ግን ሁለቱም እጆቼ ተይዘዋል፡፡ አንደኛው እጄ ሙክቱን በገመድ ሲጎትት ሌላኛው ደግሞ የቅቤውን እቃ ስለያዘ ልረዳህ አልችልም፡፡” አለችው፡፡
“ኧረ ትችያለሽ! ገመዱን አሲዥኝና እኔ ሙክቱን ስጎትትልሽ ዘንጌን በዚያ እጅሽ ይዘሽ ወደምሄድበት ልትመሪኝ ትችያለሽ፡፡” አላት፡፡
እሷም “ጥሩ ሃሳብ ነው፡፡” በማለት ዘንጉን ተቀብላው ገመዱን ሰጠችው፡፡ ጥቂት ከተጓዙም በኋላ ሌላኛው ሌባ ተከትሏቸው መጥቶ ሳያዩት ገመዱን ከሙክቱ አንገት ላይ በማውለቅ በጉን ይዞት ሄደ፡፡
ውሸታሙም ዓይነ ስውሩ ሌባ “ኧረ ገመዱ ቀሎኛል፡፡ ምን ሆኖ ነው?” አለ፡፡
በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ዞር ብላ ስትመለከት ሙክቱ የለም፡፡
ሌባውም “እኔ ምንም ነገር አላየሁም፡፡ ገመዱ ብቻ ነው በጣም ሲቀለኝ የታወቀኝ፡፡” አላት፡፡
ሴትየዋም “ታዲያ አሁን ምን እናድርግ?” ስትል ሌባውም “ለምን አንቺ ተመልሰሽ በጉን አትፈልጊውም? እኔ እዚህ ቁጭ ብዬ ቅቤውን እጠብቅልሻለሁ፡፡” አላት፡፡
እሷም በሃሳቡ ተስማምታ በጉን ልትፈልግ ስትመለስ ሌባው ቅቤውን ይዞ ተሰወረ፡፡ ከዚያም ሁለቱ ሌቦች ጫካው ውስጥ ተገናኝተው በጉንና ቅቤውን ከበሉ በኋላ ሁለቱም በጣም ታመሙ፡፡
“ምን ሆነህ ነው?” መባባል ጀመሩ፡፡ ከዚያም “አይ! መጥፎ ሥራ ነው የሰራነው፡፡ ወደ ገበያ ከምትሄድ ሴት ላይ በግና ቅቤ ወሰድንባት፡፡ ምናልባት እኮ ልጆች ይኖራት ይሆናል፡፡ አሁን እኛ ልንሞት በመሆናችን በጣም እናዝናለን፡፡” አሉ፡፡
የዚህ ታሪክ መልዕከት ሰው ባይቀጣህም አምላክ ይቀጣሃል የሚል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|