የሙሽራዋ ፈተና
በኦስማን አብዱላሂ አህመድ የተተረከ
በአንድ ወቅት ከአንዲት ልጃገረድ ጋር መጥፋት የፈለገ ልጅ ነበር፡፡ ያፈቅራት ነበርና እርሷም ከእርሱ ጋር ለመሄድ ፍቃደኛ ብትሆንም ወላጆቿ ግን ጋብቻውን አልተቀበሉም ነበር፡፡ ስለዚህ ልጁ ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆን በሌሊት ወጥተው ሊጋቡ ወደሚችሉበት ቦታ ለመሄድ ሌሊቱን ሙሉ ተጉዘው አድረው ሲነጋ ልጅቷ “ቁርስ እንብላ፡፡” አለች፡፡
ነገር ግን ምንም የሚበላ ነገር አልነበረምና እጮኛዋ ሊገባው አልቻለም፡፡ “እዚህ የሚበላ ነገር እንደሌለ ታውቂ የለም እንዴ?” አላት፡፡
ሚዜው ግን ምን ለማለት እንደፈለገች ስለገባው “አይደለም፣ ሴትየዋ ለማለት የፈለገችው ጥርሳችንን እናፅዳ ነው፡፡ ይህም ቁርስ እንደመብላት ይቆጠራል እንጂ የምንበላውማ ምንም ነገር የለም፡፡” አለ፡፡
ወጣቱም ልጅ እጮኛውን “እውነት? እንደዚያ ነው ማለት የፈለግሽው?” ሲላት እሷም “አዎ በእርግጥ እንደዚያ ማለት ነው የፈለኩት፡፡” ብላ በትዕግስት አልባነት መለሰችለት፡፡ ይህም የመጀመሪያ ፈተናዋ ነበር፡፡
እናም ጉዟቸውን ቀጥለው እኩለ ቀን ላይ በጣም ደከማቸው፡፡ ስለዚህ ሙሽራዋ “ስለደከመን እንረፍ፡፡” አለች፡፡
እናም ሁሉም ከአንድ ዛፍ ስር ተቀምጠው ሙሽራዋና ሚዜው ጫማዎቻቸውን ሲያወልቁ ወጣቱ ልጅ ጫማውን አላወለቀም ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ልጅቷ “አረፍ በል፡፡” አለችው፡፡
ወጣቱም ልጅ “እያረፍኩ እኮ ነው፡፡” አላት፡፡
ልጅቷም “እንዴት ደደብ ነው! ጫማዎቹን ሳያወልቅ እንዴት ሊያርፍ ይችላል?” ብላ አሰበች፡፡
ሚዜውም “ጫማዎችህን አውልቅ ነው የምትልህ፡፡ ምክንያቱም ጫማህን አድርገህ በደንብ ማረፍ አትችልም፡፡” አለው፡፡ ሶስተኛውም ፈተና መንደሩ ዘንድ ሲደርሱና ሰዎቹ አብረዋቸው ሥጋ እንዲበሉ ሲጋብዟቸው የሆነ ነው፡፡
ሥጋውን ከበሉ በኋላም ልጅቷ “የቀረውን ሥጋ እናውጣ፡፡” ስትል እጮኛዋ “ምን? ምን ማለትሽ ነው?” ብሎ ጠየቃት፡፡
እሷም በሃሳቧ “እንዴ! እንዴት ያለ ደደብ ነው?” አለች፡፡ ሆኖም ምንም አልተናገረችም፡፡
ከዚያም ሚዜው ስንጥር አንስቶ ጥርሱን መጎርጎር ጀመረ፡፡ “እንደዚህ ማለት ፈልጋ ነው፡፡” አለው ሚዜው፡፡
ወጣቱም ልጅ “እንደዚያ ነው እንዴ? እንደዚህ ማለት ፈልጋ ነው? እኔ እኮ አልገባኝም፡፡” አለ፡፡
በዚህ ጊዜ ወጣቷ ልጅ “ምንም ነገር አይገባህም፡፡” አለችው፡፡
በመጨረሻም ሊያጋባቸው ወደተዘጋጀው ሼኪ ቤት ደረሱ፡፡ ሆኖም ልጀቷ አሻፈረኝ አለች፡፡
“ይህንን ሰው አልወደውም፡፡ እኔ ላገባው የምፈልገው ጓደኛውን ስለሆነ ሊያገባኝ ከፈለገ ደስ ይለኛል፡፡” አለች፡፡
የዚህ ታሪክ መልዕክትም ሁልጊዜ መምረጥ ያለብን በጉብዝና፣ በመልክ እንዲሁም በሃብት ከራሳችን ያነሰ ሚዜ እንደሆነ ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|