አባ ቡኩሽ
በዩሱፍ አደም ማንደሬ የተተረከ
ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ አባ ቡኩሽ የሚባል ሰው ነበረ፡፡ በጣም ቄንጠኛ ሰው ሲሆን ንጉሱን በጣም ያስቀው ስለነበረ ንጉሱም አባ ቡኩሽ ማለትም ‘የሳቅ አባት’ ብሎ ስም አወጣለት፡፡ አባ ቡኩሽ ሁልጊዜ ከንጉሱ ጎን ነበር የሚቀመጠው፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ታዲያ ጓደኛውን “ንጉሱ በጣም ጥሩ ሰው ነው፡፡ ነገር ግን አንድ አፈወርቅ የሚባል ሰው ስህተት ሲሰራ አልቀጣውም፡፡ አንድ ዓይነት ቅጣት ሊጥልበት ይገባ ነበር፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ የአባ ቡኩሽ ጓደኛ ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄዶ አባ ቡኩሽ የተናገረውን ነገር ነገረው፡፡ ንጉሡም “አሃ! በእኔ ላይ ንቀት እያደረበት ነው ማለት ነው፡፡” ብሎ በአባ ቡኩሽ በጣም ተበሳጨበት፡፡
ከዚያም ሶስት ወታደሮቹን አስጠርቶ ወደ አባ ቡኩሽ ቤት ሄደው ፍራሹ ላይ ሠገራ እንዲፀዳዱበት አዘዛቸው፡፡
ስለዚህ ወታደሮቹ በታዘዙት መሠረት ወደ አባ ቡኩሽ ቤት ሄደው “ፍራሽህ ላይ እንድንፀዳዳ ታዘናል፡፡” ብለው ነገሩት፡፡
ወታደሮቹም ፍራሹን ከቤት ውስጥ አውጥተው ሊፀዳዱበት ሲዘጋጁ አባ ቡኩሽ ትልቅ ዱላ ይዞ መጥቶ “በሉ እንግዲህ ንጉሱ ያዘዛችሁ ሰገራችሁን እንድትፀዳዱ አንጂ ሽንታችሁን እንድትሸኑ ስላልሆነ ፍራሼ ላይ አንዲት የሽንት ጠብታ ባይ ጭንቅላታችሁን በዚህ ዱላ ነው የማፈርሰው፡፡” አላቸው፡፡
ወታደሮቹም ሳይሸኑ መፀዳዳት ስለማይችሉ በጣም ግራ ስለተጋቡ ወደ ንጉሱ ተመልሰው ሄደው ስለሁኔታው ነገሩት፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሱ በጣም ተደንቆ በመሳቅ ወታደሮቹ ለአባ ቡኩሽ ስጦታ ይዘውለት እንዲሄዱ አዘዛቸው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|