በድርቅ የተሰነጣጠቀው መሬት
በሞጌ አብዲ ኡመር የተተረከ
በአንድ ወቅት አንድ ልጅና እናቱ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ከመንደሯ ርቃ ወደምትገኘው ያገባች ልጇን ለመጠየቅ መሄድ ፈልገው በጠዋት ከወንድ ልጇ ጋር ተነስተው በእግራቸው በመጓዝ ሙሉ ቀን ሲሄዱ ስለሚውሉ ጥቂት ምግብና ውሃ ይዘው ስለነበረ ምግብና ውሃው መንገድ ላይ አለቀባቸው፡፡ እየተጓዙ ሳለም ልጁ መሬቱ ደርቆ መሰነጣጠቁን አየ፡፡
በዚህ ጊዜ “ለምንድነው መሬቱ የተሰነጣጠቀው፣ እማማ?” ብሎ እናቱን ጠየቃት፡፡
እናትየውም “ውሃ ጠምቶት ነው፡፡” አለችው፡፡
ልጁም “አሃ! ታዲያ ውሃ ስለያዝን ለምን አናጠጣውም?” አለ፡፡
“ውሃውን ለመሬቱ ከሰጠኸው አንተ ሲጠማህ ምን ትጠጣለህ?”
“አይ፣ እኔ አልጠማኝም፡፡”
“በኋላ ይጠማሃላ!”
“መሬቱ ግን አሁን ጠምቶታል፡፡” ብሎ የያዘውን ውሃ በሙሉ መሬቱ ላይ አፈሰሰው፡፡
ከዚያም ሲጓዙ፣ ሲጓዙ ልጁ ውሃ ጠማው፡፡ እናም “እማዬ እባክሽ ውሃ ስጪኝ፡፡” ሲላት “የምን ውሃ? የተሰነጠቀው መሬት ላይ ውሃውን ካፈሰስከው ሲጠማህ የምትጠጣው ነገር እንደማይኖር ነግሬሃለሁ፡፡” አለችው፡፡
“በዚያን ጊዜ አልጠማኝም ነበር፡፡ አሁን ነው የጠማኝ፡፡”
“አሁንማ ምንም ውሃ ጠርሙሳችን ውስጥ የለንም፤በአካባቢውም ምንም ውሃ የለም፡፡”
በጣምም ርቧቸው ነበር፡፡ ከዚያም አንድ መኖሪያ ቤት አይተው “እስኪ ወደዚያ ቤት ሄደን ምግብና ውሃ እንዲሰጡን እንጠይቃቸው፡፡” አሉ፡፡
ቤቱም የአንዲት ሰው በላ ሴት ሲሆን ወደቤቱ ውስጥ ለመዝለቅ ሲሉ የሴትየዋን ሴት ልጅ ከደጃፉ ላይ አገኟት፡፡ እርሷም “እናንተ፣ ምንድነው የምትፈልጉት?” ብላ ስትጠይቃቸው እነርሱም “ስለተጠማንና ስለራበን እባክሽ ውሃ እንኳን ታጠጡናላችሁ?” አሏት፡፡
እርሷም “የለም! ምንም ውሃ የለንም፡፡ እባካችሁ ከዚህ ርቃችሁ ሂዱ፡፡ እናቴ ሰው በላ ናትና እኔ ስለማላድናችሁ ከዚህ ሂዱ፡፡” አለቻቸው፡፡
“ግን እባክሽ ውሃ ስጪኝ፡፡”
“የለም፣ ምንም ውሃ የለኝም፡፡”
ነገር ግን የሰው በላዋ ሴት ልጅ እንጀራእንጀራ ጠፍጣፋና ክብ ሆኖ ከጤፍ ዱቄት የሚሰራ ሲሆን ጤፍ በኢትዮጵያ ደጋማ ስፍራዎች የሚበቅል ሰብል ነው፡፡ እየጋገረች ስለነበረ በሊጡ አናት ላይ ትንሽ ውሃ ነበረ፡፡
“እባክሽ ያንን ስጪንና በጣም ስለጠማን እንጠጣው፡፡” አሏት፡፡
“እሺ፡፡ ውሰዱና ጠጡ፡፡” ብላ ቀድታ ሰጥታቸው ከጠጡ በኋላ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ከቤቱም ከራቁ በኋላ እናትየው ከቤቱ ውስጥ ወጥታ “ልጄ፣ ከማን ጋር ነበረ የምታወሪው?” ስትላት
“ከማንም” ብላ መለሰችላት፡፡
“ከሰዎች ጋር ስታወሪ የሰማሁ መስሎኛል፡፡ የእንጀራውስ ውሃ የት ሄደ?” አለቻት፡፡
ልጅቷም “ሊጡ ውስጥ ነው፡፡” አለቻት፡፡
እናትየውም “ግን ተመልከቺ፡፡ ይህ ስኒ ተጠጥቶበታል፡፡ ከሊጡ ላይ የተወሰነውን ውሃ በስኒው ቀድተሸ ለሰው ሰጥተሻልና እውነቱን ንገሪኝ፡፡” አለቻት፡፡
ልጅቷም “እሺ እንግዲህ፣ አንዲት እናትና ልጇ በጣም ጠምቷቸው ስለነበረ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡” አለቻት፡፡
“ወዴት ነው የሄዱት?”
“የአንበሳውን መንገድ ተከትለው ሄዱ፡፡”
ሰው በላዋም ሴት ሮጣ፣ ሮጣ ብትፈልጋቸውና ዛፍ ላይ ወጥታ ብትመለከትም ልታገኛቸው አልቻለችም፡፡ ከዚያም ወደ ቤት ሮጣ ተመልሳ ልጇን “እየዋሸሺኝ ነው፡፡ እውነቱን ንገሪኝ ካለበለዚያ አንቺን ነው የምበላሽ፡፡” አለቻት፡፡
“እንግዲያው ወደ ከብቶቹ መንገድ ሂጂ፡፡”
አሁንም ልታገኛቸው ስላልቻለች በጣም ተበሳጭታ ተመልሳ መጣች፡፡ “ለምንድነው የምትዋሺው?” እውነቱን ተናገሪ!” ብላ ልጇ ላይ ጮኸችባት፡፡
በመጨረሻም ልጅቷ ትክክለኛውን አቅጣጫ አመላክታ “ሰዎቹ ወደዚያ ነው የሄዱት፡፡” አለቻት፡፡
ሰው በላዋም ሴት ወደዚያ አቅጣጫ ሮጣ፣ሮጣ፣ከሩቅ አየቻቸው፡፡ የልጁ እናት ወደ ኋላዋ ስትመለከት ሰው በላዋን ሴት አየቻት፡፡
“ልጄ ሆይ! ያቺ ሴት ሰው በላዋ ሴት ስለሆነች ምን ማድረግ ነው ያለብን? እያሳደደችን ስለሆነ እንሩጥ፡፡”
“አይሆንም፡፡ ስለማትጎዳን እንጠብቃታለን፡፡”
ከዚያም ሴትየዋ ደረሰችባቸው፡፡ እናም “አድምጡኝ፣ አሁን መምረጥ አለባችሁ፤ ይህንን አርሲ (የበሰለ ጣፋጭ በቆሎ) ልብላ ወይስ ይህንን ክኤረን (የማይጣፍጥ ገብስ) ልብላ?” አለቻቸው፡፡ አርሲ ማለቷ ልጁን ሲሆን ክኤረን ደግሞ እናትየዋን ማለቷ ነበር፡፡
ልጁም ሳይገባው ጣፋጩን በቆሎ አርሲን ብዪ፡፡” ሲላት እናቱም “አይሆንም፣ አርሲውን (ልጄን) ሳይሆን ክኤረንን (እኔን) ብይኝ፡፡” አለቻት፡፡
ከዚያም ሰው በላዋ ሴት ወደ እናትየው ሮጣ ጡቶቿን ስትቆርጣቸው ጡቶቿ እንደ አእዋፍ ወደ ሰማይ በረሩ፡፡ ከዚያም እናትየው ስትሞት ሴትየዋ በልታት ልጇን ተወችው፡፡ ልጁም አምልጦ ብዙ መንገድ ተጓዘ፡፡ ከአንድ መንደርም እንደደረሰ ፍየሎች የሚጠብቁ ልጆች አገኘ፡፡
እርሱም “እናንተ፣አኒናን ታውቋታላችሁ? እህቴ ነች፡፡” አለ፡፡ እነርሱም “እንነግርሃለን፡፡ ነገር ግን በቅድሚያ የጠፋችውን ፍየል አግኝልን፡፡ “ አሉት፡፡
እርሱም የጠፋችውን ፍየል አገኛት፡፡
እነርሱም “ሄደህ ያንን የከብት እረኛ ጠይቅ፡፡” አሉት፡፡
እርሱም “አንተ የከብት እረኛ አኒናን በዚህ መንደር ውስጥ ታውቃታለህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡
እረኛውም “አኒና የት እንዳለች እነግርሃለሁ፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያ ከብቶቼን ሰብስብልኝ፡፡” አለው፡፡ ልጁም ከብቶቹን ከሰበሰበ በኋላ እረኛው “ያ የግመል እረኛ ይነግርሃል፡፡” አለው፡፡
ልጁም ወደ ግመል እረኛው ሄዶ “አንተ የግመል እረኛ አኒና የምትባል በዚህ መንደር የምትኖር ልጅ ታውቃለህ?” ብሎ ሲጠይቀው “በቅድሚያ ግመሌን ወደዚህ አምጣልኝ፡፡” አለው፡፡
ግመሉንም አመጣለት፡፡
“በል አሁን ያንን ገበሬ ጠይቀው፡፡”
ልጁም ገበሬውን “አኒና የምትባል ልጅ ታውቃለህ?” አለው፡፡
“እነግርሃለሁ፤ ነገር ግን መጀመሪያ ማሳዬ ላይ ስራ አግዘኝ፡፡” ልጁም ሙሉ ቀን ስራ ሲሰራለት ውሎ ጀንበሯ ስታዘቀዝቅ ገበሬው የስኳር ዛፉን መታ መታ አድርጎ ጣፋጭ ፈሳሽ እንዲወጣው ካደረገ በኋላ ልጁን “ይህንን ጣፋጭ ሙጫ ብላ፡፡” አለው፡፡
ልጁም ሙጫውን አፉ ውስጥ ሲከት ጥርሶቹ ተጣበቁ፡፡ በዚህም ጊዜ ልጁ “ህምም! ህምምም!” ማለት ጀመረ፡፡
ከዚያም ገበሬው ልጁን ወደራሱ ቤት ወሰደው፡፡ ለካስ ይህ ገበሬ የአኒና ባል ነበርና ሆኖም ልጁን ስለተጠራጠረው ሊነግረው አልፈለገም ነበር፡፡ እናም ሚስቱን “ይህ ልጅ ዛሬ ስራ ሲሰራልኝ ነው የዋለው፡፡ አግኝቸው ስለሆነ መናገር አይችልምና ወስደሽ አሽከርሽ አድርጊው፡፡” አላት፡፡
ልጁም ሴትየዋ እህቱ መሆኗን አላወቀም፤ እሷም ወንድሟ መሆኑን አላወቀችም፡፡ እናም “አይ አንተ ልጅ! በል ወደ ውሃው ጉድጓድ ሄደህ ውሃ በወንፊት ቀድተህ ና፡፡” አለችው፡፡ ሆኖም ውሃውን ሊቀዳ ሲሞክር ውሃው በሙሉ ፈሰሰበት፡፡ ከዚያም መርፌ ከሰጠችው በኋላ ሙቀጫውን አሳይታው
“አሁን እህሉን ውቀጥ፡፡” አለችው፡፡
“እንዴት አድርጌ? በፍፁም አልችልም፡፡”
“በል ውቀጥ!”
ሞከረ፡፡
ከዚያም ሶስተኛውና የማይቻለውን ትዕዛዝ (ምን እንደነበር አላስታውስም) አዘዘችው፡፡ ከዚያ በኋላ የእናቱ ጡቶች የነበሩት ወፎች ወደ መንደሩ ሲበሩ መጥተው እንዲህ እያሉ መዝፈን ጀመሩ፤
“አንተ ዓሊ፣ እህትህ አላወቀችህም፡፡
ማንነትህን ብታውቅ ኖሮ፣
ውሃ የማይዙ እቃዎችን ባልሰጠችህ ነበር፣
መርፌም ሰጥታህ እህሉን ውቀጥ አትልህም ነበር፣
ሶስተኛውንም ነገር አትጠይቅህም ነበር፡፡ (ለምሳሌ በላባ ሥጋ ቁረጥ)”
ከዚያም ሁሉም ሰዎች የወፎቹን ዜማ ሰምተው “በየቀኑ እነዚህ ወፎች ይህንን ልጅ ያናግሩታል፡፡” አሉ፡፡
ለአኒናም “በየቀኑ ወፎች ይህንን ልጅ እንዲህ እያሉ ያናግሩታል፡፡” አሏት፡፡ ይህንን በሰማች ጊዜ አኒና ወደ ወንድሟ ዘንድ ስትሄድ እናታቸው እንደሞተችና ወደ ወፍነት እንደተለወጠች ነገራት፡፡ ባሏንም እንዴት እንደጠየቀውና ባሏም እንዳታለላት ነገራት፡፡ እሷም በባሏ በጣም ተበሳጭታ ስለነበረ ማታ ወደ ቤት ሲመጣ ጉድጓድ ቆፍራ ውስጡ እሳት አኑራ ጉድጓዱን ሸፈነችው፡፡ ባሏም “ይህ ሙቀት ምንድነው?” ብሎ ሲጠይቃት “እንዳይበርደን ብዬ ነው እሳት ያሞቅኩት፡፡” አለችው፡፡
ነገር ግን ባሏ እሳቱ ውስጥ ወድቆ ስለተቃጠለ ባሏን ገድላ ወንድሟን አወቀችው፡፡ ታሪኩም በዚሁ ተጠናቀቀ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|