ልጃገረዷና አንበሣው
በደገን ዓሊ አደም የተተረከ
በአንድ ወቅት ከአንዲት ልጃገረድ ጋር የተጫጨ ሰው ነበር፡፡ ለልጅቷ ቤተሰብም ጥሎሽ ለማድረስ ቀጠሮ ነበረው፡፡ ለጥሎሽ የሚሆኑትን ላሞችና በሬዎች እየነዳ ወደ መንደሩ እየሄደ ሳለ አንዲቷ ላም በአንበሳ ተያዘች፡፡ ላሟም ማጓራት ጀመረች፡፡
ሰውየውም “ላሜን ምንድነው የያዛት?” ብሎ ሲጠይቅ አንበሳው “እውነተኛ ወንድ ነው የያዛት፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
ሰውየውም “ምን?” ካለው በኋላ “አንተ ከእኔ በላይ ወንድ ሆነህ ነው? እንዴት ላሜን ትበላብኛለህ? እንደዚህማ ላሜን በልተህ አልለቅህም!” አለው፡፡
ከዚያም መደባደብ ጀምረው አንበሳው ሲወድቅ ሰውየው እላዩ ላይ ሲወጣበት አንበሳው “ልትጥለኝ የቻልከው አንተ ቀኝ እጅ ስላለህ ነው፡፡ እኔ ግን ቀኝ እጅ ስለሌለኝ እኩል አይደለንምና ቀኝ እጅህን ቆርጠህ እንደገና እንሞካከር፡፡” አለው፡፡
እናም ሰውየው ቀኝ እጁን ቆርጦ እንደገና ሲታገሉ አሁንም ሰውየው አንበሳውን ጣለው፡፡
በዚህን ጊዜ አንበሳው “አሃ! አሁንም ምክንያቱ አንተ ግራ እጅ ስላለህ ነውና ግራ እጅህን ቆርጠህ ይዋጣልን፡፡” አለው፡፡
ሰውየውም ግራ እጁን ቆርጦ እንደገና ሲሞካከሩ በዚህ ጊዜ ሰውየው ተሸንፎ ስለወደቀ አንበሳው በላው፡፡ ከዚያም አንበሳው የሰውየውን ልብስ ለብሶ ከብቶቹን እየነዳ ወደ መንደሩ ሄደ፡፡
የሙሽራዋ ቤተሰቦችም በጭፈራና በእልልታ ይጠብቁ ስለነበረ ከብቶቹን ሲያዩ “አሃ! ሰውየው ጥሎሹን ይዞ መጣ!” በማለት ወደ አንድ ክፍል ውስጥ ይዘውት ገብተው እዚያ ተቀመጠ፡፡ ከዚያም ፋጢማ የተባለቸው ሙሽራይቱ የቤተሰቡ አንድ ልጅ ነበረች፡፡ እርሷም ሙሽራው ወዳለበት ክፍል ገብታ አብረው ቁጭ አሉ፡፡ ምግብ አብስለውም ስጋ ጭምር ወስደው እንደ ሙሽራ ለለበሰው አንበሳ ቢሰጡትም አንበሳው እምቢ አለ፡፡
“ይህ ለእኔ አይገባም፡፡” ሲላቸው ስጋውን ጠብሰው ጣፋጭ ምግብ ቢያዘጋጁለትም አሁንም “እምቢ! ይህ ለእኔ አይገባም፡፡” አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ግራ ስለተጋቡ “ታዲያ ምንድነው የምትፈልገው?” ብለው ሲጠይቁት “እኔ የምፈልገው ያልበሰለ ስጋ ነው፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም “እንግዲያው ያልበሰለ ስጋ ስጡት፡፡” አሉ፡፡ ሙሽራው ለመንደሩ አዲስ በመሆኑ አፍረው ያልበሰለ ስጋ ሰጡት፡፡
የመኝታ ሰዓት ደርሶ ሊተኙ ሲሉም አንበሳው “ይህ አልጋ ለእኔ አይመቸኝም፡፡” አላቸው፡፡ እነርሱም “ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” ሲሉት እርሱም “እባካችሁ አልጋውን ቀይሩልኝ፡፡” አላቸው፡፡ ሚስቱም አልጋውን በርብራብ እንጨት ቀይራ አብረው ሲተኙ የሰውነቱን ፀጉር አየች፡፡ በዚህም ጊዜ “ወይኔ! ፀጉር! ሰውነትህ ፀጉር አለው!” ስትለው እርሱም “አዎ ይህ የእኔ ፀጉር ነው፡፡” አላት፡፡
ከዚያም ከተኛችበት ዘላ ተነስታ ወደ አባቷ በመሄድ በዘፈን እንደዚህ አለች፤
“አባቴ ሆይ፣
ለዱር እንስሳ ነው አሳልፈህ የሰጠኸኝ፣
ይህ የሰው ልጅ አይደለም፣
“የሰውነቱንም ፀጉር አይቸዋለሁ፡፡”
አባትየውም በጣም ተበሳጭቶ “ይህ በፍፁም ሊሆን አይችልምና ተመልሰሽ ወደ ባልሽ ሂጂ፡፡” ብሎ ሲቆጣት እርሷም “እኔ ግን እውነቴን ነው፣ አባባ!” እያለች ስትማፀነው አባቷም “እንግዲያው መልካም! እስኪ እንፈትሸዋለን፡፡ ነገ የመንደሩ ሰው ሁሉ ሳርና ውሃ ፍለጋ መሰማራት አለበት፡፡ ሁሉም ሰው ‘ጊዜው አሁን ነው’ የሚለውን ማስጠንቀቂያ ሲሰማ እኩል ይጮሃል፡፡ ታዲያ ያንቺም ባል ይህንን ጩኸት ካላሰማ እውነትም እንስሳ መሆኑን እንደርስበታለን፡፡ አሁን ግን ይህ አሳፋሪ ነገር ነውና በዚህ ሰዓት ወደልጄ ቤት ገብቼ ማረጋገጥ አልችልም፡፡ እርሱ ግን ‘ጊዜው አሁን ነው’ ካላለ እርምጃ እወስድበታለሁ፡፡” አላት፡፡
ታዲያ በዚህ ጊዜ አንበሳው ልጅቷን ተከትሎ ከቤቱ ውጪ በመሆን ልጅቷና አባቷ የሚነጋገሩትን ነገር ይሰማ ነበር፡፡ ልጅቷ ግን ስላላየችው ቀስ ብላ ወደባሏ ክፍል ተመለሰች፡፡
በማግስቱ በጠዋት ሰዎች ሁሉ ተኝተው ሳለ አንበሳው፤
“የመንደሩ ሰው ለምንድነው የማይንቀሳቀሰው?
የመንደሩ ሰው ለምንድነው የሚተኛው?
ጊዜው አሁን ነው፡፡” እያለ መጮህ ጀመረ፡፡
በዚህ ጊዜ የልጅቷ አባት ስለሰማው “ልጄ እንዴት ደደብ ልጅ ናት! ይህ ሰው እውነተኛ ሰው እንጂ እንስሳ አይደለም፡፡ እየዋሸች ነው!” ብሎ አሰበ፡፡
የመንደሩ ሰው በሙሉ ወደ ሌላ ስፍራ ለመሄድ መንቀሳቀስ ሲጀምር አንበሳው “ ወዴት ነው የምትሄዱት?” ሲላቸው “ወደ ሌላ ቦታ” ብለው መለሱለት፡፡
አንበሳውም “አይሆንም! እኔ ቤተሰቤና ዘመዶቼ ወዳሉበት ወደ ሌላ ቦታ እወስዳቸዋለሁ፡፡” አለ፡፡
እነርሱም “እሺ፡፡ ይህን ማድረግ ትችላለህ፡፡ መብትህም ነውና ወደ ዘመዶችህ ቦታ መሄድ ትችላለህ፡፡” አሉት፡፡
ስለዚህ አንበሳው ሚስቱን “አንቺ ልጅ፣ ሁለታችንም ግመሉን መምራት ስለማንችል አንደኛችን ተሳፍረነው አንደኛችን ደግሞ እየመራነው ስለምንሄድ መሳፈር ነው ወይስ መምራት ነው የምትፈልጊው?” አላት፡፡ እርሷም “አይ! እኔ እመራዋለሁ፡፡ አንተ ከደከመህ ተሳፈር፡፡” አለችው፡፡ እናም አንበሳው ግመሉን ተሳፍሮ እየሄደ ሳለ የግመሉን ሻኛ ስለነከሰው ግመሉ “አህህህ!” ብሎ ጮኸ፡፡
በዚህ ጊዜ ልጅቷ “ግመሉ ምን ሆኖ ነው የሚጮኸው?” ብላ ስትጠይቅ አንበሳውም “የለበስሽውን ጥቁር የአንገት ልብስ ስላልወደደው ደንግጦ ነው፡፡” አላት፡፡
እሷም “እንደሱማ ከሆነ የአንገት ልብሴን አወልቀዋለሁ፡፡” ብላ አወለቀችው፡፡ አንበሳው ግን አሁንም የግመሉን ሻኛ ስለነከሰው ግመሉ “አህህህ!” ብሎ ጮኸ፡፡
አሁንም ልጅቷ “ግመሉ ምን ሆኖ ነው?” አለች፡፡
አንበሳውም “አይ! የእጅሽን አምባርና የአንገት ጌጥሽን አልወደደውም፡፡” አላት፡፡
አሁንም አወለቀች፡፡ አንበሳው እንደገና ግመሉን ነከሰው፡፡
“ግመሉ ምን ነካው?”
“ቀሚስሽን አልወደደውም፡፡”
እሷም ቀሚሷን አውልቃ ራቁቷን ሆነች፡፡ ከዚያም በዚህ ሁኔታ ተጉዘው አንድ ጭር ያለ ቦታ ደረሱ፡፡ ማንም ሰው በስፍራው አልነበረም፡፡
እርሱም “እዚህ ነው የምንኖረው፡፡” አላት፡፡ እርሷም የሶማሌ ዘላን ቤት ከሰራች በኋላ እዚያ ውስጥ አብረው ተኙ፡፡ በዚህ ጊዜ አንበሳው “ሄጄ ዘመዶቼ የት እንዳሉ አይቼ እስክመጣ አንቺ እዚሁ ቆዪ፡፡ እመጣለሁ፡፡ ስመለስ ‘ጎጎቡክ፣ጎግቡክ’ የሚል ድምፅ ከሰማሽ ግመል ይዤ መጥቻለሁ ማለት ነው፡፡ ‘ቻካካ፣ቻካካ’ የሚል ድምፅ ከሆነ ግን ፍየሎች፣ ‘ቾምፕ!ቾምፕ!’ የሚል ከሆነ ደግሞ ላሞችን ይዤ መጥቻለሁ ማለት ነው፡፡” ሲላት እርሷም “እሺ፣ እጠብቅሃለሁ፡፡” ብላው ተነስቶ ሄደ፡፡
ብቻዋን በሆነችበት ጊዜም “ይህ ሰው አይደለም፡፡ የዱር እንስሳ ስለሆነ ምናልባትም ሌሎች የሚበሉኝን የዱር እንስሳት ይዞ ሊመጣ ይሆናል የሄደው፡፡ ከዱር እንስሳት ጋር መኖር ስለማልችል አሁን ምን ማድረግ አለብኝ? ወደ ቤተሰቤ ተመልሼ እንዳልሄድ ስለማያምኑኝ ያፍሩብኛል፡፡” እያለች ማሰብ ጀመረች፡፡
እናም ትንሿን ጣቷን ቆርጣ ሙቀጫ ውስጥ በማኖር ሮጣ ሄደች፡፡ ሮጣ፣ሮጣ፣ሮጣ፣ሮጣ ስታበቃ አንድ ደረቅ ዛፍ ከሃይቅ ወስጥ ቆሞ አየች፡፡ በአንድ ወገን የሃይቁ ውሃ በጣም ጥልቅ ስለነበረ በገመድ ተንጠላጥላ ዛፉ ላይ ወጣች፡፡ እርሷ ዛፉ ላይ ወጥታ ሳለ አንበሳው እባብ፣ ጅብና የመሳሰሉትን የዱር እንስሳት ይዞ መጥቶ ወደ ቤቱ ውስጥ ይዟቸው ገባ፡፡ ነገር ግን በቤቱ ውስጥ ፋጢማን ሳይሆን ጣቷን ብቻ በሙቀጫ ውስጥ አገኙት፡፡
አንበሳውም “ፋጢማ! ፋጢማ!” እያለ ቢጣራም እርሷ ግን እዚያ አልነበረችም፡፡
አንበሳውም በጣም ተበሳጭቶ እንስሳቱ ሁሉ በተሰበሰቡበት በሩን ሲሰብረው ትንሿ የፋጢማ ጣት “ፋጢማ እዚህ የለችም፣ ጠፍታ ሄዳለች፡፡” አለች፡፡
አንበሳውም ጣቷን በላት፡፡
አይጧ (በገሌ) “የት እንደሄደች አውቃለሁ፡፡” አለች፡፡
“አንቺ፣ በገሌ፣ አንቺ ታውቂያለሽ?”
“አዎ፣ የት እንደሄደች አይቻለሁ፡፡ ሃይቁ ውስጥ ካለው ዛፍ ላይ ነች፡፡”
“ልታሳይን ትችያለሽ?”
“አዎ”
ከዚያም ሁሉም እንስሳት አይጥ መሰሏን በገሌን ተከትለዋት ሄዱ፡፡
“አሃ! ተመልከቱ! ፋጢማ እዚያ ዛፍ ላይ ነች፡፡” አለች በገሌ፡፡
አንበሳውም “አሃ! አንቺ ፋጢማ! እባክሽ ነይ ውረጂ፡፡” ሲላት ፋጢማ “አልመጣም፡፡ እናንተ ናችሁ ወደእኔ መምጣት ያለባችሁ፡፡” አለችው፡፡
“ዛፉ ላይ እንዴት መውጣት ይቻላል?”
“ገመዱን ያዙና እኔ ወደላይ እጎትታችኋለሁ፡፡”
“እንግዲያው መጀመሪያ ማን ይውጣ?”
አንበሳው “እኔ ባሏ ስለሆንኩ መጀመሪያ እኔን ትውሰድ፡፡” አለ፡፡
“እንግዲያው ገመዱን ያዝ፡፡”
እናም አንበሳው ገመዱን ይዞ ግማሽ ያህል ወደላይ እንደወጣ ልጅቷ ገመዱን ስትቆርጠው አንበሳው ውሃው ውስጥ ወድቆ ሰምጦ ሞተ፡፡
ሌላው እንስሳም “እርሷ የእኔ ደማሺ ናት፣ የወንድሜ ሚስት፡፡ እኔን ትወስደኛለች፡፡ በእኔ ላይ ገመዱን አትቆርጥም፡፡” አለ፡፡
ነገር ግን አሁንም ገመዱን ቆረጠችው፡፡
አንድ በአንድ እንስሳቱ ዛፉ ላይ ሊወጡ ሲሞክሩ ገመዱን ቆርጣ፣ቆርጣ በመጣል ሁሉም እንስሳት ሃይቁ ውስጥ ሰምጠው ሲሞቱ እርሷ ብቻዋን ቀረች፡፡
ከዚያም አንድ ክንፍ ብቻ ያላትና የተራበች ወፍ መጣች፡፡ ወፏም “አንቺ ልጅ ሆይ፣ እባክሽ ከዛፉ ላይ የምበላው ቴምር ስጪኝ፡፡” ብላ ለመነቻት፡፡
ልጅቷም “አንቺም ለቤተሰቤ ሄደሽ መልዕክት የምታደርሺልኝ ከሆነ ቴምሩን እሰጥሻለሁ፡፡” አለቻት፡፡
ወፏም “እሺ፣ መልዕክቱስ ምንድነው?” ብላ ስትጠይቃት “እንደዚህ በያቸው ‘ልጃችሁ ፋጢማ ከዚያ ዛፍ ላይ ሆና እያለቀሰች ነው፡፡’”
ከዚያም ቴምሩን ሰጥታት ባለ አንድ ክንፏ ወፍ ወደ መንደሩ በመብረር የፋጢማ እናት ቅቤ ስትንጥ አገኘቻት፡፡ እንዲህም እያለች ትዘፍን ጀመረች፤
“አንቺ ቅቤ የምትንጪ ሴት ሆይ፣ ልጅሽ ሃይቁ ውስጥ ካለው ደረቅ ዛፍ ላይ ሆና ኦ፣ኦ፣ብዮ፣ብዮ፣ሆጌ፣ኦ፣ባዮ፣ እያለች በማልቀስ ላይ ነች፡፡ አንቺ ክፉ ሴት ልጅሽ እያለቀሰች አንቺ ምን አይነት ቅቤ ነው የምትንጪው፡፡”
ሴትየዋም “ምን አልሽ?” አለቻት፡፡
ወፏም “እኔ አንድ ክንፍ ብቻ ያለኝና ምንም የማላውቅ ወፍ ነኝ፡፡ ነገር ግን ልጅሽ እርዳታ እየፈለገች አንቺ ምን አይነት ቅቤ ነው የምትንጪው? ነው የምልሽ፡፡” አለቻት፡፡
ሚስትየዋም “ይህቺ ወፍ ምንድነው የምትሰራው?” አለች፡፡
ከዚያም ወፏ ወደ አባትየው ስትሄድ ጫማ ሲሰፋ አገኘችው፡፡ ከዚያም አባትየውን “ልጅህ እዚያ ዛፍ ላይ ሆና ‘ሆጌ ኦ ባዮ’ እያለች ስታለቅስ አንተ ምን ዓይነት መጥፎ ነገር ነው እየሰራህ ያለኸው? ለምን አትረዳትም? እኔ አንድ ክንፍ ብቻ ያለኝና ምንም የማላውቅ ወፍ ነኝና ልጅህን ለምን አትረዳትም?” አለችው፡፡
እርሱም “ይህች ደደብ ወፍ ምንድነው የምትለው?” አለ፡፡
ከዚያም ወፏ ከብቶች ይጠብቅ ወደነበረው የልጅቷ ወንድም ሄዳ “የምን መጥፎ ከብቶችን ነው የምትጠብቀው! እህትህ እርዳታ ትሻለች፡፡ ሃይቁ ውስጥ ካለው ደረቅ ዛፍ ላይ ነው ያለችው፡፡ እኔ ባለ አንድ ክንፍና ምንም የማላውቅ ወፍ ብሆንም እህትህ እንደምትፈልግህ ልነግርህ እወዳለሁ፡፡” አለችው፡፡
ከዚያም ወንድሞቿ፣ አባቷና እናቷ በሙሉ ተሰባስበው “ወፏ ምን ልትነግረን ፈልጋ ነው? እስኪ እዚያ ሃይቅ ውስጥ ያለውን ዛፍ ሄደን እንመልከት፡፡” ብለው ወደ ዛፉ በመሄድ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ሄዱ፡፡ እዚያም እንደደረሱ ብቸኛ ሴት ልጃቸውን አገኙዋት፡፡ እናትየውም “አንድ ሴት ልጄ! ባሏ እንስሳ እንደሆነና ሰው እንዳልሆነ ነግራን ነበር፡፡ ችግር ገጥሟት ይሆናልና ሄጄ ልያት!” እያለች ተጣራች፡፡
ከዚያም ዛፍ ሥር ቆመው “አንቺ ፋጢማ! ነይ ውረጂ!” ብለው ተጣሩ፡፡
ፋጢማም “አልወርድም! ለዱር እንስሳ ሰጥታችሁኛልና በጣም አዝኜባችኋለሁ፡፡ እኔ የሚረዳኝ የለምና እሞታለሁ፡፡ ከዚህ አልወርድም፡፡” አለቻቸው፡፡
እያንዳንዳቸውም “ለምን?” እያሉ ለመኗት፡፡
“አይሆንም! አልወርድም!”
ከዚያም እናትየው “አንቺ ብቸኛ ሴት ልጄ ነሽና እባክሽ ውረጂና እረዳሻለሁ፡፡ ተሳስተናል፡፡” አለቻት፡፡
“አይሆንም፡፡”
በመጨረሻም “ምን ብናደርግ ይሻላል?” ተባባሉ፡፡
ትንሹ ወንድምም “ለፈጣሪ እፀልያለሁ፡፡” አለ፡፡
እንደዚህም እያለ መፀለይ ጀመረ “ፈጣሪ ሆይ፣ ይህ ዛፍ ወድቆ እህቴ መውረድ አለባት፡፡ እናም ትንሿ ጣቷ ብቻ ተቆርጦ ሌላ ጉዳት ሳይደርስባት ትውረድ፡፡”
እንደዚህ እያለ አላህን ሲለምነው ዛፉ ወድቆ ፋጢማ ትንሿን ጣቷን ብቻ አጥታ ወረደች፡፡ ከዚያም ይቅርታ አድርጋላቸው ይዘዋት ወደ መንደሩ ሄዱ፡፡
ከመንደሩም እንደደረሱ እናትየው “ፋጢማ፣ እባክሽ ቅቤውን በመናጥ እርጂኝ፡፡” አለቻት፡፡
“የት ነው የምንጠው? ቤት ውስጥ?”
“አይሆንም! ይህማ አይቻልም፡፡”
“የከብቶቹ ቤት ውስጥ?”
“እዚያም አይቻልም፡፡ ሌላ የት ይሻልሻል?”
“ከቤቱ ጣሪያ ላይ ይሻለኛል፡፡ እዚያስ ይቻላል?”
“አዎ”
“የምፈልገው ብቸኛ ቦታ እዚያ ነው፡፡”
“እሺ፣ እዚያ ላይ ከፈለግሽ ሂጂ፡፡”
ስለዚህ ልጅቷ ወተቱንና መናጫውን ይዛ ጣሪያው ላይ ወጣች፡፡ ጣሪያው ላይ ሆና ወተቱን እየናጠች ሳለ ሃይለኛ ንፋስ መጥቶ እርሷንና መናጫውን ይዟቸው ወደ ሰማይ ወጣ፡፡ አባቷና እናቷ ሲያዩ እናትየው “ንፋሱ ሆይ፣ልጅቷን ወስደህ የወተቱን እቃ መልስልኝ፡፡” እያለች ጮኸች፡፡
አባትየው ደግሞ “ንፋስ ሆይ! የወተት እቃውን ወስደህ ልጅቷን መልስልኝ” እያለ ጮኸ፡፡
ንፋሱም የወተት እቃውን መልሶ ልጅቷን ወስዶ ከጫካ መሃል ላይ ጣላት፡፡ እርሷም ወደ ሁለት ጠማማ ዱላዎች ተለወጠች፡፡ አንድ የግመል እረኛ ዱላዎቹን አገኛቸው፡፡ እርሱም “አሃ! ጥሩ ዱላዎች አገኘሁ” ብሎ አንደኛውን አንስቶ ግመሉን ሊመታበት ሲሞክር ግመሉን እንደመታው ዱላው ግመሉ ውስጥ ገባ፡፡ ከዚያም ሌላኛውን ዱላ አንስቶ ግመሉን ሊመታበት ሲሞክር አሁንም ዱላው ወዲያው ግመሉ ውስጥ ገባ፡፡
እረኛውም ግመሉን ወደ መንደሩ እየነዳ ወስዶ ለአባቱ ሁለት የሚያማምሩ ዱላዎች አግኝቶ እንደነበርና ግመሉን በዱላዎቹ ሲመታው ዱላዎቹ አሁን ግመሉ ውስጥ እንዳሉ ነገረው፡፡
አባትየውም “እውነትህን ነው?” ብሎ ሲጠይቀው “አዎ” በማለት መለሰ፡፡
“ከዋሸህ ግን እገድልሃለሁ፡፡”
“እሺ ግደለኝ፡፡”
አባትየውም “ዱላዎቹን አገኛቸዋለሁ፡፡” ብሎ የግመሉን አንገት ቆርጦ ሲከፍተው ዱላዎቹ ግመሉ ሰውነት ውስጥ ወዲያ ወዲህ በመዝለል ከሰውየው ስለተሰወሩ ሊያገኛቸው ባለመቻሉ በብስጭት አንድና ብቸኛ የሆነውን ልጁን ገደለው፡፡
ወዲያው ሁለቱ ዱላዎች ከግመሉ ውስጥ በርረው በመውጣት ዛፍ ላይ ወጥተው “ምንም ልጅ እና ምንም ወተት እንዳይኖርህ አደረኩ፡፡ (ወተት ያለው ግመል እርሱ ብቻ ነበር)፡፡ ምንም ወተት፣ምንም ልጅ እንዳይኖርህ አደረኩ፡፡” አሉ፡፡
የታሪኩም መጨረሻ ይኸው ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|