ሰው በላዋ ሴት
በደገን ዓሊ አደም የተተረከ
በአንድ መንደር የምትኖር አንዲት ሰው በላ ሴት ነበረች፡፡ የመንደሯ ሰዎችም መጥታ እንዳትበላቸው ሁልጊዜ ይፈሯት ነበር፡፡
ታዲያ የአንድ ቤተሰብ አባወራ ለጉዞ ሲዘጋጅ ሚስቱን “እባክሽ ማታ ማታ በሩን ክፍቱን አትተይው፡፡ አንዲት ሰዎችን የምትበላ ሴት በዚህ መንደር ስለምትገኝ ተጠንቀቂ፡፡” ብሏት ሄደ፡፡
በመሸ ጊዜም ሰው በላዋ ሴት መጥታ የቤቱን በር አንኳኳች፡፡ የሰውየው ሚስት ብቻዋን ነበረች፡፡ እናም “ማነው?” ብላ ስትጠይቅ ሰው በላዋ ሴት ባልዋ እንደሆነች ስትናገር ሴትየዋ ሳታውቅ በሩን ከፈተችው፡፡ ወዲያው ሰው በላዋ ሴትዮ ወደቤቱ ውስጥ በመግባት ሴትየዋን በልታ የእርሷን ቀሚስ ለበሰች፡፡
ከዚያም የሴትየዋ ባል ከሄደበት ተመልሶ መጣ፡፡ ሄዶ የነበረውም (ዘላን በመሆኑ) ለከብቶቹ ሣርና ውሃ ፍለጋ ነበር፡፡ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆንም አንድ ጥሩ ቦታ ስላገኙ ወደዚህ ወዳገኙትና መርጠው ወደመጡት ቦታ መኖሪያቸውን ለመቀየር ፈልገው ነበር፡፡ ስለዚህ ሁሉም የመንደሩ ቤተሰቦች እቃቸውን ጭነው ወደ አዲሱ ቦታ ለመሄድ ተዘጋጁ፡፡
ሰውየውም ወደቤቱ ሲገባ ቤቱ ውስጥ ያገኛት ሴት የሚስቱን ቀሚስ ለብሳ ስላያት ሚስቱ መስላው እሷም ለመሄድ እንድትዘጋጅ ነገራት፡፡ ሚስቱ ነፍሰ ጡር ስለነበረች ሰው በላዋ ሴት የሟቹን ሚስትና ልጅ አስከሬኖች ጉድጓድ ውስጥ ከቀበረቻቸው በኋላ እርሷ ራሷ እርጉዝ ለመምሰል ሰው ሰራሽ እርግዝና ፈጠረች፡፡
ወዲያው ታዲያ ያላቸውን እቃ በሙሉ ካዘጋጀች በኋላ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ቤተሰቡም አንድ ውሻ፣ አንዲት ዶሮ፣ አንዲት ድመት፣ አንዲት ግመል፣ አንዲት ላም፣ አንድ ፍየልና አንድ በግ ነበራቸው፡፡ ግመሏንም ለማለብ ሲሞክሩ ግመሏ ሸሸች፡፡ ሁሉም እንስሳት ጋ ሲጠጉ እንስሳቱ ይሸሽዋቸው ስለጀመሩ ሰውየው ግራ ገባው፡፡
በመጨረሻ ግን ሴትየዋ ሚስቱ ሳትሆን ሰው በላዋ ሴት እንደሆነች አወቀ፡፡ ሴትየዋንም ከገደላት በኋላ በእንስሳቱ አኳኋን ነገሩን ስለተረዳው የሚስቱንና የልጁን አስከሬን ፈልጎ አገኘ፡፡ ታሪኩም ይኸው ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|