ሌላ የቀበሮ ታሪክ
በአይሻ አዋደም የተተረከ
አጭበርባሪዋ ቀበሮ የአንበሳው እህት ልጅ ነበረች፡፡ አንበሳው፣ ቀበሮዋ፣ ሁሙ ሁሙ ወፍ (ጥንብ አንሳ)፣መንሽ፣መጥረቢያ፣ የቡና ፍሬ ገለባ፣ ቅቤ፣ የበቆሎ ገለባና ጅብ ሁሉም በአንድነት ይኖሩ ነበር፡፡ የሚጠብቋቸውና የሚጠቀሙባቸው ብዙ ከብቶችም ነበሯቸው፡፡ አጭበርባሪዋ ቀበሮ የዚህ ቤተሰብ አባል ስትሆን አንበሳም ንጉሳቸው ነበር፡፡ አንበሳውም የእህቱን ልጅ ቀበሮዋንና ጅቧን ከብቶች ይጠብቁ ዘንድ ላካቸው፡፡ እነርሱም ከብቶቹን ወደ ግጦሽ ይዘው አሰማሩ፡፡
ጀንበሯም ስትጠልቅ ቀበሮዋ “እባክሽ ርቦናል፤ ሆኖም የራሳችንን ከብቶች መብላት የለብንም፣ አለበለዚያ አንበሳው ይደበድበናል፡፡ ይልቁንም የሌላ ሰው የሆነች አንዲት ላም ለመያዝ እንሞክር፡፡” ብላ ጅቧን አማከረቻት፡፡
ጅቧም “እሺ” ብላ የሌሎች እረኞችን ላም ልትገድል ስትሞክር እረኞቹ አይተዋት ተኩሰው ገደሏት፡፡
ጀንበሯ ከጠለቀች በኋላም ቀበሮዋ ከብቶቹን በሙሉ ብቻዋን እየነዳች ወደ መንደሩ በመመለስ አንበሳውን “አያ አጎቴ አንበሳ ሆይ፣ ከብቶቹን በሙሉ ብቻዬን ሙሉ ቀን ስጠብቅ ዋልኩ፡፡ ያቺ ጅል ጅብ የሌሎች እረኞችን ላም ገድላ ልትበላ ስሞክር ስለገደሏት ሙሉ ቀን ብቻዬን ነው የዋልኩት፡፡” አለችው፡፡
አንበሳውም “አይይ! ታዲያ ነገ ከማን ጋር መሄድ ትፈልጊያለሽ?” አላት፡፡
እሷም “ከሁሙ ሁሙ ወፍ ጋር” አለች፡፡
አንበሳውም “እሺ” ብሎ በማግስቱ ጠዋት ቀበሮዋና ሁሙ ሁሙ ወፏ ከብቶቹን ይዘው ወደ ግጦሽ አሰማሩ፡፡ ቀበሮዋም ገና በጠዋቱ “እባክሽ ሁሙ ሁሙ ወፍ ሆይ፣ አንድ የሚበላ ነገር ልታገኝልን ትችያለሽ? አንቺ ካልቻልሽ ግን እኔ አገኛለሁ፡፡” አለቻት፡፡
ሁሙ ሁሙ ወፏም ምግብ ፍለጋ መሄድ ስላልፈለገች ቀበሮዋ ቀኑን ሙሉ የሚበላ ነገር ፍለጋ ስትሯሯጥ ዋለች፡፡ በመጨረሻም ጀንበር ስትጠልቅ ቀበሮዋ ወደ መንደሩ መመለስ ስለነበረባት “አንቺ ሁሙ ሁሙ፣ እኔ ላገኝ የቻልኩት ድንጋይና ትንሽ ሾርባ ስለሆነ ይህንኑ ለመዋጥ ሞክሪ፡፡” አለቻት፡፡
በዚህ ጊዜ ሁሙ ሁሙ ወፏ አፏን ከፍታ ድንጋዩን ለመዋጥ ስትሞክር ድንጋዩ ጉሮሮዋ ውስጥ ተሰነቀረ፡፡
ሁሙ ሁሙ ወፏም መናገር የቻለችው “ሁሙ፣ሁሙ” የሚለውን ቃል ብቻ ነበር፡፡
ከዚያም ወደ መንደሩ ሲመለሱ ቀበሮዋ አንበሳውን “ተመልከት፣ ይህቺ ደደብ ወፍ በጠዋት ተነስታ ሙሉ ቀን ለራስዋ ምግብ ስትፈልግ ውላ አሁን ስትመለስ በጣም ጠግባ ስለመጣች ድምጿ ተዘግቶ ጉሮሮዋ ተደፍኗል፡፡ እኔ ግን ከብቶቹን ብቻዬን ሙሉ ቀን ስጠበቅ ዋልኩ፡፡” አለችው፡፡
አንበሳውም ወፏን “ለምን እንደዚህ አደረግሽ?” ብሎ ሲጠይቃት እሷም “ሁሙ ሁሙ” ብላ መለሰችለት፡፡
በዚህ የተበሳጨው አንበሳ “አንቺ ደደብ!” ብሎ ወፏን ከገደላት በኋላ “አሁን አንቺ ቀበሮ፣ ነገ ማን አብሮሽ እንዲሄድ ትፈልጊያለሽ?” አላት፡፡
እሷም “አብሮኝ እንዲሄድ የምፈልገው መንሽ ነው፡፡” አለችው፡፡ በዚህም ተስማምተው በማግስቱ ጠዋት ቀበሮዋና መንሹ አብረው ከብቶቹን ወደ መስክ አሰማሩ፡፡
ሙሉ ቀን አብረው ሲጠብቁ ቀበሮዋም መንሹን “እባክህ አንተ መንሽ ሆይ፣ እነዚህ ሰዎች ለከብቶች አጥር የሚሆን እሾሃማ ቅርንጫፎቹን ሙሉ ቀን ሲቆርጡ ነው የዋሉት፡፡ ተመልከት! ሰዎቹ አጎቶችህ ስለሆኑ እባክህ ሄደህ እርዳቸው፡፡” አለችው፡፡
እርሱም “አዎ፣ እሺ” ብሎ ሰዎቹን ሊረዳ ሄደ፡፡ እነርሱም ወዲያው አንስተውት ስለወደዱት እየተጠቀሙበት ሳለ መንሹ ተሰብሮ ሞተ፡፡ ከዚያም ቀበሮዋ ከብቶቹን እየነዳች ወደ መንደሩ በመመለስ አንበሳውን “ያ ደደብ መንሽ ለከብቶቻቸው አጥር ወደሚሰሩ ዘመዶቹ ሄዶ ‘እገዛዬን ከፈለጋችሁ ተጠቀሙብኝ’ ሲላቸው እነርሱም እየተጠቀሙበት ሳለ በመሰበሩ ከብቶቹን ሙሉ ቀን ብቻዬን ስጠብቅ፣ ስጠብቅ ዋልኩ፡፡” አለችው፡፡
አንበሳውም “ታዲያ ነገ ጠዋት አብሮሽ ማን እንዲሄድ ትፈልጊያለሽ?” አላት፡፡
እሷም “የቡናው ገለባ” ብላው በማግስቱ ከቡናው ገለባ ጋር አብራ ስትጠብቅ ውላ ከሰዓት በኋላ ቀበሮዋ ወደ ሰዎቹ በመጠቆም “እነዚያን ምስኪን ሰዎች እንዴት እንደሞቃቸውና እንደተጠሙ ተመልከት! የሚጠጡት ነገር ይፈልጋሉና የቡና ገለባ የቡናን ያህል ስለሚጠቅማቸው ልትረዳቸው ትችላለህ?” አለችው፡፡ የቡናውም ገለባ “እሺ” ብሎ ወደ ሰዎቹ ሄደ፡፡
ሰዎቹም “አሃ! እድለኛ ነን፡፡ የቡና ገለባ አግኝተናልና ውሃ አፍልተን እንጠቀምበት፡፡” ተባብለው የቡናውን ገለባ ቆልተው ከወቀጡት በኋላ እንደ ቡና አፍልተው ጠጡት፡፡
ቀበሮዋም ወደ ቤት ተመልሳ አንበሳውን “አይይ! ያ ደደብ የቡና ገለባ ወደ ዘመዶቹ ሄዶ አፍልተው ጠጡት፡፡” አለችው፡፡
አንበሳውም “ታዲያ ነገ ማን አብሮሽ እንዲሄድ ትፈልጊያለሽ?” ብሎ ሲጠይቃት “ቅቤው አብሮኝ ሊሄድ ይችላል፡፡” አለችው፡፡
በዚህም ተስማምተው ቅቤውና ቀበሮዋ ወደ መስኩ ሲሄዱ ቀበሮዋ ቅቤውን “አንተ እዚያ ትልቅ ቋጥኝ ላይ ተቀመጥ፡፡ ሥራውን እኔ እሰራለሁ፡፡” አለችው፡፡
ቋጥኙ ሙሉ ለሙሉ ፀሃይ ላይ ስለዋለ በጣም ግሎ ነበርና ቅቤው ቀና እላዩ ላይ ሲቀመጥ ቀልጦ ወደ ምንምነት ተቀየረ፡፡ ቀበሮዋም ወደቤት ስትመለስ አንበሳውን “ሙሉ ቀን ብቻዬን ስጠብቅ፣ ስጠብቅ ነው የዋልኩት፡፡ ምክንያቱም ያ ደደብ ቅቤ የጋለ ቋጥኝ ላይ ተቀምጦ ቀለጠ፡፡” አለችው፡፡
አንበሳውም “አይይ! ታዲያ ነገ ጠዋት ማን አብሮሽ እንዲሄድ ትፈልጊያለሽ?” አላት፡፡
“የበቆሎ ገለባ” አለችው፡፡
የበቆሎውም ገለባ ከቀበሮዋ ጋራ ሄደ፡፡ ወደቤት መመለሻቸው ጊዜም ሲደርስ ቀበሮዋ ገለባውን “ሁላችንም ሞቆን ስለቆሸሽን ወደ ወንዙ ሄደን እንዋኝ፡፡” አለችው፡፡
ገለባውም “እሺ” ብሎ ለመዋኘት ሲሞክር ውሃው ውስጥ በመደበላለቁ ድራሹ ጠፋ፡፡
ስለዚህ ቀበሮዋ ወደ አንበሳው ሄዳ “ያ ደደብ ገለባ ወንዙ ውስጥ እዋኛለሁ ብሎ ደብዛው ጠፋ፡፡” አለችው፡፡
“ታዲያ ነገ ከአንቺ ጋር ለመሄድ የቀረው ማነው?” አላት፡፡ ቀበሮዋም “ማንም የለም፡፡ አንተ ራስህ አብረኸኝ መሄድ አለብህ፡፡” አለችው፡፡ አንበሳውም “እሺ” ብሏት አብረው ሄዱ፡፡
ከዚያም ቀበሮዋ ትልቅ ጉድጓድ ቆፍራ ውስጡ እሳት በማቀጣጠል ላዩን ሸፍና አንበሳውን “አጎቴ አንበሳ ሆይ፣ አንተ እዚህ ተቀመጥ፤ ከብቶቹን መጠበቁን ለእኔ ተወው፡፡” አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው ሲቀመጥ ጉድጓዱ ውስጥ ወድቆ ሞተ፡፡ እናም ሁሉም ስላለቁ ቀበሮዋ ብቻዋን ከብቶቹን ይዛ ቀረች፡፡ ሰዎችም ከብቶቹ በሙሉ የቀበሮ መሆናቸውን ሲመለከቱ “እንዝረፋት! ብቸኛና ማንም የሚረዳት የለም፡፡” ተባብለው ሊዘርፏት መጡ፡፡
ከዚያም “እዚህ ቤት ሰው አለ?” ብለው ሲጣሩ ቀበሮዋ “የለም! እናንተ እነማን ናችሁ?” አለቻቸው፡፡ በዚህ ጊዜ አካባቢውን በሩጫ እየዞረች ብዙ ለመምሰል ሞከረች፡፡ እንዲህም የሚል ዘፈን መዝፈን ጀመረች፡፡ “ቀበሮዋ ዴያ ዓሊ ሆይ! ሰዎቹ መምጣቴን አይተው ሸሹ፡፡”
ሰዎቹም ለሁለተኛ ጊዜ ተመልሰው ሲመጡ ከቀበሮዋ በስተቀር አንበሳ፣ጅብ፣ ወይም ሌላ ነገር አልነበረም፡፡
ስለዚህ “ለምንድነው የምንፈራው? ቀበሮዋ እንደው ብቻዋን ነች፡፡ ሄደን ከብቶቹን በሙሉ እንዝረፍ፡፡” ተባብለው ከዚህም ከዚያም ተጠራርተው ከብቶቹን በመዝረፍ ሮጠው ሄዱ፡፡ ቀበሮዋም ሰዎቹ ከብቶቹን በሙሉ መዝረፋቸውን ስታይ ጥቂት አስባ ብዙ ነገሮች በመሰብሰብና ሰውነቷ ላይ በማሰር ድምጽ ማውጣት ቻለች፡፡ ከዚያም ስትሮጥ ሰውነቷ ላይ ያሰረቻቸው ቁሣቁሶች ቼላሉም፣ቼላሉም፣ቼላሉም የሚል የፈረስ አይነት ድምፅ ያሰሙ ጀመር፡፡ ኮላሉም፣ኮላሉም፣ቹም፣ኮላሉም፣ኮላሉም ቹም (እያለ ተራኪው የፈረስ ኮቴ አይነት ድምፅ ያወጣል፡፡)
በዚህ ጊዜ ቀበሮዋ “አንተ አሊ! አንተ ኡመር! ፈረስህ ወደ እኔ ፈረስ በጣም ስለቀረበ ፈረሴ እግሩን የሚያሳርፍበት ቦታ እንኳን የለውም፡፡ ወደዚያ፣ወደዚያ፣ ወደዚያ ተመለስ!” እያለች መጮህ ጀመረች፡፡ ድምፁም ኮላሉም፣ኮላሉም፣ፕስት፣ኮላሉም፣ኮላሉም ፕስት እያለ ቀጠለ፡፡
ነገር ግን ሰዎቹ ሲመለከቱ ቀበሮዋ ብቻዋን መሆኗን ስላዩ ተመልሰው መጥተው የቀራትን ንብረት በሙሉ ወሰዱባት፡፡
ስለዚህ ይህ ታሪክ የሚያሳየው አንድ ሰው ብቻውን መኖር እንደማይችልና ሁሉንም ለእኔ ብሎ ወንድሞቹንና እህቶቹን ከገደለ ብቸኛ እንደሚሆን ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|