ዲያ ዓሊ፣ አጭበርባሪዋ ቀበሮ
በአይሻ አዋደም የተተረከ
በአንድ ወቅት ዴያ ዓሊ የተባለችው አጭበርባሪ ቀበሮ በአንድ መንደር ተገኝታ ሰዎች ሲያለቅሱ ስትመለከት “ምን ሆናችሁ ነው?” ብላ ጠየቀቻቸው፡፡
እነርሱም “አንድ ሰው በጠና ታሞ ሊሞትብን ነው፡፡ ለዚህ ነው የምናለቅሰው፡፡” አሏት፡፡
ዴያ ዓሊም “ላድነው ብሞክር ምክሬን ትሰማላችሁ?” አለቻቸው፡፡ እነርሱም “እንዴታ!” ሲሏት ዴያ ዓሊም “አሁን ግመሎቻችሁንና ከብቶቻችሁን አርዳችሁ ስጋቸውን ከቆረጣችሁ በኋላ ወደ ቤት ውስጥ ይዛችሁ ኑ፡፡ ከእኔና ከበሽተኛው ሰው በስተቀርም ሌላ ማንም ሰው በክፍሉ ውስጥ መገኘት የለበትም፡፡ እንደማድነውም እርግጠኛ ነኝ፡፡” አለቻቸው፡፡
በተባሉትም መሠረት “እሺ” ብለው ብዙ ስጋ ወደ ቤቱ ውስጥ ካስገቡ በኋላ ቀበሮዋ (ዴያ አሊ) እስከምታድነው ድረስ ውጪ ሆነው ይጠባበቁ ጀመር፡፡ ሆኖም ሰውየው ወዲያው ቢሞትም ሰዎቹ “እንዴት ነው?” እያሉ መጠየቃቸውን ቀጠሉ፡፡
እሷም “ኧረ እሱ እየተሻለው ነው፡፡ ተጨማሪ ስጋ አምጡ፡፡ ብዙ ሥጋ!” አለቻቸው፡፡
እነርሱም ሥጋ ማምጣታቸውን ቀጠሉ፡፡ እሷም ቤቱን ዘግታ ዝንቦችን በደንበጃን ከሰበሰበች በኋላ ሌሊቱን ሙሉ ከድና አቆየችው፡፡ በጠዋትም ተነስታ ደንበጃኑን ስትከፍተው ዝንቦቹ በከፍተኛ ድምፅ ወጥተው መብረር ጀመሩ፡፡
ውጪ በመጠባበቅ ላይ ያሉት ሰዎች “ምን እየሆነ ነው?” ብለው ሲጠይቋት “ኧረ በሽተኛው ‘አድሃን’ (ፀሎት) ለማድረስ እየሞከረ ነው፡፡” አለቻቸው፡፡
እነርሱም “አሃ! በጣም ጥሩ!” አሉ፡፡
በዚህ ዓይነት ቀበሮዋ ዝንቦቹን ከደንበጃኑ በለቀቀቻቸው ጊዜ ሰዎቹ ታማሚው እየፀለየ ይመስላቸው ጀመር፡፡ በዚህ ሁኔታ ሥጋውን በሙሉ በልታ እስክትጨርስ ድረስ ቆየች፡፡
ሥጋውንም በልታ በጨረሰች ጊዜ የሟቹን አስከሬን ሸፍና “አሁን ስለተኛ ለተወሰነ ጊዜ እንዳትነኩት፡፡ ሲነቃ ይሻለዋል፡፡ በሉ ደህና ሁኑ፡፡” ብላ ሄደች፡፡
ከቆይታ በኋላ ልብሱን ሲገልጡት ሰውየው መሞቱንና ቀበሮዋ ስትዋሻቸው መቆየቷን ተረዱ፡፡
“አይይ! እሷንማ ፈልገን መያዝ አለብን!” ብለው ፈረሶቻቸውን ጭነው አባረው ከያዟት በኋላ ከአንድ ዛፍ ላይ በገመድ አስረዋት ሲያበቁ “አሁን ውሃ አፍልተን የፈላው ውሃ ውስጥ ጨምረን እንገድላታለን፡፡” ብለው ወደ መንደራቸው ውሃ ሊያፈሉ ሄዱ፡፡
ውሃውን ሊያፈሉ በሄዱም ጊዜ አንድ ጅብ በቀበሮዋ አጠገብ ሲያልፍ “አንቺ ቀበሮ ምን ሆነሽ ነው የታሰርሽው?” ብሎ ጠየቃት፡፡ እሷም “አይ አጎቴ ካልጋበዝኩሽ ብሎ ብዙ ስጋ ሊያመጣልኝ ሄዶ ነው፡፡ እናም ‘የትም እንዳትሄጂ እንዳትንቀሳቀሺ ያለሽበትንም ቦታ በቀላሉ አውቀን ብዙ ስጋ እናመጣልሽ ዘንድ ነው ከዚህ ዛፍ ላይ ያሰርንሽ፡፡’ ብሎኝ ነው፡፡” አለችው፡፡
አያ ጅቦም “እኔን ልትለውጪኝ ትችያለሽ?” አላት፡፡ “ስጋውን መብላት እፈልጋለሁ፡፡” ብሎም ተማፀናት፡፡
ቀበሮዋም ፈጠን ብላ “እሺ! ስጋውን መብላት ከፈለክ እኔን ፍታኝና በእኔ ምትክ አንተን አስርሃለሁ፡፡” አለችው፡፡
እሱም በዚህ ተስማምቶ በቀበሮዋ ምትክ ታሰረ፡፡
ከዚያም ቀበሮዋ በአካባቢው ካለ አንድ ዛፍ ስር ተደብቃ ስትመለከት ሰዎቹ በአንድ ትልቅ እንስራ የፈላ ውሃ ይዘው ሲመጡ ጅቡ “አሃ! ስጋ ይዘውልኝ እየመጡ ነው፡፡” እያለ በጣም ይደሰት ጀመር፡፡
ሆኖም ሰዎቹ ወደስፍራው በተቃረቡ ጊዜ ጅቡን ሳያስተውሉ አንስተው የፈላው ውሃ ውስጥ ጨመሩት፡፡
ጅቡም “እባክሽ አንቺ ቀበሮ! እርጂኝ!” እያለ መጮህ ጀመረ፡፡ እሷም “እኔ ልረዳህ አልችልም፡፡ ምናልባት እንደ ግመል ለመወዛወዝ ብትሞክር ይሻልህ ይሆናል፡፡” ስትለው በመወዛወዙ ቆዳው በጣም ቀላ፡፡
ታሪኩም ይኸው ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|