ጭንቅላቱ
በፕሮፌሰር አህመድ መሃመድ አሊ የተተረከ
የአንዲት መልካም ሴት ባል የነበረ አንድ ሰው ነበር፡፡ ሴትየዋም በጣም ታማኝና ጠንካራ ሠራተኛ የነበረች ሲሆን ሁሉንም ነገር በጥሩ ሁኔታ ታከናውን ነበር፡፡ ሆኖም ምስጋና ያልነበረው ባሏ ከፈታት በኋላ ሌላ ሴት ያገባል፡፡ ሁለተኛዋ ሚስት ለተወሰነ ጊዜ ሳትወልድ ብትቆይም ከጊዜ በኋላ በማርገዟ ሰውየው በደስታና በጉጉት ቆይቶ በመጨረሻ ሚስቱ ጭንቅላት ብቻ ወለደች፡፡ ጭንቅላቱም መመገብ፣ መጠጣትና ሁሉንም ነገር ማድረግ ቢችልም ሊያስወግዱት ወስነው በከረጢት ውስጥ ካደረጉት በኋላ በመንገድ ላይ ጣሉት፡፡
ጭንቅላቱ ግን በከረጢቱ ውስጥ እየዘለለ “እባካችሁ ውሰዱኝ!” እያለ ይጮህ ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎች ተሰባስበው ከረጢቱን በማንሳት ወደ ከተማው እየወሰዱት “ምን ልናደርግልህ እንችላለን? ብለው ጠየቁት፡፡
ጭንቅላቱም “በአቅራቢያው ወደሚገኘው አንድ ሻይ ቤት ወስዳችሁ ብቻ እዚያ አስቀምጡኝ፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም እንደተባሉት አደረጉ፡፡
ጭንቅላቱም ባለ ሻይ ቤቱን “ስማ! ሃብታም መሆን ትፈልጋለህ?” አለው፡፡ ባለሻይ ቤቱም “አዎ” አለው፡፡
“እንግዲያውስ እኔን ልትንከባከበኝ ይገባል፡፡”
“እሺ፣ ግን……….”
“ሌላ ምንም እንዳትጠይቀኝ፡፡”
በዚህ ጊዜ ነጋዴው እየመገበው ይንከባከበው ጀመር፡፡ ጭንቅላቱም ነጋዴውን ብዙ ከብቶች ገድሎ ብዙ ጨርቆችንና ሌሎች እቃዎችን እንዲያመጣ አዘዘው፡፡ ከዚህ በኋላ ሰዎች እዚህ እየመጡ እቃዎቹን ሁሉ መግዛት ስለጀመሩ ሰውየው በጣም ሃብታም ሆነ፡፡
በዚያ አካባቢ አንዲት ሴት ልጅ ያለችው ንጉስ ወይም አገረ ገዢ ነበር፡፡ ልጅቷም እድሜዋ ለጋብቻ ሲደርስ ንጉሱ “ ልጄን የምድረው የምፈልገውን ነገር ሁሉ ለሚሰጠኝ ሰው ነው፡፡” አለ፡፡
ብዙ ሰዎችም ቅዳሜ፣ ቅዳሜ፣ ስጦታቸውን እየያዙ ወደ ንጉሱ ይሄዱ ጀመር፡፡
ንጉሱም “ምን ይዘህ እንደመጣህ አሳየኝ፡፡” እያለ እያንዳንዱን ሰው በመጠየቅ “ይህንን አልፈልግም፣ ይህንን ወይም ያንን አምጣ፡፡” እያለ የማይቻል ነገር ይጠይቃቸው ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ጭንቅላቱ ጓደኛውን ባለ ሻይ ቤት “ወደ ንጉሱ ሄደህ ልጁን ይድርልህ ዘንድ ምን እንደሚፈልግ ጠይቀው፡፡” አለው፡፡
ነጋዴውም በዚህ ተስማምቶ በመሄድ ንጉሱን ሲጠይቀው ንጉሱም “እኔ የምፈልገው ግመል ነው፡፡” በማለት የግመሉን አይነት በመዘርዘር “ግመሉ ከፊቴ ቆሞ ሰላምታ ሊሰጠኝና በቋንቋዬ ሊያናግረኝ ይገባል፡፡” አለ፡፡
ነጋዴውም ወደ ጭንቅላቱ ተመልሶ ይህንኑ ነገረው፡፡ ጭንቅላቱም “እንደዚያ ነው ያለው?” ሲለው ነጋዴውም “አዎ” አለው፡፡
ጭንቅላቱም “እንግዲያው የሚያወራውን ግመል ለንጉሱ እናመጣለታለን፡፡ እንደዚህ ወደሚባል ቦታ ሄደህ እንደዚህ አይነት ወንድ ግመል ገዝተህ ና፡፡” ብሎ ነጋዴውን አዘዘው፡፡
ነጋዴውም ጭንቅላቱ ባዘዘው መሠረት ወደተባለው ቦታ ሄዶ የተባለውን ዓይነት ግመል ገዝቶ ከመጣ በኋላ ብዙ ሰዎች በተሰባሰቡበት ሁኔታ ግመሉን ለንጉሱ ሲያደርስ ግመሉ ንጉሱን እጅ ከነሳ በኋላ ንጉሱ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ማድረግ ጀመረ፡፡ ንጉሱም በሁኔታው በጣም ተገረመ፡፡
ከዚያም “ልጄን መጥተህ የምታገባት መቼ ነው?” ብሎ ነጋዴውን ጠየቀው፡፡ ነጋዴውም “ነገ” ብሎ ከመለሰለት በኋላ ወደ ጭንቅላቱ ሮጦ በመመለስ “ሁሉ ነገር ዝግጁ ነው፡፡ ምንድነው ማድረግ ያለብን?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ጭንቅላቱም “እኔን ይዘኸኝ ሂድና እኔ ላግባት፡፡” አለው፡፡
ነጋዴውም በዚህ ተስማምቶ ይዞት ሄደ፡፡
ንጉሱም ትልቅ ድግስ ደግሶ ሰዎች ሁሉ ተጠሩ፡፡ “ልጄን ሊያገባ የሚመጣው ሰው ማነው?” ብሎ ሲጠይቅ ነጋዴውም “ይኸው” ብሎ ጭንቅላቱን አሳየ፡፡
ንጉሱም “እንዴ! ይህ ምንድነው?” ብሎ ጠየቀ፡፡ በሃፍረትም የሚያደርገው ነገር ግራ ገባው፡፡
ሆኖም መታለሉን ህዝቡ እንዳያውቅ ስለፈለገ “እሺ፤ እስማማለሁ፡፡ ቃሌንም አከብራለሁ፡፡” አለ፡፡
ከዚያም ጭንቅላቱ በሙሽርነት ወደ ቤት ተወስዶ ልጅቷ መጥታ ጋብቻው ተፈፀመ፡፡ የመኝታ ሰዓት ደርሶም ወደ አልጋ በሄዱ ጊዜ ጭንቅላቱ ወደ በጣም፣ በጣም፣ ጠንካራ ወጣት ሰውነት ተለወጠ፡፡ በማግስቱ ጠዋት የሙሽራዋ እናት በጣም አዝና በጠዋት ሰዎቹ ወደተሰባሰቡበት ቦታ ስትመጣ ንጉሱም እጅግ ተክዞ ነበር፡፡
አራት ሰአት ሲሆንም ልጅቷ በሩን ከፍታ “ለምንድነው ቁርስ የማታመጡልን?” ብላ ጠየቀች፡፡
እናትየውም “ለማን ነው የምናመጣው፣ ምስኪኗ ልጄ?” አለች፡፡ በዚህ ጊዜ መልከ መልካሙ ወጣት ብቅ ብሎ በታየ ጊዜ ንጉሱ ተጠርቶ ከተማዋ በደስታ ተሞላች፡፡ ወጣቱም ልጅ የዙፋኑ ወራሽ በመሆን ለንጉስነት በቃ፡፡
የጭንቅላቱም አባት በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ንብረቱን ሁሉ ስላጣ ወደ ከተማው በመምጣት ከአገረ ገዢው እርዳታን ለመጠየቅ ተገደደ፡፡ ስለዚህ አባቱና እናቱ ከራሳቸው ልጅ እርዳታ ሊለምኑ መጡ፡፡
ጭንቅላቱም “ወደ እነዚህ ሰዎች ሄዳችሁ ወደ ውስጥ አስገቧቸውና ለሴትየዋ ምግብ ሰጥታችሁ ሰውየውን ወደ እኔ አቅርቡልኝ፡፡” ብሎ አዘዘ፡፡
እንደተባሉትም አደረጉ፤ አሃ! አሃ!
በመጨረሻም ጭንቅላቱ አባቱን “እኔ የወረወርከኝ ልጅህ ነኝ፡፡ ይኸውልህ ይህንን፣ ይህንንና ይህንን ይዘህ ወደመጣህበት ተመለስ፡፡ ነገር ግን እኔ ያንተ ልጅ መሆኔን ለማንም እንዳትነግር፡፡” ብሎ ስጦታ ሰጥቶት ሸኘው፡፡
የዚህ ታሪክ መልዕክት የሚያሳየው የመጀመሪያዋ ሚስት ታማኝና መልካም ብትሆንም አባትየው ፈቷት በመሄዱ ይህ ቅጣት መሆኑን ነው፡፡ የሻይ ነጋዴውም ከዚያ በኋላ በህይወቱ ሙሉ ሃብታምና ደስተኛ ሆኖ ቀረ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|