ሁሉም ነገር ያልፋል
በይስሃቅ አልዳዴ የተተረከ
በአንድ ወቅት ወደ ብዙ ሩቅ ቦታዎች እየተጓዘ የሚነግድ ነጋዴ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን በአንድ ስፍራ በኩል እያለፈ ሳለ በአንድ ቦታ ተሰባስበው አንዳች ነገር የሚመለከቱ ብዙ ሰዎች አየ፡፡ ነጋዴውም ወደ ሰዎቹ ጠጋ ብሎ ሲመለከት ያየው ነገር በጣም አስገራሚ ነበር፡፡ ነጋዴውና ሰዎቹ ይመለከቱ የነበረው አንድ ገበሬ አንድ ሰውና አንድ በሬ አቆራኝቶ ሲያርስ ነበር፡፡ ሰውየውና በሬው በአንድ ቀንበር ስር ሆነው እያረሱ ገበሬው ያለ ርህራሄ ሁለቱንም በጅራፍ እየገረፈ ያርሳል፡፡
በዚህ ጊዜ ነጋዴው ባየው ነገር በጣም ስላዘነ ማልቀስ ጀመረ፡፡
በቀንበሩ ስር ያለው ሰውዬም ነጋዴውን ቀና ብሎ አይቶት “ምን እያደረክ ነው? ለእኔ ማልቀስ አይገባህም፡፡ መንገድህንም ቀጥል እንጂ እዚህ አትቁም፡፡” አለው፡፡
ነገር ግን ነጋዴው አሁንም እያለቀሰ “ይህ የጭካኔ ተግባር ነው፡፡ እንዴት የሰው ልጅ እንደ በሬ ቀንበር ይጎትታል?” አለ፡፡
ሰውየውም “ግድ የለም፣ ግድ የለም፣ ሁሉም ነገር ያልፋል፣ የእኔም ስቃይ እንዲሁ ያልፋል፡፡” አለ፡፡
ነጋዴውም ትንሽ አልቅሶ መንገዱን ቀጠለ፡፡
ይህ ነጋዴ ወደተለያዩ ቦታዎች በስፋትና በርቀት ስለሚጓዝ በሚቀጥለው አመት በተመሳሳይ ወቅት በዚያ ስፍራ ሲያልፍ አምና ከበሬ ጋር ተጠምዶ ሲያርስ ያየውን ሰው አስታወሰ፡፡
በዚህ ጊዜ ወደ አካባቢው ሰዎች ሄዶ “ባለፈው አመት በዚህ ቦታ ሳልፍ አንድ ሰው ከበሬ ጋር ተጠምዶ ሲያርስ አይቼ ነበር፡፡ ታዲያ ያ ሰው የት ደረሰ? ሞቶ ይሆን?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “ኧረ በፍፁም! እንዲያውም ከዚህ ተቃራኒው ነው የሆነው፡፡ ፈጣሪ ወደታች ሲመለከት የሰውየውን ስቃይና እንባ አይቶ አሁን ንጉስ አድርጎታል፡፡ ከዚህ በኋላ ስቃዩ አብቅቶለት እንዲያውም የዚህ አገረ ግዛት ንጉስ በመሆን ህይወቱን በደስታ እየኖረ ይገኛል፡፡” አሉት፡፡
ነጋዴውም በሰማው ነገር በጣም ተደሰተ፡፡ የአንድ ምስኪን ሰው እድል እንደዚህ በፍጥነት ተቀይሮ ንጉሥ መሆኑ የማይታመን ሃቅ ሆነበት፡፡
ከዚያም “ይህንን ንጉስ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ እኔው እራሴ በአይኔ አይቼ መመስከር አለብኝ፡፡” ብሎ ወደ ቤተመንግስቱ አመራ፡፡ ወደ ቤተመንግስቱ ውስጥም ዘልቆ ሰውየው እውነትም ንጉስ ሆኖ ሲያየው ደስታው ከመጠን ያለፈ ነበር፡፡ ንጉሱም ነጋዴው ሲደሰት አይቶት “አንተ ሰው ምን እያደረክ ነው? ስለምንስ ነው የምትደሰተው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ነጋዴውም “አምና በዚህ ስፍራ እያለፍኩ ሳለ አንድ ምስኪን ሰው ከበሬ ጋር ተጠምዶ ሲያርስ በማየቴ እጅግ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ ታዲያ ዘንድሮ ወደዚህ ስፍራ ተመልሼ ስመጣ ይኸው ሰው ንጉስ እንደሆነ ሰምቼ ይህንኑ ለማረጋገጥ እችል ዘንድ ያንተን ንጉስነት በአይኔ ለማየት መጣሁ፡፡” አለው፡፡
ንጉሱም “ይህ በጣም መልካም ነገር ነው፡፡ በል ግባና ምግብና መጠጥ ይቅረብልህ” ብሎ ወደ ቤተመንግስቱ ጋብዞት ጥቂት ሃብትም ጨምሮ ከሰጠው በኋላ “ልጄ ሆይ፣ በቀንበሩ ስር የነበረውን ምስኪን ሰው በማስታወስህ እግዜር ይባርክህ፡፡ ነገር ግን ባለፈው ጊዜ የነገርኩህን ነገር ታስታውስ እንደሁ ነገሮች ይለወጣሉና የእኔም ህይወት እነሆ ተቀይሮ አሁን ንጉስ ሆኛለሁ፡፡” አለው፡፡
ነጋዴውም “ይህ በርግጥ የማይታመንና ድንቅ የሆነ ነገር ነው፡፡” አለ፡፡ ከዚያም ንጉሱ ቀበል አድርጎ “አዎ! ነገር ግን አሁንም ሁሉም ነገር ያልፋልና፣ ሁሉም ነገር ይለወጣልና ይህም ስለሚያልፍ ብዙ አትደነቅ፡፡ እኔም ብሆን ለዘለዓለም ንጉስ ሆኜ አልኖርም፡፡” አለው፡፡
ከዚያም በኋላ ነጋዴው ንጉሱን ተሰናብቶ ሄደ፡፡ ከተወሰነ ጊዜም በኋላ ነጋዴው ተመልሶ በአመቱ በዚያ ስፍራ ሲያልፍ ወዳጁን ንጉሱን መጎብኘት ፈልጎ ወደ ቤተመንግስቱ ሲሄድ በምትኩ ሌላ ንጉስ ተተክቶ አገኘ፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ አንድ ሰው ዘንድ ጠጋ ብሎ “ይቅርታ አድርግልኝ፡፡ ነገር ግን የዚህ አገረ ግዛት ንጉስ የነበረው ሰው ወዳጄ ነበርና አሁን የት እንዳለ ልትነግረኝ ትችላለህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ሰውየውም “አዎ እርሱ ሞቷል፣ ንጉሱ ሞቷል፡፡” ብሎ ሲነግረው ነጋዴው አልቅሶ፣ አልቅሶ ሲያበቃ “የመቃብሩን ስፍራ ልታሳየኝ ትችላለህ?” ብሎ ጠይቆት ወደ መቃብሩ ቦታ ሲሄዱ በሃውልቱ ላይ ጎላ ጎላ ባሉ ፊደላት “ሁሉም ነገር ያልፋልና ይህም እንደዚሁ፡፡” የሚል መልዕክት የተፃፈበትን የንጉሱን መቃብር አይቶ ነጋዴው በጣም በማዘን አልቅሶ ሄደ፡፡
በአራተኛውም አመት ወደዚሁ ስፍራ ሲመጣ “መቃብሩ በእርግጠኝነት በስፍራው ይኖራል ምክንያቱም ይህ ሊቀየር የሚችል ነገር አይደለምና፡፡” ብሎ ወደ መካነ መቃብሩ ሲሄድ መቃብሩን በስፍራው አላገኘውም፡፡ ሃውልቱን ለማግኘት ላይ ታች ቢልም ሊያገኘው ስላልቻለ ወደ አንድ ሰው ጠጋ ብሎ “ይቅርታ፣ ነገር ግን ከዚህ ቦታ ላይ አንድ ሃውልት ነበር፡፡ ሃውልቱ ላይም “ሁሉም ነገር ያልፋልና ይህም እንዲሁ” ተብሎ የተፃፈበት ሲሆን አሁን ሃውልቱ በስፍራው የለም፡፡ ወዴት እንደሄደ ልትነግረኝ ትችላለህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ሰውየውም “አዎ፣ ያንን ሃውልት አስታውሰዋለሁ፡፡ ሆኖም ሃውልቱ አሁን የት እንዳለ ልነግርህ አልችልም፡፡ በከተማዋ አዲስ አወቃቀር (ማስተር ፕላን) መሰረት ስፍራው ለሌላ ስራ ስለተፈለገ የግንባታ ማሽኑ በስፍራው ላይ ያለውን ነገር ካፈራረሰው በኋላ አሁን ባለ አስራ አምስት ፎቅ ህንፃ ሃውልቱ በነበረበት ቦታ ላይ ተሰርቷል፡፡” አለው፡፡
ነጋዴውም ሰማይ ጠቀስ ፎቁን ቀና ብሎ ተመልክቶ “እውነትም ሁሉም ነገር ያልፋል፡፡” አለ፡፡
የዚህም ታሪክ መልእክት የሚያመለክተው ምንም ብትቸገር፣ ብትጎሳቆልና ብታዝን በመጨረሻ ሁሉም ነገር እንደሚያልፍ ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|