ፌንጣው
በይስሃቅ አልዳዴ የተተረከ
በደቡብ ኢትዮጵያ በየአምስትና አስር አመታት ፌንጣዎች አካባቢውን በመውረር በምድሪቱ ላይ ከፍተና ጥፋት ያደርሳሉ፡፡ ሰብሉን በሙሉ ሙልጭ አድርገው ከበሉ በኋላ ረሃብን ትተው ይጠፋሉ፡፡
ታዲያ በአንድ ወቅት እነዚሁ ፌንጣዎች አካባቢውን በመውረር አየር ሰማዩን አጥቁረው በአካባቢው የነበረውን ሰብል በሙሉ ማውደም በጀመሩ ጊዜ ሰው ሁሉ በጩኸትና በቁጣ ቢነሳም ፌንጣዎቹ የሰውን ጩኸት ከቁብ ሳይቆጥሩ ሁሉንም ነገር እንዳልነበረ አድርገው ከስፍራው ተሰወሩ፡፡ ታዲያ ፌንጣዎቹ ከሄዱ በኋላ ጥቂት ደካማ የነበሩት ፌንጣዎች ከመንጋው ጋር ችለው መሄድ ስላልቻሉ በስፍራው ቀርተው ነበር፡፡ ሆኖም እነዚህ ደካማ ፌንጣዎች እንደበፊቱ አጥፊ ጠላቶች ሳይሆኑ ወዲያው ሰላማዊ በመሆን ከህዝቡና ከከብቱ ጋር አብረው በአንድነት መኖር ጀመሩ፡፡ ፌንጣዎቹ በሳሩ ውስጥ እየዘለሉ የሚኖሩ ሲሆን ሰዎችም በአካባቢያቸው ሲያልፉ ከቁርጭምጭሚታቸው ወይም ከጉልበታቸው በላይ አይዘሉም፡፡ ላሞችም ሲያልፉ መንገድ ይለቁላቸዋል፡፡
በመጨረሻም ጊዜ ባለፈ ቁጥር ወደ አረንጓዴ አንበጣነት ተለውጠው ከሰዎችና ከከብቶች መንገድ ላይ ዞር እያሉ ከሁሉም ነገር ጋር ተስማምተው በሰላም መኖር ጀመሩ፡፡
ከዚያም በዚህ ዓይነት ብዙ ዓመታት አለፉ፡፡
ከተጨማሪ አምስት አመታት በኋላ ሰዎች በሳር ውስጥ እየሄዱ ሳለ አንበጣዎቹ በጣም ትምክህተኛ በመሆን ከሰዎቹ ጉልበት በላይ መዝለል ጀመሩ፡፡ ገሚሱ የሰዎች እግር ውስጥ ሲገቡ፣ ገሚሱ ደግሞ ትከሻዎቻቸውና ሌሎቹም ሰዎቹ አናት ድረስ ሳይቀር እየዘለሉ መውጣት ጀመሩ፡፡
በዚህ ጊዜ ሰዎቹ “እነዚህ አንበጣዎች እንዴት ነው የጠገቡት?” ብለው አንበጦቹን “በሰላም አብረን እንኖር ነበር፡፡ ተስማምተንም እንኖር ነበር፡፡ ታዲያ አሁን ምን ነካችሁ?” ብለው ጠየቋቸው፡፡
አንበጦቹም “አሁን ነገሮች ሁሉ ተለውጠዋል፡፡ የሰማዩንም አድማስ እስኪ ተመልከቱ፡፡ ደመናውን ትመለከታላችሁ? ያ ደመና የሚመስለው ነገር ምን ይመስላችኋል? እነዚህ የፌንጣ መንጋ ስለሆኑ እንደገና ልንወራችሁ በመሆኑ ከእንግዲህ ነገሮች እንደ ቀድሞው አይሆኑም፡፡” አሉ ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|