ንጉሱና ሙዚቀኞቹ
በይስሃቅ አልዳዴ የተተረከ
በአንድ ወቅት በግዛቱ ውስጥ በፍትሃዊነቱና በብልህነቱ የታወቀ ንጉስ ነበር፡፡ ንጉሡ በጣም ጥሩ ሰው ስለነበረ ህዝቡ ሁሉ ይወደው ነበር፡፡ ይህ ንጉስ በራሱ ላይ ጥምጥም አስሮ በየቦታው ይዘዋወር ስለነበረ ሰዎች ንጉሱ ለምን እንደሚጠመጥም ስለማያውቁ ይህ የተለመደ ነገር ነበር፡፡ ሚስጢሩ ግን ንገሱ ጭንቀላቱ ላይ ትልቅ ቁስል ስለነበረበት ሰው እንዳያይበት ፈልጎ ነበር፡፡ እንዲያውም ንጉሱ ሲወለድ ጀምሮ ይህ ቁስል የነበረበት ቢሆንም ማንም ሰው በፍፁም አይቶት ስለማያውቅ ሰዎች ንጉሡ ጥምጥም ማድረግ ስለሚወድ የሚያደርግ ይመስላቸው ነበር፡፡
ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን ንጉሱ ሰውነቱን ሊታጠብ ሲል ልብሱን አውልቆ ወደ መታጠቢያው ሲገባ አንድ በአካባቢው ያልፍ የነበረ ሰው ወደ መታጠቢያው ውስጥ አጮልቆ ሲመለከት ንጉሱ ሰውነቱን ሲታጠብና ጭንቅላቱም ላይ ትልቅ ቁስል እንዳለበት አየ፡፡ በዚህ ጊዜ ይህን አይነቱ ሚስጢር ለረጅም ጊዜ ከህዝብ ተደብቆ በመቆየቱ እጅግ መገረምና መደነቅ ጀመረ፡፡ ስለዚህ ይህ ሰው ስላየው ነገር ለሌላ ሰው መንገር ፈልጎ ነገር ግን ይህንን ካደረገ ጉዳዩ ምስጢርነቱ ይቀርና ንጉሱ ምስጢሩን ያወጣው ሰው እሱ መሆኑን ከደረሰበት ሆርሶዚ ወደተባለውና የሞት ፍርድ ወደሚፈፀምበት ቦታ ወስዶ እንዳይገድለው ፈራ፡፡ ወደዚህ ስፍራ ከተወሰደ ደግሞ ከገደሉ አፋፍ ላይ አቁመው አንገቱን በገጀራ በመቀንጠስ ጭንቅላቱና ሰውነቱ ወደ ገደሉ ውስጥ እንዲወድቅ እንደሚያደርጉና ንጉሱም ይሀንን ከማድረግ እንደማይመለስ አወቀ፡፡ ስለዚህ በጣም ስለፈራ የሚያደርገው ነገር ግራ ገባው፡፡
ሆኖም ይህንን ትልቅ አገራዊ ምስጢር ለራሱ ይዞ መቆየት ስላልቻለ ለአንድ ሰው ንጉሱ ጭንቅላቱ ላይ ቁስል እንዳለው መናገር ነበረበት፡፡
ለተወሰኑ ቀናት ምስጢሩን ለራሱ ይዞ ቢቆይም ውስጥ ውስጡን አላስችል ብሎ አንጀቱንና ጨጓራውን ይበላው ስለጀመረ ከውስጡ ሊያወጣውና ለአንድ ሰው ሊነግረው ፈለገ፡፡ በመጨረሻም አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበትና ምስጢሩ ውስጥ ውስጡን በልቶ ሳይጨርሰው መናገር እንዳለበት ወሰነ፡፡
ከዚያም ወደ አንድ ወንዝ አጠገብ ሄዶ ጉድጓድ በመቆፈር ወደጉድጓዱ አጎንብሶ “ንጉሡ ጭንቅላቱ ላይ ቁስል አለበት፣ ንጉሱ ጭንቅላቱ ላይ ቁስል አለበት፡፡” እያለ ማንሾካሾክ ጀመረ፡፡
ከዚያ በኋላ ጉድጓዱን በአፈር ሞልቶ ምስጢሩን ከሰውነቱ ውስጥ አውጥቶና በዚህ ምክንያት መቃጠሉን እፎይ ብሎ ወደቤቱ ሄደ፡፡ ጊዜም እያለፈ ሄዶ ጉዳዩ አንድ አመት ሲያልፈው የተወሰኑ ሸንበቆዎች በወንዙ አጠገብ መብቀል ጀመሩ፡፡ አንደኛው ሸምበቆ የበቀለው ሰውየው ከአመት በፊት የቆፈረው ጉድጓድ አናት ላይ ነበር፡፡
ታዲያ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ንጉሱ ድግስ ጥሎ ሰውን ለማብላት ሙዚቀኞችንም ጋብዞ ነበርና ሙዚቀኞቹ ሙዚቃ ለመጫወት መጡ፡፡ እናም በወላይታ አንድ ረጅም ዋሽንት መሰል ከሸንበቆ የሚሰራ ቁመቱ ከ2 – 3 ሜትር የሚደርስ የሙዚቃ መሳሪያ ነበርና ሙዚቀኞቹም በዚህ መሳሪያ መጫወት ፈልገው ወደ ወንዙ ዳርቻ በመሄድና ሸምበቆዎችን በመቁረጥ ተመልሰው ድግሱ ላይ መጫወት ጀመሩ፡፡
ሊጫወቱ የፈለጉት ዘፈን ንጉሱን የሚያወድስ ሲሆን የዘፈኑም መልዕክት እንደሚከተለው እንዲሆን ታስቦ ነበር፤
ንጉሱ አንበሳ ነው፣ ንጉሱ አንበሳ ነው፣ ንጉሱ አንበሳ ነው፡፡
ይህ ሃረግ በሙዚቃ ቃና በዋሽንት ድምፅ ታጅቦ በመውጣት ንጉሱ አንበሳ ነው፣ ንጉሱ አንበሳ ነው፣ ንጉሱ አንበሳ ነው የሚለውን ቅላፄ ያወጣል፡፡
እናም ሙዚቀኞቹ ዝግጅታቸውን ጨርሰው ሙዚቃውን ሲጀምሩ ሙዚቀኛው በከባድ ትንፋሽ ዋሽንቱን ሲነፋው የሙዚቃው ድምፅ ቢወጣም እንደታሰበው ንጉሱ አንበሳ ነው የሚለውን ቅላፄ አልያዘም፡፡ ዋሽንቱ ራሱን ችሎ መናገር በመጀመር እንዲህ እያለ ይዘፍን ጀመር፤
ንጉሱ ጭንቅላቱ ላይ ቁስል አለበት፣ ንጉሱ ጭንቅላቱ ላይ ቁስል አለበት፡፡
ንጉሱም በሁኔታው በጣም ተበሳጭቶ ይህ ሙዚቀኛ ክበረቢስና ተሳዳቢ በመሆኑ ይህንን አይነቱን ዘፈን ህዝብ ፊት ዘፍኗልና ወደ ሆርሎዚ ተወስዶ ጭንቅላቱ እንዲቆረጥ አዘዘ፡፡
ከዚህ በኋላ ንጉሱ ሁለተኛውን ሙዚቀኛ ጠርቶ እንዲጫወት ሲጋብዘው ሁለተኛውም ሙዚቀኛ ዘፈኑን መጫወት ሲጀምር አሁንም ዋሽንቱ
ንጉሱ ጭንቅላቱ ላይ ቁስል አለው፣ ንጉሱ ጭንቅላቱ ላይ ቁስል አለው እያለ መዝፈን ጀመረ፡፡
ሁለተኛውም ሙዚቀኛ ወደ ሆርሎዚ ተወስዶ አንገቱ እንዲቀላ ተፈረደበት፡፡ ንጉሱም እጅግ በጣም በመቆጣት ድግሱ እንዲቆም ካደረገ በኋላ ሙዚቀኞቹን ጠርቶ “ምን እየሰራችሁ ነው? እኔ እዚህ ያመጣኋችሁ እንድታሞግሱኝ እንጂ እንድትሰድቡኝ አይደለም፡፡” አላቸው፡፡
እናም ሁሉም ነገር ተቋርጦ ንጉሱ ሄራጋ የተባሉትን የወላይታ አዛውንቶች በማስጠራት ይህንን ማጭበርበር አጣርተው እውነቱን እንዲያሳውቁት አዘዛቸው፡፡ አዛውንቶቹም ጉዳዩን በመመርመር ሁኔታውን ከተለያየ አቅጣጫ ከተመለከቱት በኋላ በመጨረሻ ዋሽንቱን ራሳቸው በመንፋት ሲሞክሩት ንጉሱ ጭንቅላቱ ላይ ቁስል አለው የሚለውን ዘፈን ማውጣት ጀመረ፡፡
ከዚያም አዛውንቶቹ ወደ ንጉሱ ሄደው “ሁለቱ የተገደሉት ሙዚቀኞች ጥፋተኛ አልነበሩም፡፡ ታሪኩ ከረጅም ጊዜ በፊት አንድ መንገደኛ በጭንቅላትህ ላይ ያለውን ቁስል አንተ ገላህን ስትታጠብ አይቶ በመሄድ ጉድጓድ ቆፍሮ ለጉድጓዱ ነግሮ በቀበረበት ቦታ እነዚህ ሸምበቆዎች በመብቀላቸው ሚስጢሩ ዋሽንቱ ውስጥ ገብቶ ዋሽንቱ ሲነፋ ምስጢሩን አውጥቶ ነው፡፡” አሉት፡፡
የታሪኩም መጨረሻ ይኸው ነው፡፡ ታሪኩ ሁለት መልእክቶች ሲኖሩት አንደኛው፣ ሚስጢር መያዝ ከፈለክ ሚስጢሩን ለራስህ ብቻ ልትይዘው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ምስጢር ከማንም ተደብቆ መኖር አይችልምና ነው፡፡ በመጨረሻም መታወቁ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ይኸኛው መልዕክት ስለምስጢር አያያዝ ነው፡፡
ሁለተኛው መልዕክት ግን እውነት በፍፁም ተደብቆ አይቀርም፡፡ እናት ምድር እንኳን በመጨረሻ ትተፋዋለች፡፡ ስለዚህ እውነት ትመነምናለች እንጂ አትጠፋም ልንል እንችላለን፡፡ አንድ ቀን እውነቱ መታወቁ አይቀርምና፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|