ሰማዩ እየወደቀ ነው
በይስሃቅ አልዳዴ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንዲት በግ እና አንዲት ፍየል አብረው ሲኖሩ ባለቤቶቻቸው በጣም ይጨቁኗቸው ስለነበረ በጣም ገርጥተው፣ ከስተውና ተጎሳቁለው በጣም፣ በጣም አሳዛኝ መልክ ይዘው ነበር፡፡
ባለቤቶቻቸውም በበጓና በፍየሏ እጅግ መጎሳቆል ተስፋ ቆርጠው ስለነበረ አይንከባከቧቸውም ነበር፡፡ ሌሎቹን እንስሳት ሩቅ ቦታ ወደሚገኝ ፍል ውሃ ሲወስዷቸው በጓንና ፍየሏን ግን ከቤት አስረው ያቆዩዋቸው ነበር፡፡
ይህ ለበጓና ለፍየሏ እጅግ በጣም የሚያበሳጭ ነበር፡፡ ምክንያቱም እነርሱም ከሌሎቹ እንስሳት ጋር ሄደው ከለምለሙ መስክ ሳር መጋጥና ውሃውንም መጠጣት ይፈልጉ ነበር፡፡ ነገር ግን ጉዞው ወደ ሁለት ቀናት ገደማ ስለሚፈጅና ባለቤቶቹም ብዙ እንስሳትን ወደ ስፍራው መንዳት ስለማይችሉ በጓንና ፍየሏን ሁልጊዜ ትተዋቸው ይሄዱ ነበር፡፡ ብዙ ወተት የምትታለበውን ላም፣ ወፍራሞቹን በጎችና ፍየሎች እንጂ ምስኪኖቹን በግና ፍየል ይዘዋቸው አይሄዱም ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ጎስቋላ እንስሳት ሁልጊዜ በግቢው ውስጥ ታስረው የሚበሉት ሳይኖራቸው ይውሉ ነበር፡፡
በዚህ ምክንያት በጣም የተበሳጩትና ግቢው ውስጥ ታስሮ በቤቱ አካባቢ ያለውን ነገር ከመለቃቀም ባለፈ ምንም የማያገኙት ሁለቱ እንስሳት ከእለታት አንድ ቀን ጠፍተው ወደ ፍል ውሃው ስፍራ በመሄድ የሚፈልጉትን ያህል መብላትና መጠጣት ፈለጉ፡፡
ስለዚህ በማለዳ ተነስተው ጉዟቸውን በመጀመር መንገዱ በጣም ረጅም ነበርና ሲሄዱ፣ ሲሄዱ ውለው በድንገት ከአንድ ትልቅ አንበሳ ዘንድ ደረሱ፡፡
አንበሳውም “ጎሽ! ፍየልና በግ አገኘሁ! እበላቸዋለሁ!” ብሎ በደስታ አገሣ፡፡
በጓና ፍየሏም ፈጠን ብለው “ምን እንደተፈጠረ አልሰማህም እንዴ?” ሲሉት እርሱም “አልሰማሁም፡፡ ምን ተፈጠረ?” አላቸው፡፡
“ኧረ ምድር እየተሰነጠቀች ነውና ሰማዩ ሊወድቅ ስለሆነ ነው እኛ እየሸሸን ያለነው፡፡ ሁሉም ከዚህ የተፈጥሮ አደጋ እየሸሸ ነው፡፡”
በጓና ፍየሏ ይህንን ብለው መሮጥ ሲጀምሩ አንበሳውም እውነት መስሎት ወደ ጫካው መሮጥ ጀመረ፡፡
በጓና ፍየሏም ሮጠው፣ ሮጠው፣ሮጠው ከአንድ ነብር ዘንድ ደረሱ፡፡
ነብሩም “ጎሽ! ምግቤን አገኘሁ!” ብሎ ዘሎ ጉሮሮአቸውን ሊዘነጥለው ሲል ሁለቱም “ኧረ ቆይ አያ ነብር! ክፉውን ዜና አልሰማህም እንዴ? መሬት ተሰንጥቃ ሰማዩ ሊወድቅ እኮ ነው! ስለዚህ አንተ እኛን የምትበላ ከሆነ የተፈጠረው አደጋ ይደርስብህና ይገድልሃል፡፡ ስለዚህ ሮጠህ ህይወትህን ብታተርፍ ይሻላል፡፡” አሉት፡፡ ነብሩም እነርሱን ትቷቸው ህይወቱን ለማዳን ሩጫውን ቀጠለ፡፡
አሁንም ሁለቱ እንስሳት ሲሮጡ፣ ሲሮጡ አንድ ጅብ ዘንድ ደረሱ፡፡
ጅቡም “ጎሽ! በጣም ተርቤአለሁና የምበላው ያስፈልገኛል፡፡” አለ፡፡
እነርሱም “ኧረ ቆይ አያ ጅቦ! እኛን ለመብላት ጊዜ የለህም፡፡ የተፈጠረውን ነገር አልሰማህም እንዴ? ሰማዩ ሊወድቅ ነው፡፡ ምድሪቱም እየተሰነጠቀች ነውና ይልቅ ሸሽተህ ህይወትህን አትርፍ፡፡” አሉት፡፡
ጅቡም “እሺ” ብሎ ሩጫውን ተያያዘው፡፡
ከዚያም በጓና ፍየሏ ሩጫቸውን ቀጥለው ብዙ ከተጓዙ በኋላ ፍል ውሃው ይህን ያህል የሚርቅና ከለምለሙ የሳር ምድርም ለመድረስ ይህን ያህል ጊዜ የሚወስድባቸው አልመሰላቸውም ነበር፡፡
ከተወሰነ ጊዜም በኋላ አንድ ቀበሮ አጋጠማቸው፡፡
ቀበሮውም “ጎሽ! ሁለታችሁንም እበላችኋለሁ፡፡” ሲል እነርሱም “ኧረ አይሆንም! ይህን ለማድረግ ጊዜ የለህም፡፡ የተፈጥሮ አደጋ ተነስቶ ምድሪቱ በመሬት መንቀጥቀጥ እየተሰነጠቀች ስለሆነ ሰማዩ እየወደቀ ነውና አንተም እንደሌሎቹ ሮጠህ ህይወትህን ብታተርፍ ይሻልሃል፡፡” አሉት፡፡
ቀበሮውም ሽሽቱን ተያያዘው፡፡
ከዚያም ለረጅም ጊዜ ሮጠው፣ ሮጠው ሲያበቁ ፍል ውሃው ካለበት ከአንድ ጥልቅ ሸለቆ አጠገብ ደረሱ፡፡ በዚህ ጊዜ አቀበታማውን ገደል በሩጫ በመውረድ ከውሃው ከደረሱ በኋላ የሚችሉትን ያህል ጠጥተው እስኪጠግቡም ድረስ ሳሩን ጋጡ፡፡
ጣፋጩን ፍል ውሃ ጠጥተው፣ ጠጥተው እንዲሁም አጠገቡ ያለውን ለምለም ሳር ግጠው፣ ግጠው፣ ሲያበቁ በዚያ ስፍራ ለረጅም ጊዜ ቆዩ፡፡ በመጨረሻም ወደቤታቸው መመለስ እንዳለባቸው ወስነው መንገዱን ተያያዙት፡፡
ነገር ግን የገደሉን አቀበት ሽቅብ መውጣት እንደመውረዱ ቀላል አልነበረም፡፡ ሙሉ ቀን ሲሮጡ ስለዋሉ ከመድከማቸውም በላይ ሆዳቸው በበሉት ሳርና በጠጡት ውሃ ተወጥሮ ነበረ፡፡ ሆኖም ቀስ በቀስ፣ ደረጃ በደረጃ ወደ ላይ ከፍ እያሉ በመውጣት ሆዳቸው በጥጋብ እንደተወጠረ ከረጅም ጊዜ በኋላ አቀበቱን ወጥተው ጨረሱ፡፡ ከተደላደለው መስክ ላይ በደረሱ ጊዜም በጣም ደክሟቸውና ቀኑም መሽቶ ነበር፡፡ በመጨረሻም ቀኑ በመሸ ጊዜ ሌሊቱን ከቤት ውጪ ሜዳ ላይ አድረው ስለማያውቁና በአውሬዎች እንበላለን ብለው ስለሰጉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ገባቸው፡፡ ከዚያም ወደ አንድ ግዙፍ ዛፍ አጠገብ ሄደው ጥቂት ከተነጋገሩ በኋላ “እንግዲህ እዚህ ዛፍ ስር ካደርን አውሬ ሊበላን ስለሚችል ቅርንጫፎቹ ላይ ብንወጣ ይሻላል፡፡” አሉ፡፡
ታዲያ በተፈጥሮአቸው ፍየሎች አንደዳንድ ነገሮች ላይ መውጣት ቢችሉም በጎች ግን አይችሉም፡፡ ስለዚህ ፍየሏ ዛፍ ላይ በቀላሉ መውጣት ስትችል ምስኪኗ በግ ግን ሸሆናዋ ስለማይቆነጥጥላት ዛፉ ላይ ለመውጣት ብዙ ትግል ገጠማት፡፡ በመጨረሻም ቀስ በቀስ እየቧጠጠች ከዛፉ ላይ ወጣች፡፡
ከዚያም ሁለቱም ለትንሽ ጊዜ ዛፉ ላይ ከተኙ በኋላ ከበታቻቸው አንዳች ድምፅ ሰምተው ቁልቁል ሲመለከቱ የእንስሳት ስብሰባ መሆኑን አዩ፡፡ ሁሉም እንስሳት፤ አንበሳ፣ጅብ፣ነብር፣ ተኩላ፣ ቀበሮንም ጨምሮ በታላቅ ስብሰባ ላይ ሆነው ሲወያዩ ተመለከቱ፡፡
በዚህ ጊዜ በጓና ፍየሏ በጣም ደንግጠውና ፈርተው ቀስ ብለው በቅርንጫፎቹ ላይ በመለጠፍ ከስራቸው የሚካሄደውን ስብሰባ መከታተል ጀመሩ፡፡
ከተሰብሳቢዎቹም አንዱ “እና ምን ብናደርግ ይሻላል?” ሲል ሌላኛው “እባክህ ዝም ብለህ አዳምጥ፡፡” አለው በለሆሳስ፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንስሳቱ መናገር ጀመሩ፡፡
በመጀመሪያ አንበሳው “ያምላክ ያለ! ዛሬ እንዲህ ልታለል?!” አለ፡፡
ሌሎቹም “እውነት? ምን ሆንከ?” ሲሉት “አንዲት በግና ፍየል መንገዴ ላይ አጋጥመውኝ ልበላቸው ስል ምድር እየተሰነጠቀች መሆኗንና ሰማይም ሊወድቅ እንደሆነ አስጠነቀቁኝ፡፡ እኔም የሚናገሩት ነገር እውነት መስሎኝ ህይወቴን ለማትረፍ ሮጥኩ፡፡ ለካስ እነርሱ ህይወታቸውን ለማዳን የፈጠሩት ውሸት ነበር፡፡” አለ፡፡
ነብሩም ወዲያው ቀበል አድርጎ “የፈጣሪ ያለህ! እኔም ላይ ይኸው ነገር ደርሶብኛል፡፡ እኔም ሳዳምጣቸው በተመሳሳይ ሁኔታ አታለውኛል፡፡ በእነዚያ ደደብ በግና ፍየል መታለሌ ሞኝነት ኖሯል፡፡” አለ፡፡
ጅቡና ቀበሮውም ይኸው ታሪክ በእነርሱም ላይ እንደተፈፀመ ተናገሩ፡፡
በመጨረሻም እንስሳቱ በሙሉ “ይህ በጣም አሳፋሪ ነውና በሌላ ጊዜ እነዚያን ሁለት ወሽካቶች ይዘን እንበላቸዋለን፡፡” ብለው ተስማሙ፡፡
በዚህ ጊዜ የበጓ ፊኛ በጠጣችው ውሃ ምክንያት በሽንት ስለተሞላ መሽናት ፈለገች፡፡ ነገር ግን ከዛፉ ላይ ሆና ቁልቁል ብትሽና ሽንቷ ከታች ያለው አንበሳ ላይ ስለሚያርፍ ሁሉም ዛፉ ላይ ወጥተው በአንድ ደቂቃ ይሰለቅጧቸዋል፡፡ ስለዚህ በጣም ተጨነቀች፡፡ ሽንቷን ችላ ልትይዘው ብትሞክርም ፊኛዋ ሊፈነዳ ሆነ፡፡ ስለዚህ ፍየሏን “ፍየሊት ሆይ! ፊኛዬ ስለሞላ ወደ ሽንት ቤት መሄድ አለብኝ፡፡” ብላ በሹከሹክታ ነገረቻት፡፡
ፍየሏም “የማትረቢ! አንዳች ነገር አደርጋለሁ ብለሽ ታስጨርሺናለሽ፡፡ ትንሽ ታገሽ፡፡” አለቻት፡፡
“በፍፁም፣ በፍፁም፣ በፍፁም ከዚህ በላይ መታገስ አልችልም፡፡ መሽናት አለብኝ፡፡” አለች፡፡
“አንቺ ደደብ በግ፣” አለች ፍየሏ፣ “ቢያንስ ራሳችንን ማዳን ስላለብን ልታደርጊ የምትችይው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ይኼውም ጭንቅላትሽን ቀስ ብለሽ ወደታች ዘቅዝቀሽ በቀስታ በመሽናት ሽንትሽ በሙሉ ያለ አንዳች ጠብታ የሰውነትሽ ፀጉር ውስጥ እንዲቀር ማድረግ ነው፡፡ ሽንትሽን ከዚህ በላይ መቋጠር ካልቻልሽ ያለን ብቸኛው አማራጭ ይህ ነው፡፡”
በጓ ግን “አይሆንም! አይሆንም! አልችልምና መሄድ አለብኝ፡፡” ብላ ቀስ ብላ በመዘቅዘቅ እላዩዋ ላይ ለመሽናት ልትሞክር ስትገላበጥ ሸሆናዎቿ ቅርንጫፎቹን ቆንጥጠው መያዝ ባለመቻላቸው ተንሸራታ ዱብ በማለት ከዛፉ ስር ካሉት እንስሳት መሃከል ወደቀች፡፡ ታዲያ በጓ ወድቃ ከመሬቱ ጋር በከፍተኛ ድምፅ ስትላተም እንስሳቱ እውነትም ሰማይ የወደቀ መስሏቸው ህይወታቸውን ለማትረፍ በየአቅጣጫው መሸሽ ጀመሩ፡፡ በዚህ ዓይነት በጓና ፍየሏ ከመሞት ተርፈው ሌሊቱ ሲነጋ በሰላም ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|