የአምላክ ፍትህ
በይስሃቅ አልዳዴ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንድ አዛውንት ንጉስ አንዲት ኮረዳ ያገባል፡፡ ይህቺ ወጣት ልጃገረድ ወደ ንጉሱ ቤተመንግስት ገብታ ንግስት ሆነች፡፡ በግልፅ እንደሚታወቀውም በቤተመንግስቱ ውስጥ ብዙ ማር፣ ቅቤ፣ ስጋና የፈለገችው ነገር ስላለ በጣም ተስማማት፡፡ ሆኖም የሰው ተፈጥሮ ነውና ሰው የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ሲያገኝ ሌላ መመኘቱ አይቀርም፡፡
እናም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ንግስቲቱ ከሌላ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት መመስረት ፈልጋ የባሏን አገልጋዮች በሙሉ ስትመለከት ከመሃከላቸው አንድ ወጣት ወንድ ታያለች፡፡ ወጣቱም ልጅ ረጅም፣ ደንዳናና በጣም፣ በጣም ቆንጆ ስለሆነ ከእርሱ ጋር ግንኙነት ለመመስረት ወሰነች፡፡ ከዚያም ብዙ አይነት ስራ ትሰጠው ጀመር፡፡ በዚህ ሁኔታ ሁልጊዜ አጠገቧ እንዲሆን በማድረግ የምትፈልገውን ነገር ሁሉ እያዘዘችው ሁልጊዜም ከአይኗ እንዳይሰወር ማድረግ ጀመረች፡፡
ይህ አገልጋይ በንጉሱ ቤት ያደገ ልጅ በመሆኑ እየተካሄደ ያለውን ነገር በምንም መልኩ ሳይጠረጥር በንግስቲቱ የሚታዘዘውን ነገር ሁሉ እያከናወነ ቆየ፡፡
ከዚያም ከእለታት አንድ ቀን ንግቲቱ ስሜቷን መቆጣጠር ስላቃታት ወጣቱን በቀጥታ አብሯት ይተኛ ወይም አይተኛ እንደሆን ጠየቀችው፡፡
እርሱም “አምላኬ ሆይ! ይህ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ ንጉሱ ልክ እንደ አባቴ ነው፡፡ አሳድጎኛልም፡፡ ከሚስቱ ጋር እንዴት ግንኙነት ላደርግ እችላለሁ? ይህ በፍፁም የማይቻል ነገር ነው፡፡ እናም ከአንቺ ጋር ይህንን ዓይነት ግንኙነት ከማደርግ ብሞት ይሻለኛል፡፡” አላት፡፡
በዚህ ጊዜ ንግስቲቱ በጣም ተቆጥታ ደጋግማ ብትገፋፋውም ወጣቱ ልጅ በውሳኔው ፀና፡፡ ታማኝ ስለሆነም በእምቢታው ስለገፋበት ንግስቲቱ በጣም ተበሳጨች፡፡ ከዚህ በኋላ በፍፁም ልታየው ካለመፈለጓም በላይ ልትበቀለው ፈለገች፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የንጉሱ የልደት ቀን ይከበር ነበርና ንግስቲቱ በፍፁም ደስተኛ አትመስልም ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሱ “ምን ሆነሻል?” ብሎ ሲጠይቃት “ከአገልጋዮችህ አንዱ አዋርዶኛል፣ ክብሬንም አራክሶ ንቆኛል፡፡” አለችው፡፡
ንጉሱም “ለምን? ምንድነው የተከሰተው?” አላት
እርሷም “ያንን ወጣቱን አገልጋይህን ታውቀው የለም? አብሬው እንድተኛ ጠየቀኝ፡፡” አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሱ በጣም ተናዶ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? እርሱ ማለት ልክ እንደልጄ ነው የማየው፡፡ ሰው እስኪሆን ያደገውም በዚህ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ይህ በጣም አስደንጋጭ ነገር ነው፡፡ ይህ ለአንቺ ብቻ ሳይሆን ለእኔም ንቀት በመሆኑ ልጁ መሞት አለበት፡፡ አሁኑኑ አስገድለዋለሁ፡፡” አለ፡፡
ንግስቲቱም “ነገ የልደት ቀንህ ነውና አሁን አይሆንም፡፡ ነገ እኔም አብሬ ሆኜ እንገድለዋለን፡፡ ለመቃብሩ የሚሆን ጉድጓድ እንዲቆፈር እፈልጋለሁ፡፡” አለች፡፡
ንጉሱም በዚህ ተስማምቶ በጣም ተበሳጭቶም ስለነበረ “እሺ እንግዲያው አንቺ ጉድጓዱን እንድታስቆፍሪ ሃላፊነቱን ሰጥቼሻለሁ፡፡ እኔ ደግሞ አስገድለዋለሁ፡፡” አላት፡፡
በዚህ አይነት ንጉሱ ወታደሮቹን ጠርቶ “ተመልከቱ፣ ወጥታችሁ ከዚህ መግቢያ ላይ ካለው ጉድጓድ አፋፍ ላይ ነገ ትቆሙና ማንም ቢሆን ወደ እናንተ የምልከውን ሰው አንገቱን ቀንጥሳችሁ ጉድጓዱ ውስጥ ቅበሩት፡፡” ብሎ አዘዛቸው፡፡
ንግስቲቱም ሄዳ ለልጁ መቅበሪያ የሚሆነውን ትልቅ ጉድጓድ አስቆፈረች፡፡
ከጥቂት ቆይታ በኋላም ንጉሱ ወጣቱን ልጅ አስጠርቶ “አንተ ልጅ፣ ነገ ጠዋት እንድታደርግ የምፈልገውን ነገር ልክ በሶስት ሰአት ላይ እንደዚህ ወደሚባል ቦታ ትሄዳለህ፡፡” አለው፡፡ ወጣቱም ልጅ ምንም ሳይጠራጠር “እሺ ጃንሆይ፣ እርስዎ ካሉ እሄዳለሁ፡፡” አለ፡፡
እናም በማግስቱ ወደ ሁለት ሰአት ተኩል ገደማ ሲሆን ንግስቲቱ “መቼም ንጉሱ እስካሁን አስገድሎት ስለሚሆን ቀብሩ እንዴት እየተካሄደ እንደሆነ ሄጄ ማየት አለብኝ፡፡” ብላ አሰበች፡፡
ይህንንም ብላ ጉድጓዱ ወዳለበት ቦታ ስትሄድ የንጉሱ ጠባቂዎች ሲይዟት “ምን እያደረጋችሁ ነው?” አለቻቸው፡፡
እነርሱም “ንጉሱ በዚህ ሰአት ወደዚህ የሚመጣ ማንኛውንም ሰው አንገት ቆርጠን በመጣል እንድንቀብረው አዞናል፡፡” አሏት፡፡ ንግስቲቱም “ይህ በፍፁም የማይታመን ነው፡፡ እኔን ለማለት ፈልጎ አይደለም፡፡” እያለች ብትለፈልፍም ጠባቂዎቹ “አይሆንም፣ እኛ ትዕዛዙን መፈፀም አለብንና የጌታችንን ቃል መፈፀም አለብን፡፡” ብለው አንገቷን ቆርጠው ጉድጓዱ ውስጥ ቀበሯት፡፡
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ወጣቱ አገልጋይ መጥቶ “ምን እየተካሄደ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡
እነርሱም “ይህ የማይታመንና በፍፁም የሚያስደነግጥ ነገር ነው፡፡ ንጉሱ ሚስቱን እንድንገድላት ነግሮን ይህንን ነው ያደረግነው፡፡” አሉት፡፡
በዚህ ጊዜ ወጣቱ አገልጋይ ወደ ንጉሱ ሮጦ በመሄድ “ጃንሆይ፣ ንግስቲቱ በጠባቂዎችህ ተገድላለች፡፡” አለው፡፡
ንጉሱም በጣም ተበሳጭቶ ፀጉሩን እየነጨ መጀመሪያ በጣም መናደዱን ገለፀ፡፡ በኋላም ተረጋግቶ ታሪኩን ሲመለከትና እውነቱን ሲረዳ በጣም፣ በጣም አዝኖ “ንግስቲቱ ልክ የሚገባትን ቅጣት ነው ያገኘችው፡፡” አለ፡፡
ከዚያም በኋላ ንጉሱ እንደገና አግብቶ፣ በደስታ መኖር ጀመረ፡፡
ስለዚህ የዚህ ታሪክ መልእክት ለጠላትህ መቀበሪያውን አስፍተህ አትቆፍር፣ አንተ ራስህ ልትገባበት ትችላለህና የሚል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|