የአምላክ ፍርድ
በይስሃቅ አልዳዴ የተተረከ
ፈጣሪ አምላክ ቢያንስም ቢበዛም የእያንዳንዱን ሰው ፀሎት ይሰማል፡፡ የሚከተለው ታሪክም የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡
በአንድ ወቅት አንድ በጫካ ውስጥ ይኖር የነበረ ግዙፍና አስፈሪ አንበሳ ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ ለፈጣሪ አምላኩ ፀሎት ያደርስ ነበርና ከእለታት አንድ ቀን “አምላኬ ሆይ፣ የእለት እንጀራዬን ስጠኝ፡፡ ቀኑን ሙሉ ምንም ሳልበላ ማሳለፍ አልፈልግምና አንድ የደነደነ ድኩላ፣ ሚዳቋ፣ አይጠ መጎጥ፣ ወይም የዱር አሳማም ሆነ ሌላ የሚበላ ነገር ትሰጠኝ ዘንድ እማፀንሃለሁ፡፡ አምላኬ ሆይ ሁሉ ነገር በአንተ እጅ ነውና ያለው አንተ ታውቃለህ፡፡” እያለ ፀለየ፡፡
ታዲያም በሚያስገርም ሁኔታ ጥቂት ኪሎሜትሮች ራቅ ብሎ አንዲት እርጉዝ አይጠ መጎጥ ነበረች፡፡ አይጠ መጎጧም በጠዋት አምላኳን “ፈጣሪ ሆይ፣ እርጉዝ በመሆኔ አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጉልበቴ ደክሟልና ምንም ነገር ሊይዘኝ ቢመጣ እንደድሮው ሮጬ ማምለጥ የማልችልበትና የመውለጃ ጊዜዬም ስለደረሰ ከክብደቴ የተነሳ መንቀሳቀስ የማልችልበት ወቅት ላይ በመሆኔ አምላኬ ሆይ ሁሉንም ነገር ላንተ ትቸዋለሁና ምንም አይነት የዱር እንስሳ፣ አንበሳ፣ ነብር፣ ጅብም ሆነ ሌላ አውሬ እንዳያየኝ አድርግልኝ፡፡ ደካማህ ነኝና አምላኬ ሆይ እንዳልሞት ጠብቀኝ፡፡” ብላ ፀልያለች፡፡
እናም አይጠ መጎጧና አንበሳው በየፊናቸው የጠዋት ፀሎታቸውን ካደረሱ በኋላ ከጫካው ወጡ፡፡ አንበሳው በበኩሉ የእለት ጉርሱን ያገኝ ዘንድ ፀልዮ ከጫካው አንድ ወገን ሲወጣ አይጠ መጎጧም ክፉ እንዳይገጥማት በመፀለይ ከሌላው የጫካ ክፍል ወጣች፡፡ በመጨረሻም እነዚህ ሁለት እንስሳት በድንገት ተገናኝተው ፊት ለፊት ተፋጠጡ፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው “ተመስገን አምላኬ፡፡ አንተ ደግና ሚዛናዊ አምላክ በመሆንህ ለእለት ጉርሴ ፀልዬ ከመውጣቴ አይጠ መጎጧን ፊት ለፊት አመጣህልኝ፡፡ እውነትም አንተ ሩህሩህ ጌታ ነህና ፀሎቴን በፍጥነት በመስማትህ አመሰግንሃለሁ፡፡” ብሎ ፈጣሪውን አመሰገነ፡፡
አይጠ መጎጧ ግን “ምነው አምላኬ? ምን ጉድ ጣልክብኝ? አደራህን ብዬ ስፀልይ ቆይቼ ፀሎቴን እንኳን ተናግሬ ሳልጨርስ ዘሎ ሊያንቀኝ በተዘጋጀ አንበሳ ላይ ትጥለኝ! ፈጣሪዬ ሆይ አሁን ምን ማድረግ እችላለሁ? መቼም አንተ የዚህ ሁሉ አለም ፈጣሪ በመሆንህ ሁሉንም አንተ ታውቃለህና ይህንንም ጉዳይ ላንተው እተወዋለሁ፡፡” ብላ በብዙ ፍራቻ ተናገረች፡፡
እናም አንበሳው ጡንቻውን ወጣጥሮ ዘሎ ሊይዛት በተዘጋጀበት ቅፅበት አንድ በጣም ትልቅ የዱር አሳማ መንጋ መጣ፡፡ አሁን መቼም ሁላችሁም የዱር አሳማን ምንነት ታውቃላችሁ፡፡ እነዚህ እንስሳት በጫካ ውስጥ ከሚኖሩ አውሬዎች ሁሉ በጣም አጥፊዎች ናቸው፡፡ እነዚህ እንስሳት በጣም ትምክህተኞችና እምነት አልባ በመሆናቸው ስለፈጣሪ ግድ የላቸውም፡፡ ጭቃ ውስጥ ገብተው እየተንቦጫረቁ መጮህና ይህንንም ደጋግመው ማድረግ ይወዳሉ፡፡ በዚህ አይነት ቀኑን ሙሉ ያለገደብ ሲበሉ የሚውሉ በጣም መጥፎ እንስሳት ናቸው፡፡ እናም እነዚህ መልከ ጥፉ እንስሳት አንበሳውና አይጠ መጓጧ በተፋጠጡበት ቅፅበት በጎዳናው እየተንጋጉ በሁለቱ እንስሳት መሃከል አቋርጠው መሮጥ ጀመሩ፡፡ አንበሳም አሳማዎችን ስለሚበላ ዘሎ አንዱን ሲይዘው፣ አንዱ ሲያመልጠው፣ እነደገና ሌላውን ሲይዝና ሲጥል ቆይቶ በመጨረሻ አራትና አምስት የሚሆኑትን ለመግደል ቻለ፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ምስኪኗ አይጠ መጎጥ ቀስ ብላ ወደጫካው በመሄድ ቅጠሎቹ ውስጥ ተሰወረች፡፡
ስለዚህ ይህ የሚያሳየን አምላክ የፈጠራቸውን ማንኛቸውንም ፍጡራን እንደማይረሳቸው ነው፡፡ ግዙፉና ኃያሉ አንበሳ ለቁርሱ ሲፀልይ ምግቡን አገኘ፡፡ ትንሿ ምስኪን አይጠ መጎጥ ደግሞ ለህይወቷ ስትፀልይ ከሞት መትረፍ ቻለች፡፡
እናም ይህ ታሪክ የሚነግረን ትልቅም ሆንን ትንሽ ፈጣሪ ፀሎታችንን ሁልጊዜ እንደሚሰማ ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|