ስስታም አትሁን
በይስሃቅ አልዳዴ የተተረከ
በአንድ ወቅት ሁሉንም ነገር አብረው የሚያደርጉ፣ የሚዋደዱ፣ አንዱ ሌላውን የሚንከባከብና ያላቸውን ተካፍለው የሚኖሩ ሰባት ጅቦች ነበሩ፡፡ አብረውም በአካባቢው በመዟዟር ያገኙትን ተካፍለው የሚበሉ ጓደኞች ነበሩ፡፡ ስድስቱ ጅቦች ወንዶች ሲሆኑ አንዷ ሴት ነበረች፡፡ ሴቷ ደካማ ስለነበረች ከወንዶቹ ጋር መወዳደር አልቻለችም፡፡ በአንጻሩ እነርሱ ጠንካራ፣ ጡንቻ ያላቸውና ቁጡ ሲሆኑ ከሴቷ ቀድመው በመሮጥ ያገኙትን እንስሳ እየገደሉ እርሷ ሳትደርስ በልተው ይጨርሱት ነበር፡፡ ስለዚህ ከወንዶቹ ጋር እኩል መሻማትና ከእነርሱ እኩል መሰለፍ አልቻለችም፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ወንዶቹ መስኩን አቋርጠው ሲሮጡ እርሷም ከኋላቸው እየተከተለች ከአንድ ጉድጓድ አጠገብ ሲደርሱ አንድ አህያ ሞቶ ከጉድጓዱ ውስጥ ወድቆ አዩ፡፡
በዚህ ጊዜ ስድስቱ ወንድ ጅቦች ለማሰብ ጊዜም ሳያባክኑ ወደ ጉድጓዱ ዘለው ሲገቡ ሴቷ ጅብ “ከዘለልኩ ከጉድጓዱ ተመልሼ መውጣት አልችል ይሆናል፡፡” ብላ በማሰብ ጉድጓድ ውስጥ መግባት ፈራች፡፡
እናም ገብጋቦቹ ጅቦች የአህያውን አካል እየዘነጣጠሉ በፍጥነት በስግብግብነት መብላት ጀመሩ፡፡
ምስኪኗ ሴት ጅብም ወደ ጉድጓዱ አዘቅዝቃ እየተመለከተች “እባካችሁ፣ እባካችሁ ትንሽ ነገር ወርውሩልኝ፡፡ ትንሽ የኩላሊት ቁራጭ ወይም ልቡን ወይም ደግሞ የአከርካሪውን አጥንትም ሆነ አንዳች ነገር ጣሉልኝ፡፡” እያለች ብትማፀናቸውም እነርሱ ግን አሻቅበው ወደ ላይ እየተመለከቷት “አንቺ ፈሪ ጅብ ለምን አብረሽን ዘለሽ አልገባሽም? በጣም ርቦናልና ምንም ልናደርግልሽ አንችልም፡፡” አሏት፡፡
ስለዚህ ሴቷ ጅብ ወንዶቹ እያንዳንዱን ነገር ጠራርገው ሲበሉ በጉጉት ከመመልከት በስተቀር ምንም ማደረግ አልቻለችም፡፡
ነገር ግን ሌሊቱ አልፎ ንጋት በመጣ ጊዜ ጅቦቹ ሁሉ ወደ ቤታቸው መመለስ ነበረባቸውና ሴቷ ጅብ ተነስታ ወደ ቤቷ ሄደች፡፡
ወንዶቹ ግን በጣም ብዙ በልተው ሆዳቸው ተወጥሮ ስለነበረ ከጉድጓዱ ውስጥ ዘለው መውጣት አቃታቸው፡፡ ቢዘሉ፣ ቢዘሉ፣ ከጉድጓዱ መውጣት አቃታቸው፡፡ ሴቷም ጅብ ወደ ዋሻዋ ከመግባቷ በፊት ምንም የምትበላው ነገር ስላልነበራት ጥቂት ጥንዚዛዎችን በልታ ነበር፡፡
በሁለተኛው ቀን ከዋሻዋ ወጥታ ጥቂት እንሽላሊቶችን ይዛ ወንድሞቿ ቀኑን እንዴት እንዳሳለፉ ልታያቸው ሄደች፡፡ ወደታች ስትመለከትም ሁሉም ጅቦች ጉድጓዱ ውስጥ ነበሩ፡፡
እርሷም “እንዴት ናችሁ?” ብላ ሰላምታ ስትሰጣቸው እነርሱም “እኛ ደህና ነን፡፡ አንቺ እንዴት ነሽ?” ብለው ጠየቋት
እርሷም “እኔም ደህና ነኝ፡፡ ለምንድነው ከጉድጓዱ ዘላችሁ የማትወጡት?” አለቻቸው፡፡
እነርሱም “ለማምለጥ ሞክረን ነበር፡፡ ነገር ግን በቂ ጉልበት የለንም፡፡” አሏት፡፡ እርሷም “እስኪ ራሳችሁን ተመልከቱ፡፡ለምንድነው በቂ አቅም የሌላችሁ? አንድ ሙሉ አህያ ብቻችሁን በልታችኋል፡፡ ትንሽ ቁራጭ እንኳን እንድትሰጡኝ ብለምናችሁ እምቢ አላችሁ፡፡ በሉ ኃይላችሁን አሰባስባችሁ ዘላችሁ ውጡ፡፡” አለቻቸው፡፡
እነርሱም “ብንሞከር፣ ብንሞክር አቅቶናልና መሰላል ወይም ምሰሶ አለያም አንዳች ነገር አምጥተሽ ለምን አትጎትችንም?” ሲሏት “እኔ እናንተን እንድረዳችሁ በእውነት ትጠብቃላችሁ? አታስታውሱም እንዴ ቁራጭ ኩላሊት ወይም ልብ ብለምናችሁ ምንም ብጣሽ ስጋ አንሰጥም አላላችሁኝም?” ብላቸው ጥላቸው ሄደች፡፡
በሶስተኛውም ቀን ልታያቸው ስትመጣ ምንም ስላልተመገቡ በጣም ርቧቸው አገኘቻቸው፡፡
እናም “እንደምንድናችሁ?” ብላ ስትጠይቃቸው “በጣም ተርበናል፡፡ እጅግ ስለተራብን አንድ ሁለት እንሽላሊቶችን ይዘሽ ወርውሪልን፡፡” አሏት፡፡
እርሷም “እየቀለዳችሁ መሆን አለበት፡፡ እናንተ አህያውን ስትበሉ ምንም ነገር ልትወረውሩልኝ አልፈለጋችሁም ነበር፡፡ እናም እንዴት እንሽላሊት ይዤ እንድወረውርላችሁ ትጠብቃላችሁ?” አለቻቸው፡፡
በዚህም ዓይነት ለተወሰኑ ቀናት ቀጠለች፡፡
በየቀኑ እየመጣች በመጣች ቁጥርም “ተመልከቺ! በጣም ተርበናል፣ በረሀብ ልንሞት ነውና እባክሽ እርጂን፡፡” ሲሏት በየቀኑ ትታቸው ትመለሳለች፡፡
ታዲያ አንድ ቀን “አንድ መፍትሄ አለኝ፡፡” አለቻቸው፡፡ እነርሱም ቀና ብለው አይተዋት “ምንድነው?” ሲሏት “ስድስታችሁም ትግል ግጠሙና ደካማ ሆኖ የተገኘው ጅብ እጣ ፈንታ በፈጣሪ ስለሚወሰን አሸናፊዎቹ ይበሉታል፡፡” አለቻቸው፡፡
እናም አንዱ እስኪወድቅ ታግለው አንዱ ሲወድቅ በሉት፡፡ ይህ በእንደዚህ አይነት ቀጥሎ በየቀኑ የዙር ግብግብ ሲደረግ እርሷ ጉድጓዱ አፋፍ ላይ ቁጭ ብላ ወደታች ጅቦቹ አንድ በአንድ እየሞቱ ሁለት ብቻ ቀሩ፡፡
እነርሱም “እባክሽ፣ እባክሽ በረሃብ መሞታችን ነውና እርጅን፡፡” አሏት፡፡
እርሷም “ነገር ግን አሁን የቀራችሁት ሁለታችሁ ብቻ ናችሁና ታግላችሁ ከሁለታችሁ የወደቀ መበላት አለበት፡፡” አለቻቸው፡፡
የቀሩት ሁለት ጅቦች በጣም ግዙፍና በመንጋው ውስጥ እጅግ ጠንካራ የነበሩ ናቸው፡፡ እነርሱም ታግለው፣ ታግለው እርስ በርስ እየተገፋፉና እየተነካከሱ ቆይተው አንደኛው ማሸነፍ ነበረበትና አንደኛው ሲወድቅ ሌላው በላው፡፡ ስለዚህ ይህኛው ጅብ ለጥቂት ቀናት የሚበላው ስላገኘ ቢረካም በኋላ በራበው ጊዜ ሴቷ ጅብ ስትመጣ “ተመልከቺ! አሁን ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡ በረሃብ እየተሰቃየሁ ነውና ምን ባደርግ ይሻለኛል?” አላት፡፡
እርሷም “እንግዲህ እኛ ጅቦች አንደኛው እግራችን ጥቅም ስለሌለው እናነክሳለን፡፡ ስለዚህ የማይጠቅመውን አንዱን የኋላ እግርህን ዘንጥለህ ብላው፡፡” አለችው፡፡
ጅቡም የኋላ እግሩን ዘንጥሎ ሲያነሳው እጅግ በጣም ቢያመውም እርሱን በልቶ ሲጠግብ ተኛ፡፡
በሚቀጥለው ጊዜ ተመልሳ ስትመጣ “ዛሬ እንዴት ነህ?” አለችው፡፡ እርሱም “ቁስሉ በጣም እያመመኝ ነው፡፡ ረሃቡም ጠንቶብኛል፡፡ ምን ላድርግ?” አላት፡፡
እርሷም “ሁለቱም የኋላ እግሮችህ አይጠቅሙምና ሌላኛውንም ብላው፡፡” አለችው፡፡
ከዚያም ሁለተኛውንም የኋላ እግር ዘንጥሎ ህመሙን ቻል በማድረግ በላው፡፡ ሆኖም የእግሩ ቁስል አመርቅዞበት ጋንግሪን ስለያዘው ሞተ፡፡
በዚህ አይነት ስድስቱም ገብጋባ ጅቦች ሆዳቸውን ብቻ በማሰብ ወደ ጉድጓዱ ገብተው በእንደዚህ ያለ አሰቃቂ ሁኔታ ሲሞቱ ከሆዷ ባሻገር ማሰብ የቻለቸው ሴቷ ጅብ ግን ከዚህ ተርፋ በደስታ መኖር ጀመረች፡፡
ስለዚህ ለጊዜያዊ ጥቅም ብለን ወዳልተገባ ነገር ከመግባታችን በፊት ነገሮችን በማመዛዘን ክፉውንና ደጉን መለየት አለብን፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|