ዘጠኙ ወንድማማቾች
በአበበ ከበደ የተተረከ
በአንድ ወቅት ዘጠኝ ልጆች የነበሩት ሰው ነበር፡፡ ልጆቹንም ከመጀመሪያው ጀምሮ “ልጅ ቁጥር አንድ፣ ልጅ ቁጥር ሁለት” እያለ ሁሉንም በቁጥር ሰየማቸው፡፡
ታዲያ አንድ ቀን አባትየው የመጨረሻ ልጁን ልጅ ቁጥር ዘጠኝን ወደ ወላይታ ልኮ ቡልኮ እንዲገዛለት አዘዘው፡፡ ጥሩ ቡልኮ የሚገኘው ከወላይታ ነበር፡፡ እናም ልጁ ተነስቶ ወደ ወላይታ በመሄድ ሩቅ ጉዞ ስለነበረ አምስት ቀናት ለመሄድ፣ አምስት ቀናት ደግሞ ለመመለስ ይፈጅ
ነበር፡፡ ሆኖም ልጁ ቡልኮውን ለመግዛት ወደ ወላይታ ሄዶ ሳለ አባትየው በድንገት ታሞ ሞተ፡፡
በዚህ ጊዜ የቀሩት ስምንቱ ልጆች ያባታቸውን ንብረት በሙሉ፤ ከብቶቹን፣ መሬቱን፣ሰብሉንና ሁሉንም ነገር ተከፋፍለው ለልጅ ቁጥር የተውለት አንድ በጣም ከሲታና ታማሚ የማይረባ በሬ ብቻ ነበር፡፡
ልጅ ቁጥር ዘጠኝ ቡልኮውን ይዞ ከሄደበት ሲመለስ “አባታችን ሞቷል፡፡ ለአንትም ትቶልህ የሞተው ይህንን ከሲታ በሬ ብቻ ነው፡፡” አሉት፡፡
በዚህ ጊዜ ቁጥር ዘጠኝ በሁኔታው ስለተከፋ ምን ማድረግ እንዳለበት ማሰብ ጀመረ፡፡ በሬውንም አርዶ ስጋውን ከበላ በኋላ ቆዳውን ወደ ገበያ ይዞ ወጣ፡፡
በየቦታው ተዟዙሮ ቆዳውን ለመሸጥ ቢፈልግም በዚያ የገበያ ቦታ ቆዳ ተፈላጊ ዕቃ ባለመሆኑ የሚገዛው ሰው አጣ፡፡ ቀኑን ሙሉ ገበያው ስፍራ ውሎ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገባው፡፡ ቀኑ በመሸ ጊዜም ዝናቡ መጥቶ ያወርደው ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ ሰው ሁሉ እቃውን፣ ገንዘቡንና ንብረቱን እየያዘ ወደ አንድ ዛፍ ስር መጠለል ጀመረ፡፡
በዚህ ጊዜ ልጅ ቁጥር ዘጠኝ ማንም ሳያየው ቀስ ብሎ ከዛፉ ላይ በመውጣት አደፈጠ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ግዙፍ ብልጭልጭታ በሰማዩ ላይ መብለጭለጭ ሲጀምር ልጅ ቁጥር ዘጠኝ ቆዳውን ቀስ ብሎ በመወጠር ከዛፉ ግንድ ጋር በሃይል ይመታው ጀመር፡፡
ቆዳውም ከዛፉ ግንድ ጋር ሲመታ ባወጣው አስፈሪ ድምጽ ምክንያት ሰው ሁሉ ዛፉ በመብረቅ የተመታ መሰለው፡፡ በዚህም ደንግጠው ቀና ብለው ሳይመለከቱ ገንዘባቸውንና ንብረታቸውን ትተው ወደ ተለያዩ አቅጣጫ ተበታተኑ፡፡
በዚህ ጊዜ ቁጥር ዘጠኝ ከዛፉ ላይ ወርዶ ውድ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ሰብስቦ ወደ ወንድሞቹ ሄደ፡፡
ወንድሞቹም ይዞ የመጣውን ባዩ ጊዜ “ይህን ሁሉ ሃብትና ንብረት እንዴት ልታገኝ ቻልክ?” ብለው ጠየቁት፡፡
እርሱም “አልሰማችሁም እንዴ? ዛሬ የከብት ቆዳ ገበያው ላይ በጣም፣ በጣም በውድ ሲሸጥ ነው የዋለው፡፡ ያ ትንሽ፣ ከሲታና ደቃቃ የሰጣችሁኝ በሬ ቆዳ ነው ይህንን ሁሉ ንብረት ያስገኘልኝ፡፡ ታዲያ የትልቅ ወፍራም በሬ ቆዳ ገበያው ላይ ምን ያሀል ሊያወጣ እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ስምንቱ ወንድማማቾች ከብቶቻቸውን ሁሉ አርደው ቆዳቸውን ወደ ገበያ ይዘው ወጡ፡፡
ነገር ግን ገበያው ቦታ ደርሰው ሲመለከቱ የቆዳ መሸጫ ቦታ አልነበረም፡፡ አንደኛው ቦታ ሽንኩርት መሸጫ ሲሆን ሌሎች ቦታዎች እንደዚሁ የሌሎች ነገሮች መሸጫ ነበሩ፡፡ ወንድማማቾቹም ሌላ ቦታ ፈልገው ቆዳውን ለመሸጥ ሲሞክሩ ነጋዴዎቹ “ጥፉ ከዚህ! የእናንተን የገማ ቆዳ ከእቃዎቻችን አካባቢ አጥፉ፡፡ ሄዳችሁ ቆዳ የሚሸጥበት ቦታ ተቀመጡ፡፡” ቢሏቸውም እንደዚህ ያለ ቦታ አልነበረም፡፡
በመጨረሻ ቀኑ በመሸ ጊዜ ወንድማማቾቹ በጣም ተበሳጭተው ወደ ቤት በመመለስ “አታለልከን፣ አሞኘኸን፡፡ ይህንን ለምንድነው ያደረከው?” ብለው ሲጠይቁት ቁጥር ዘጠኝ “ምንም አይደል፡፡ ይህን ለምን እንዳደረኩ እነግራችኋለሁ፡፡ ነገር ግን በቅድሚያ አንድ ውለታ ዋሉልኝና ምስጢሩን እነግራችኋለሁ፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም “እሺ” ሲሉት “አሁን ወደ ጎዳናው አውጥታችሁ የንብ ቀፎ ላይ አድርጋችሁኝ ከዛፉ ላይ እንድታስሩኝ እፈልጋለሁ፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም እርሱ እንደጠየቃቸው በማድረግ ከአንድ ትልቅ ዛፍ ላይ ወስደው ከንቡ ቀፎ ጋር ቅርንጫፉ ላይ አሰሩት፡፡ ከዚያም “በሉ አሁን ወደ ቤት ሂዱና እኔ ስመለስ ስለጉዳዩ እነግራችኋለሁ፡፡” ብሏቸው እነርሱም ትተውት ሄዱ፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አንድ ሃብታም ሰው በበቅሎ ላይ ሆኖ በስፍራው ሲያልፍ ቀና ብሎ ተመልክቶ ከንብ ቀፎ ጋር ታስሮ ዛፍ ላይ የተሰቀለውን ሰው ሲያይ በመገረም “አንተ ሰው ሆይ! እዚያ ላይ ምን እያደረክ ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ልጁም “የዚህ አካባቢ ሰዎች ንጉሳቸው እንድሆን ስለፈለጉ እንደዚህ አድርገው ለንጉስነት እያሰለጠኑኝ ነው፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ስልጣን የጠማው ነጋዴ “ይህ በጣም ደስ ይላል፡፡ እኔም ንጉስ ብሆን እወዳለሁ፡፡” አለ፡፡
ልጁም “ታዲያ ለምን ቦታ አንቀያየርም?” ብሎት ነጋዴው ቁጥር ዘጠኝን ከዛፉ ላይ አውርዶት ራሱ ቀፎው ውስጥ በመግባት ቁጥር ዘጠኝ ዛፍ ላይ እንዲሰቅለው ካደረገ በኋላ ልጁ ቆንጆዋን በቅሎ ተሳፍሮ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
ወንድሞቹም በዚህች ቆንጆ በቅሎ መመለሱን ሲያዩ በጣም ተገርመው “ይህችን ቆንጆ በቅሎ እንዴት ልታገኝ ቻልክ?” ብለው ጠየቁት፡፡
ቁጥር ዘጠኝም “አንዲት በቅሎ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ምስጢሩን አልነግራችሁም፡፡ ነገር ግን እዚያ ላይ ቀፎው ውስጥ የፈለጋችሁትን ነገር ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ እንዲያውም ሮጬ የመጣሁት ይህንኑ ዜና ልነግራችሁ ነው እንጂ እዚያው ቆይቼ ብዙ ነገሮችን ማግኘት እችል ነበር፡፡ ሆኖም አንዲቷን በቅሎ ብቻ ወስጄ ዜናውን ለእናንተ ልነግር መጣሁ፡፡” አላቸው፡፡
ሁሉም ወንድሞቹ በነገሩ ተደስተው “እውነትህን ነው?” ሲሉት “አዎ! እስኪ አስቡት! አንድ ሰው ከቀፎ ውስጥ ይህን ያሀል ነገር ማግኘት ከቻለ ስምንት ሰዎች ምን ሊያገኙ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ሁሉም እየሮጡ ወደ ዛፉ በመሄድ እየተጋገዙ እያንዳንዳቸው አንድ ቀፎ ውስጥ ገቡ፡፡ ገመድ በመጠቀም መዘውር በማዘጋጀት ሁሉም እየተሳሳቡ ዛፉ ላይ ወጡ፡፡ ነገር ግን ቁጥር ዘጠኝ ገመዱን አጥብቆ ይዞ ስለነበረ ሁሉም ወጥተው ካበቁ በኋላ የያዘውን ገመድ ሲለቀው ስምንቱም ልጆች ከነበሩበት ሩቅ የዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ወደ መሬት በመፈጥፈጥ ሞቱ፡፡
ቁጥር ዘጠኝም ስምንቱን ወንድሞቹን በዚህ አይነት ካስወገዳቸው በኋላ ወደ አባቱ መሬት በመመለስ ከብቶች ባይኖራቸውም የቀረውን ንብረት ሁሉ ወርሶ፤ የቡና ተክሉን፣ የእንስት ማሳውን፣ ቤቶቹንና የቀረውን ነገር ሁሉ ወርሶ በአባቱ ሃብት በደስታ መኖር ጀመረ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|