ንጉሱና ለማኟ ሴት
በአበበ ከበደ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንዲት ትንሽ ጎጆ የነበራት ለማኝ ሴት ጎጆዋን እየተወች ልመና ትውል ነበር፡፡ ሴትየዋ ለማኝ ትሁን እንጂ በግዛቲቱ ውስጥ ካሉት እጅግ በጣም ውብ ሴቶች አንዷ ነበረች፡፡
ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን ወደ ጎዳና ወጥታ በመለመን ላይ ሳለች የግዛቲቱ ንጉስ ከችሎት ሲመለስ አገኘችው፡፡ ንጉሱም ይህችን ውብ ሴት አይቶ በመማረክ የጥርስ መፋቂያ ሰጣት፡፡ ለማኟም ሴት መፋቂያውን ይዛ ወደቤቷ ሄዳ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እጅግ በጣም የሚያምር ወንድ ልጅ ወለደች፡፡
ለማኟ ሴት ወደ ልመና ተግባሯ ስትሰማራ ልጇን ይዛው መሄድ ስላልፈለገች በጨርቅ ጠቅልላ ቤቷ ትታው ትሄድ ነበር፡፡ የልጁንም ስም “መፋቂያ” (በሲዳምኛ ፊክዎ ፊኪቾ) አለችው፡፡ እናም ከቤት በወጣች ቁጥር በጨርቅ ሸፍናው ትሄድና ወደ ቤት ስትመለስ ልጇ ደህና መሆኑን ለማረጋገጥ ትዘፍንለት ነበር፡፡ ልጁም የእናቱንም የዘፈን ድምጽ ሲሰማ ከተጠቀለለበት ጨርቅ ውስጥ እየሮጠ መጥቶ ሰላምታ ይሰጣታል፡፡
በሌላ ጊዜ ግን ሌሎች ሰዎች መጥተው ሌላ ድምጽ ሲሰማ ጥቅልል ብሎ በመተኛት አይመልስላቸውም ነበር፡፡
ያንን መፋቂያ የሰጣት ንጉስ ታዲያ ባለትዳር ቢሆንም ሚስቱ መሃንና የማትወልድ ነበረች፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ይህች የንጉሱ ሚስት በጣም ቆንጆ ወንድ ልጅ ስለወለደችው ለማኝ ሴት ትሰማና ልጇን ከለማኟ ሴት ትሰርቅባታለች፡፡
ለማኟም ሴት ከልመናዋ ተመልሳ ወደ ቤት ስትመጣ “የእኔ ፊክዎ ፊኪቾ፣ የት ነው ያለኸው? በጨርቅ ሥር ጠቅልዬ የተውኩህ ልጄ አለህ ወይ?” እያለች ብትዘፍንም ምንም መልስ አጣች፡፡ ወደ ጎጆዋ ሮጣ ገብታ ብትፈልገውም ልጇ አልነበረም፡፡ እናም በአካባቢው ሁሉ ብትፈልግ፣ ብትፈልግ ልታገኘው አልቻለችም፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ታዲያ ንግስቲቱ ወለድኩ ብላ በቤተመንግስቱ ታላቅ ድግስ ማስጣሏን ሰማች፡፡ በዚህ ጊዜ ቀድሞውኑ ንግስቲቱ መሃን መሆኗን ሰምታ ስለነበረ ለማኟ ሴት ወደ ቤተመንግስቱ ሄደች፡፡ እናም ወደ ቤተመንግስቱ ሄዳ ልጇን ልትፈልገው ወደቦታው ስትቃረብ ብዙ ደስታና ጭፈራ እንዲሁም ዘፈንና እልልታው ቀልጦ ነበር፡፡ እርሷም ጠጋ ብላ “ይቅርታ፣ ልጄን ያየ ሰው አለ?” ብላ ጠየቀች፡፡
እዚያ የነበሩትም አገልጋዮች “ስላንቺ ልጅ ምን አገባን? ንግስቲቱ ወልዳለች፣ ንግስቲቱ ልዑል ስለወለደች ሰው ሁሉ በጣም፣ በጣም፣ በጣም ደስ ብሎት ደስታውን እየገለፀ ነው፡፡ ስለ አንዲት ደሃ ለማኝ ልጅ ማን ግድ አለው? ይልቁንስ ወደ ውስጥ ገብተሽ መብልና ጭፈራውን ተቀላቀይ፡፡ ስላንቺ ልጅ እኛ አያገባንም፡፡” አሏት፡፡
ነገር ግን ለማኟ ሴት በጣም ሰግታ በአካባቢው እየዞረች “ፊክዎ ፊኪቾ፣ የእኔ መፋቂያ ልጅ፣ ጨርቅ ውስጥ እደብቅህ የነበርኩት ልጄ የት ነህ? እዚህ አካባቢ ነህ? በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ያሳደኩት ልጄ የታለ?” እያለች መዝፈን ጀመረች፡፡
በዚህ ጊዜ ልጁ ከቤተመንግስቱ ውስጥ “ውድ እናቴ ሆይ፣ አሁን በወፍራም ልብስ ተጠቅልያለሁ፡፡ ወዳንቺ እንዳልመጣ የለበስኩት ልብስ ተጭኖኛልና ምን ባደርግ ይሻላል?” እያለ መዝፈን ጀመረ፡፡ (ልብሱ ቡልኮ የተባለው ወፍራም ጋቢ ነበር፡፡)
የልጇንም ድምጽ በሰማች ጊዜ ለማኟ ሴት በጣም ተደስታ ወደ ቤተ መንግስቱ ሮጣ በመግባት ልጇን ይዛ ስትወጣ ትልቅ ብጥብጥ ተፈጠረ፡፡
ንጉሱም “ምንድነው? ምን እየተፈጠረ ነው?” ብሎ በመጠየቅ ምን እንደተከሰተ ለማወቅ ሞከረ፡፡
ለማኟም ሴት “ጌታዬ ሆይ! አለቃዬ ሆይ! እኔ በአንዲት ትንሽ ጎጆዬ ውስጥ የምኖር ደሃና ለማኝ ሴት ነበርኩ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አንተን በመንገድ ላይ አግኝቼህ መፋቂያ ብትሰጠኝ መፋቂያውን ወደ ቤቴ ወስጄ አስቀምጬው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወንድ ልጅ አርግዤ ወለድኩ፡፡ ልጁንም ተመልከተው፡፡” አለችው፡፡
ልጁንም በተመለከቱ ጊዜ ልጁ አሁን የተወለደ ህፃን ሳይሆን ትልቅ ልጅ ነበር፡፡
ለማኟም ሴትዮ ንግግሯን በመቀጠል “የእኔ ንጉስ ሆይ! እንደሚታየው ይህ ልጅ የእኔ ሆኖ ሳለ ንግስቲቱ ሰርቃብኝ ወደ እዚህ ስላመጣችው ልጄን ልወስድ ነው የመጣሁት፡፡” አለች፡፡
ንጉሱም በለማኟ ሴት ታማኝነት በጣም ሲገረም በአንፃሩ ልጅ ወለድኩ ብላ ልታታልለው በሞከረችው ንግስት በጣም ተበሳጨ፡፡ ስለዚህ ንግስቲቱን ገድሎ ለማኟን ሴት በማግባት ልጇ አልጋ ወራሽ ሆኖ አብረው በደስታ ይኖሩ ጀመር፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|