አይጥና ጅግራ
በአበበ ከበደ የተተረከ
በአንድ ወቅት በጫካ ውስጥ ትኖር የነበረ አንዲት ጅግራ ነበረች፡፡ ጅግራዋም በሰማይና በምድር የሚኖሩ ጠላቶች ነበሩዋት፡፡ ከሰማይ ጭልፊቶችና ንስሮች ወደ ምድር ወርደው እርሷንና ጫጩቶቿን መብላት ሲፈልጉ በምድር ካሉት ደግሞ ጅቦችና ሌሎች የተለያዩ እንስሳት ሊበሏት ይቋምጡ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት እጅግ በጣም ትጠነቀቅ ነበር፡፡
እናም ይህች ጅግራ ብዙ ጫጩቶች ነበሯትና እርሷ ጥራጥሬ ፍለጋ ስትሄድ ጫጩቶቿ በጫካው ውስጥ እንዴት መደበቅ እንዳለባቸው ታስተምራቸው ነበር፡፡ እርሷ በማትኖርበት ጊዜ እንዳይወጡና እንዲደበቁ ትነግራቸዋለች፡፡
ከሄደችበት ስትመለስም ጫጩቶቿን የምትጠራበት ልዩ ድምፅ ነበራትና ትንሽ አሽካክታ “ልጆች ሆይ! በዚህ በችግር ጊዜ ጥሬ ለቀማ የምሄደው እናንተን ለመመገብ አይደለም? የት ናችሁ?” ትላቸዋለች፡፡
ጫጩቶቹም በህፃን ድምፃቸው “ሰዎች ቢጠሩንም ተደብቀን ቆየን፣ ንፋስም ሲነፍስ ተደብቀን ቆየን፣ አሁን ግን አንቺ እናታችን ስትመጪ ካለንበት ወጣን፡፡” ይሏታል፡፡
ታዲያ አንድ ሁልጊዜ ጫጩቶቹን መብላት ቢፈልግም ሊያገኛቸው ያልቻለ ጅብ ከእለታት አንድ ቀን ወደ ጅግራዋ ሄዶ ጓደኛዋ በመምሰል ካቀረባት በኋላ “እባክሽ ያንቺን ቋንቋ አስተምሪኝ፡፡ እንዳንቺ መናገር እፈልጋለሁ፡፡” አላት፡፡
እርሷም የምታሽካካበትን አኳኋን አስተማረችው፡፡
በሚቀጥለውም ቀን ጅቡ ጫጩቶቹ ወደተደበቁበት ስፍራ ሄዶ በጎርናና ድምጹ “ልጆቼ ሆይ! ጥራጥሬ ስፈልግ የምውለው ለማን ሆነና ነው? በአስቸጋሪ ሁኔታስ ያሳደኩት ማንን ነው? የት ነው ያላችሁት ልጆቼ?” ብሎ ተጣራ፡፡
ጫጩቶቹ ግን ይህ የእናታቸው ድምጽ እንዳልሆነ ስለገባቸው ከተደበቁበት አልወጡም፡፡
በሚቀጥለውም ቀን ጅቡ ተመልሶ መጥቶ የእናታቸውን ድምጽ አስመስሎ “ልጆቼ ሆይ፣ የት ናችሁ? ጥራጥሬ ስፈልግ የዋልኩት ለእናንተ ነው፣ በዚህ በችግር ጊዜ ላሳድጋችሁ ነው የምጥረው፡፡ የት ናችሁ የእኔ ጫጩቶች?” ብሎ ጠራቸው፡፡
ጫጩቶቹም እናታቸው መስላቸው ከተደበቁበት ሲወጡ ጅቡ ሁሉንም ይዞ በላቸው፡፡ ከዚያም እናታቸውንም ሊበላት ቁጭ ብሎ ይጠብቃት ጀመር፡፡
ቁጭ ብሎ ሲጠብቅ፣ሲጠብቅ ውሎ በመጨረሻ ጅግራዋ ስትመጣ ዘሎ ሊይዛት ሲል ጅግራዋ በጣም ፈጣን ስለሆነች ሮጣ አመለጠችው፡፡ ጅቡ ሲያባርራት፣ ጅግራዋ ስትሮጥ፣ ጅቡ ሲያባርራት፣ እርሷ ስትሮጥ፣ ሮጣ፣ ሮጣ ሮጣ አንዲት የእንሰት ግንድ ትፍቅ የነበረች ሴት ዘንድ ደረሰች፡፡
ሴትየዋንም “እባክሽ ጅቡ ሊበላኝ ነውና አድኚኝ፡፡ እባክሽ ደብቂኝ፡፡” ብላ ተማፀነቻት፡፡
ሴትየዋም “እሺ፣ በይ እዚያ ሄደሽ ከእቃዎቹ ስር ተደበቂ፡፡” አለቻትና ጅግራዋም ተደበቀች፡፡
ከጥቂት ደቂቃዎችም በኋላ ጅቡ እየሮጠና እያለከለከ ደርሶ “አድምጪኝ አንቺ ሴት፣ አድምጪኝ፣ ጅግራዋን አይተሻታል?” ብሎ ጠየቃት፡፡
ሴትየዋም “አላየኋትም፡፡” ብላ ስትመልስ ጅቡ አሁንም “አንቺ ሴትዮ አድምጪኝ፡፡ ጅግራዋን የት እንዳየሻት ካልነገርሽኝ አንቺኑ ነው የምጎርስሽ፡፡ ቆረጣጥሜ ሳልውጥሽ ጅግራዋ የት እንዳለች ብትነግሪኝ ይሻልሻል፡፡” ብሎ አፈጠጠባት፡፡
በዚህ ጊዜ ሴትየዋ “እኔንማ ከምትጎዳኝ አንዲት ጅግራ እነዚያ ማሰሮዎች ስር ተደብቃልሃለች፡፡” አለችው፡፡
ጅግራዋም ይህን ስትሰማ ከተደበቀችበት ወጥታ ስትሮጥ ጅቡ ማባረሩን ቀጠለ፡፡ ሲያባርራት፣ ሲያባርራት ቆይቶ በመጨረሻ እህል እየወቃ የነበረ አንድ አይጥ ዘንድ ደርሳ “አያ አይጥ ሆይ እባክህ አድነኝ፡፡ ጅቡ ሊበላኝ ነውና ካዳንከኝ ሚስት እሆንሃለሁ፣ ልታገባኝም ትችላለህ፡፡” አለችው፡፡
አይጡም “እሺ፡፡ እንግዲያው አንቺ ተደበቂና ጅቡ ሲመጣ እኔ እመልስለታለሁ፡፡” አላት፡፡
ከጥቂት ደቂቃዎችም በኋላ ጅቡ ሲሮጥ መጥቶ “አንተ ትንሽ አይጥ! ጅግራዬን አይተሃታል?” አለው፡፡
አይጡ ግን ዝም ብሎ ስራውን ቀጠለ፡፡
ጅቡም አጓርቶ “አንተ ትንሽ አይጥ! ጅግራዬን አይተሃታል?” ብሎ በጩኸት ጠየቀው፡፡
አይጡም “እኔ ያንተ ጅግራ ጠባቂ ነኝ? ጅግራህን የምጠብቅልህ ይመስልሃል?” ብሎ ለራሱ እያጉተመተመ ስራውን ቀጠለ፡፡ መውቃቱንም በርትቶ ቀጠለ፡፡
በዚህ ጊዜ ጅቡ “አዳምጥ አንተ አይጥ፣ ብትጠነቀቅ ይሻልሃል፤ ካልነገርከኝ አንተኑ ነው የምውጥህ፡፡” አለው፡፡
አይጡ ግን አሁንም ዝም ብሎ ስራውን መስራት ቀጠለ፡፡ በዚህ ጊዜ በአይጡ ሁኔታ የተበሳጨው ጅብ ዘሎ አይጡን ይዞ ዋጠው፡፡ ሆኖም ትንሹ አይጥ በጅቡ ፊንጢጣ በኩል ሲወጣ አሁንም ጅቡ ዋጠው፡፡ አሁንም አይጡ በጅቡ ፊንጢጣ በኩል ወጣ፡፡ ይህ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተደጋግሞ ሲከሰት ጅቡ በጣም፣ በጣም ስለተናደደ አይጡ እንዳያመልጥ ጅቡ የራሱን ፊንጢጣ ለመስፋት ወሰነ፡፡
በዚህ ጊዜ ግን አይጡ ወደ አንድ ቀጥቃጭ ዘንድ ሄዶ አንድ የሰላ ምላጭ ገዝቶ መጣ፡፡ ጅቡም መጥቶ ትንሹን አይጥ ሲውጠው አይጡ ምላጩን ይዞ የጅቡ ሆድ ውስጥ ስለገባ የጅቡን አንጀት ይበጣጥሰው ጀመር፡፡
ታዲያ ይህ ሲሆን ጅቡ “አንተ ትንሽ አይጥ ና ውጣ፣ ና ውጣ፣ ከእንግዲህም አልፈልግህም፡፡” አለው፡፡
አይጡም “እንዴት አድርጌ ነው የምወጣው? በአንዱ በኩል ተሰፍቷል በሌላው በኩል ደግሞ ሃይለኛ ዳገት ስለሆነ ዳገቱን መውጣት አልችልም፡፡” አለው፡፡
ጅቡ “አይሆንም! እያመመኝ ነው! እያመመኝ ነው!” እያለ መጮህ ጀመረ፡፡
አይጡም አንጀቱን መበጣጠስ ቀጠለ፡፡
ጅቡም “ያማል አንተ አይጥ! እውስጤ እንድትቆይ አልፈልግምና ና ውጣ፡፡” ማለቱን ቀጠለ፡፡
አይጡም “በየትኛው በኩል ነው መውጣት ያለብኝ? አንደኛው ጫፍ ተሰፍቷል፣ ሌላኛው ደግሞ አቀበታማ ዳገት ስለሆነ መውጣት አልችልም፡፡” ይለዋል፡፡
ሸርከት፣ ሸርከት፣ ሸርከት በማድረግ በመጨረሻ በጅቡ ጨጓራ በኩል አይጡ ቀዶ ሲወጣ ጀቡ ወድቆ ሞተ፡፡
እናም በስምምነታቸው መሰረት አይጡ ጅግራዋን አግብቶ እንዲህ አላት፣ “አንቺ ወደቤቱ ውስጥ ገብተሽ ገንፎ ስትሰሪልኝ እኔ ደግሞ ፀሃይ ውስጥ ቁጭ ብዬ ሰውነቴን በቅቤ እታሻለሁ፡፡ ምክንያቱም ጎበዝ ታጋዮች ከታላቅ ግዳይ በኋላ እንደዚህ ነው የሚያደርጉትና፡፡” አላት፡፡
ይህንንም ካለ በኋላ ፀሀይ ውስጥ ተቀምጦ ሰውነቱን ሁሉ በቅቤ ይታሽ ጀመር፡፡ ማቅራራትና የድል ዜማንም ማንጎራጎር ጀመረ፡፡
በዚህ ጊዜ አንዲት ጭልፊት በአካባቢው በሰማይ ላይ ስታልፍ አይጡ ፀሀይ ውስጥ ቁጭ ብሎ ሲያቅራራ አይታው አንድ ጊዜ ወርዳ መንትፋው ሄደች፡፡
አይጡም “አያ ጭልፊት ሆይ ስማ! እንደኔ ያሉ አይጦች በሜዳ ላይ ከበላህ በጣም መጥፎ ነው፡፡ እኛ መበላት ያለብን በትልልቅ ቁጥቋጦዎች ውስጥ ወይም ብዙ ቅርንጫፎች ባሉት ዛፍ ላይ ነው፡፡” አላት፡፡
ጭልፊቷም “እንደዚያ ነው?” ብላ ወደ አንድ ትልቅና ብዙ ቅርንጫፎች ወዳሉት ዛፍ ይዛው ስትሄድ አይጡ ሾልኮ አምልጦ ወደ ሚስቱ ሮጦ ሄደ፡፡ አሁንም አይጡ ፀሃይ ላይ ቁጭ ብሎ በቅቤ እየታሸ የጀግንነት ዘፈኑን መዝፈኑን ቀጠለ፡፡ ምክንያቱም አሁን ጅብ ከመግደሉም በላይ ጭልፊቷን አታሏታልና፡፡
ሆኖም ሁለተኛው ጭልፊት አሁንም መጥቶ ጠልፎት ሄደ፡፡ አይጡም “አያ ጭልፊት ሆይ! እንደኔ ያሉ አይጦች ሜዳ ላይ ስንበላ ብዙ ችግር እናመጣለንና በድንጋዮች ላይ ነው መበላት ያለብን፡፡” አለው፡፡
ጭልፊቱም “እንደዚያ ነው?” ብሎ ወደ አንድ ድንጋያማ ቦታ ይዞት ሲሄድ አይጡ አሁንም አምልጦ ወደ ቤቱ እየሮጠ ተመለሰ፡፡ አሁንም በድጋሚ ፀሃይ ላይ ተቀምጦ ቅቤ ሲቀባ ጅግራዋ ተጣርታ “ገንፎው ደርሷል፣ ማሰሮው ውስጥ ነው፡፡” አለችው፡፡
አይጡም “አሃ ነው እንዴ?” ብሎ እየሮጠ በመሄድ “ገንፎው በቂ ነው? በቂ እህል ጨምረሽበታል?” ብሎ ጠየቀ፡፡
የገንፎውንም መጠን አጮልቆ ለማየት አንገቱን ወደ ማሰሮው ለማስገባት ሲያጎነብስ በድንገት አንሸራቶት ማሰሮው ውስጥ በመግባቱ የፈላው ውሃ ውስጥ ገብቶ ሞተ፡፡
ይህም ታሪክ የሚያሳየን አንድ ታላቅ ጀግና ከብዙ አደጋዎች ካመለጠ በኋላ በትንሽና ባልተጠበቀ ነገር ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|