ቀበሮና ቁራ
በአበበ ከበደ የተተረከ
ከእለታት አንድ ቀን አንድ ቀበሮ በጉዞ ላይ እያለ የሚበላው ነገር በማጣቱ በጣም ይርበውና ግራና ቀኙን ሲመለከትም የሚበላው አጥቶ አፉ ደርቆ ክፉኛ ተርቦ የሚበላው በአካባቢው ያጣል፡፡
ታዲያ ድንገት ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ሲመለከት አንድ አሞራ አንድ ትልቅ ሙዳ ስጋ ይዞ ሲበር አይቶ ያንን ስጋ መብላት አለብኝ ብሎ ወሰነ፡፡
“አያ አሞራ፣ እንደምን አደርክ? ደህና ነህ?” ብሎ ተጣራ፡፡ አሞራው ግን የሰማውን ብቻ ሰምቶ ዝም አለ፡፡
አሁንም ቀበሮው “አሞራ፣አሞራ ሆይ፣ ስፈልግህ ነበር እኮ!” ቢለውም አሞራው አሁንም ዝም አለ፡፡
ቀበሮው ልፍለፋውን በመቀጠል “ዛሬ ምን እንደተከሰተ ታውቃለህ? ሁሉም እንስሳት ተሰባስበው አንድ ጌታ ሊኖራቸው እንደሚፈልጉና ንጉስ መሾም እንዳለበት ተስማምተው የተለያዩ ሰዎችን በማሰብ እንስሳቱ ሁሉ ተሰብስበው የተለያዩ እንስሳትንና አእዋፋትን በእጩነት ካቀረቡ በኋላ ሁሉም የራሱን አስተያየት ሰጥቶ ሲያበቃ በመጨረሻ አንተን መርጠውሃል፡፡ አንተም በጣም ጥቁር በመሆንህ በጣም ቆንጆ ነህ ብለው ወደውሃል፡፡ በአናትህ ላይ ያለውም ነጭ ፀጉር ለዘውዱ ማረፊያ ተስማሚ ነው ብለዋል፡፡ ሁሉም በምርጫው ተደስተው በሙሉ ድምጽ ነው ያንተን መመረጥ ያፀደቁት፡፡ ነገር ግን አንድ ችግር ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች ምናልባት ድምጽህ ያማረ ላይሆንና ጥሩ ቅላፄ ላይኖረው ስለሚችል ለንጉስነት ላይበቃ ይችላል ብለው ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሆኖም ሁሉም እርግጠኛ ባለመሆናቸው እኔን ወክለው ወዳንተ ስለላኩኝ ወደ ቤትህ ለመምጣት በመንገድ ላይ ሳለሁ ነው አሁን እንዳጋጣሚ ያገኘሁህ፡፡ ስለዚህ ምን ዓይነት ድምፅ እንዳለህ መስማት እፈልጋለሁ፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ቁራው የእንስሳቱ ሁሉ መሪና አለቃ ሆኖ በመመረጡ ደስታው ከልክ ያለፈ ሆነ፡፡ ለቀበሮውም ምን አይነት ጣፋጭ ድምፅ እንዳለው ሊያሰማው አፉን ከፍቶ “አርክ! አርክ! አርክ!” እያለ መጮህ ጀመረ፡፡
አፉን ከፍቶ መጮህ ሲጀምር በአፉ ይዞት የነበረው ሙዳ ስጋ ወደ መሬት ወደቀ፡፡ ቀበሮውም በፍጥነት ስጋውን መንትፎ መሮጥ ጀመረ፡፡
ከዚያም አሞራውን “አንተ ቆሻሻ ጥቁር ሰይጣን! ማን አባክ አንተን ጌታ አድርጎ ይመርጣል? እንኳን ጌታ ልትሆን ይቅርና ሰዎች ባሪያቸውም እንድትሆን አይፈልጉም፡፡” ብሎት ሮጦ ሄደ ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|