ተኩላ፣ቀበሮና ጥንቸል
በአበበ ከበደ የተተረከ
በአንድ ወቅት ተኩላ፣ ቀበሮና ጥንቸል አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ጥሩ ጓደኛሞች ስለነበሩ መልካም ቡድን ፈጥረው ነበር፡፡
ሆኖም እንደሚታወቀው ተኩላና ቀበሮ ስጋ በል እንስሳት ሲሆኑ ጥንቸል ሳር በል እንስሳ ነውና በተፈጥሮአቸው ልዩነት ነበራቸው፡፡ ስለዚህ ተኩላውና ቀበሮው የተሻለ መግባባት ቢኖራቸውም ጥንቸሉ ፈጣንና ነገሮችን በቶሎ ማድረግ ስለሚችል ይወዱት ነበር፡፡
ታዲያ ጊዜ እያለፈ ሲሄድና ተኩላውና ቀበሮው ጥንቸሉን በጣም እየተላመዱት ሲሄዱ ሊበሉት ፈለጉ፡፡ ለስላሳና ጣፋጭ እንደሆነም ተስማሙ፡፡
በውይይታቸውም “ልንገነጣጥለውም እንችላለን፡፡ አንተ አንድ እግሩን ስትይዝ እኔ ሌላውን ይዤ በቀላሉ በመገነጣጠል ልንበላው እንችላለን፡፡ በመጠን ትንሽ ስለሆነ ለምሳ የሚበቃም ባይሆን ለቅምሻ ወይም ለቁርስ ይሆነናል፡፡” ብለው በመስማማት ጥንቸሉ ከሄደበት ሲመለስ ሊበሉት ወሰኑ፡፡
ነገር ግን ጥንቸሉ በጣም ብልህ ነበርና ተመልሶ ሲመጣ ተኩላው ጥርሱን ሲያፋጭ ስለሰማው ጥርጣሬ አድሮበት በሩቅ ሆኖ “ምን ሆናችኋል?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡
እነርሱም “ምንም፣ ምንም፣ ምንም ችግር የለም፡፡” አሉት፡፡ ጥንቸሉ ግን እንዳይዙት ራሱን ከእነርሱ ቀስ እያለ ማሸሽ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ቀበሮውና ተኩላው ትንሽ በስጨት ብለው “ከዚህ በኋላ እንደበፊቱ ስለማይቀርበን ቀስ ብለን ልናታልለው ይገባናል፡፡” አሉ፡፡
በጉዳዩም ላይ ለተወሰነ ጊዜ ከተወያዩበት በኋላ አንድ ዘዴ ፈጠሩ፡፡ በእቅዱም መሰረት ተኩላው በጠና የታመመ በመምሰል ወደ ቤቱ ሄዶ ሲተኛ ቀበሮው ጥንቸሉን ልኮ እንዲጠይቀው ማድረግ ነበር፡፡ ከዚያም ጥንቸሉ ሊጠይቀው ሲሄድ ተኩላው በቀላሉ ሊይዘው ይችላል፡፡
እናም በተነጋገሩት መሰረት ተኩላው ወደቤቱ ሄዶ አይኖቹን ጨፍኖና አፉን ዘግቶ በመተኛት አልፎ አልፎ ቀስ ብሎ እያጮለቀ የጥንቸሉን መምጣት መጠባበቅ ጀመረ፡፡
በሌላ በኩል ቀበሮው ወደ መስኩ በመሄድ ጥንቸሉ እስኪመጣ ጠብቆ ጥንቸሉ ሲመጣ ቀበሮው “አያ ጥንቸል፣ ወሬውን ሰማህ እንዴ?” አለው፡፡
ጥንቸሉም “አልሰማሁም፣ ምን ተከሰተ?” አለ፡፡
ቀበሮውም “ምን እባክህ ጓደኛችን አያ ተኩላ በጠና ታሟል፡፡ ሳይሞት ባለመጠየቅህ ሲቆጭህ ትኖራለህና አሁን ሄደህ ከመሞቱ በፊት ብታየው ይሻላል፡፡” አለው፡፡
ጥንቸሉም “እውነት ብለሃል ብሎ በጥርጣሬ ወደ ተኩላው ቤት አመራ፡፡ ታዲያ ተኩላው እያጮለቀ ያይ ስለነበረ የአይኑ ሽፋሽፍት ይርገበገቡ ነበር፡፡ ጥንቸሉም በጣም ሳይጠጋ አይኑን አፍጥጦ ቢመለከትም ምንም ነገር መስማት አልቻለም፡፡ አስተውሎ ሲመለከትም ተኩላው እያጮለቀ መሆኑንና አፉንም አጥብቆ እንደገጠመው አየ፡፡
ጥንቸሉ እንዴት ማምለጥ እንዳለበት ግራ ገብቶት ጥቂት አሰብ ካደረገ በኋላ “ያምላክ ያለህ! ይህ ተኩላ በፍፁም የሞተ አይመስልም፡፡ ተኩላዎች ሲሞቱ አይናቸው በቶሎ ሲከደን አፋቸው ግን ይከፈታል፡፡” አለ፡፡
ተኩላውም ይህን በሰማ ጊዜ ቀስ ብሎ አይኖቹን አጥብቆ በመጨፈን አፉን ከፈት አደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ የተኩላው አይኖች መጨፈናቸውን ሲያይ ጥንቸሉ ሳይታይ ሮጦ አመለጠ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎችም በኋላ ቀበሮው እስካሁን ተኩላው ጥንቸሉን ይገድለዋል ብሎ አስቦ ምግቡን ለመካፈል ወደ ተኩላው ዘንድ አመራ፡፡ ነገር ግን ተኩላው ዘንድ በደረሰ ጊዜ ተኩላው ብቻውን ተበሳጭቶ ከአልጋው ጋር እየተላተመ አገኘው፡፡
ቀበሮውም “ምን ሆነሃል?” ብሎ ሲጠይቀው “ጥንቸሉ እኮ አመለጠኝ፡፡” አለው፡፡
ከዚያን እለት ጀምሮ የሶስቱ ጓደኝነት አብቅቶ ተኩላና ቀበሮ ጥንቸልን በማሳደድ ሊይዟት ሲሞክሩ ይኖራሉ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|