ንግስት ፉራ
በአበበ ከበደ የተተረከ
ንግስት ፉራ ስመጥር የሲዳማ ንግስት የነበረች ሲሆን ሴቶችን ሁሉ መልካም ባህሪን ያስተማረችና እስካሁንም ድረስ ተቀባይነት ያላት ሴት ነች፡፡ ንግስቲቱ በጣም ብልህ ነበረች፡፡ በቅድሚያ ሴቶች ለወንዶች ሙሉ ለሙሉ ተገዢ እንዳይሆኑ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሴቶች ለወንዶች ሙሉ ለሙሉ ታዛዥ እንዳይሆኑ ትመክራቸው ነበር፡፡ ከዚያም በላይ ሴቶች አይን አፋር እንዲሆኑና ወንዶች እነርሱ ስለሚያስቡት ነገር ሁልጊዜም ግምታዊ እንጂ ግልፅ እንዳይሆን ታስተምራቸው ነበር፡፡ ሃፍረተ ገላቸውንም በአደባባይ እንዳያሳዩና ሰውነታቸውንም ከጉልበታቸው እስከ ወገባቸው ድረስ እንዲሸፍኑ ትነግራቸው ነበር፡፡ ወንዶች በውበት ስለሚማረኩ ሴቶች ራሳቸውን በደንብ እንዲጠብቁ ታስተምራቸው ነበር፡፡
ነገር ግን ንግስት ፉራ ለወንዶች በጣም መጥፎ ሴት ነበረች፡፡ የማይቻሉ ነገሮችን ሁሉ እንዲሰሩ ታዛቸው ነበር፡፡
“ወደ ወንዙ ሄደህ ውሃ በወንፊት አምጣ፡፡” እያለች ታዝ ነበር፡፡ ወይም በጣም ስስ ከሆነ ሳር ትልልቅ ገንዳዎችን እንዲሰሩ አለያም ከረጃጅም ፀጉሮቿ አንዱን ነቅላ ስድስት ቦታ እንዲሰነጥቁት በማዘዝ ወንዶችን ታሰቃያቸው ነበር፡፡
ከሁሉ በላይ ግን ራሰ በራና አጭር ወንዶችን አጥብቃ ትጠላ ነበር፡፡ ስለዚህ አጫጭር እንዲሁም ራሰ በራ ሰዎችን ሁሉ እንዲገደሉ ታዝ ነበር፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አጫጭርና ራሰ በራ ሰዎች ሲገደሉ አንድ መላጣና አንድ ራሰ በራ ወንዶች ግን ከዚህ ችግር ተርፈው ነበር፡፡ አጭሩ ሰው ረጃጅም ተረከዝ ያሏቸው ጫማዎች በማድረግ ሲተርፍ (ረጅም ተረከዝን የፈጠረው እርሱ ነው) ራሰ በራው ሰው ደግሞ ሰው ሰራሽ ጸጉር (ዊግ) በማድረግ ከሞት ዳነ፡፡ (ዊግን የፈጠረው ሰው እርሱ ነው፡፡)
ታዲያ አጭሩና ራሰ በራው ሰዎች ንግስቲቱን ምን እንደሚያደርጓት ግራ ገብቷቸው ነበር፡፡ ሊገድሏትም አሰቡ፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ ሁለት ግዙፍ ችግሮች ነበሩት፡፡ የመጀመሪያው በባህሉ መሰረት ሴትን መግደል በፍፁም ነውር ነው፡፡ ሁለኛው ደግሞ እርሷ ንግስት ስለነበረች ይህ የማይሆን በመሆኑ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተቸገሩ፡፡
ከዚያም ጥቂት ካሰቡ በኋላ አንድ ዘዴ ዘየዱ፡፡ አንድ ቀጭኔ ለመያዝ አስበው ቀጭኔዎቹን ሁሉ እያሳደዱ ወደ ረግረጋማው ስፍራ ከነዷቸው በኋላ አንዱ በጭቃው ተይዞ ሲቀር እርሱን ያዙት፡፡
ንግስቲቱንም ጠርተው “አንቺ ታላቅ ንግስት ነሽ፡፡ አንቺ መሳፈር ያለብሽ ተራውን እንስሳ ሳይሆን ረጅምና ሞገስ ያለውን እንስሳ ነው፡፡” አሏት፡፡
ከዚያም በሰአቱ ቀጭኔው እግሩ ጭቃው ውስጥ ዘልቆ ስለነበረ ንግስቲቱ ያለችግር ተሳፈረችው፡፡ ከዚያም ንግስቲቱን ቀጭኔው ላይ አስረዋት ቀጭኔውን ከጭቃው ካወጡ በኋላ ሲያባርሩት ቀጭኔው ሲሮጥ፣ ሲሮጥ፣ ሲሮጥ፣ ንግስቲቱ እየተቆራረጠች መውደቅ ጀመረች፡፡ ጭንቅላቷ ወደ አንድ ቦታ፣ እጆቿ ወደ ሌላ ቦታ፣ አንጀቷ ወደ አንድ አቅጣጫ፣ እግሮቿ ወደ ሌላ ስፍራ ተበጣጥሰው ወደቁ፡፡
በዚህ ምክንያት ነው እስከ ዛሬ ድረስ ሲዳማ ውስጥ ጭንቅላት፣ እግር፣ ሰውነት፣ አንጀት፣ እጅ የሚባሉ የከተማ ስሞች ያሉት፡፡
አኦውን፣ ጭንቅላት፤ ጎዱቦሬ፣ አንጀት፤ ሌላ፣ እግር፤ አንጋ፣ እጅ ማለት ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|