ጦጣ፣ ዝንጀሮና አንበሳ
በአበበ ከበደ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንበሳ፣ ዝንጀሮና ጦጣ በአንድ ቤት ውስጥ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ አብረውም በደስታ እየኖሩ ስራቸውን ተከፋፍለው ይሰሩ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው አንበሳው የቤቱ ጌታ ስለነበረ በጌታነቱ ቤቱን የመጠበቅ ኃላፊነት ነበረበትና ወደ ጫካ በመሄድ እያደነ የቤቱን ጠቅላላ ጉዳዮች እንደጌታነቱ ያከናውን ነበር፡፡ በሌላ በኩል ዝንጀሮው ቤት ጠባቂ በመሆን ቤቱን የማፅዳትና የመሳሰሉትን ስራዎች በሃላፊነት ይወጣ ነበረ፡፡ ጦጣው ግን አትክልተኛ በመሆን ከቤት ውጪ ያሉትን ስራዎች ማለትም ዛፍ ላይ በመውጣት ሰብሉን እየጠበቀ ከቤት ውጪ ያሉትን የመላላክ ስራዎች ይሰራ ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንበሳው፣ ዝንጀሮውና ጦጣው አንድ ላም በጋራ ስለነበረቻቸው በየተራ ይንከባከቧት ነበር፡፡ ላሚቷን ወደ መስክ ወስዶ በቂ ግጦሽ እንድታገኝ የማድረጉ ኃላፊነት የጦጣው ሲሆን ዝንጀሮው ደግሞ ላሟን እቤት ውስጥ በማሰርና በመንከባከብ የራሱን ሃላፊነት ይወጣል፡፡ አንበሳው ደግሞ ላሟን የማለቡን ስራ ይሰራል፡፡
በምግብ ሰአት ደግሞ ጦጣው በጣም ፈጣንና ቀልጣፋ ስለሆነ አንበሳው ጠረጴዛው ጋ ሲቀመጥ ምግብ የሚያቀርበው ጦጣው ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ጦጣው አንበሳው ጋ ሄዶ “ጌታዬ ሆይ፣ አንድ ነገር እየጠረጠርኩ ነው፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው “ምንድነው?” ብሎ ሲጠይቀው ጦጣው “አንተ ላሚቷን ታልባታለህ፡፡ ሆኖም በሚቀጥለው ቀን ወተቱን ላንተ ሳቀርብልህ አንተ ካለብከው መጠን ያነሰ ይመስለኛል፡፡” አለው፡፡
አንበሳውም “እውነትህን ነው? ታዲያ ወተቱ ምን እየሆነ ይመስልሃል?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ጦጣውም “ጌታዬ ይታይህ! አንተ ለአደን ወደ ጫካ ስትሄድ እኔም ሰብሉን ለመጠበቅ ስወጣ ዝንጀሮው የተወሰነውን ወተት ሳይጠጣ አይቀርም፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው ተቆጥቶ “ያ አስቀያሚ ዝንጀሮ! ይህን ቢያደርግ አይገርመኝም፡፡ ልቀጣውም ይገባል፡፡” ብሎ ጮኸ፡፡
ከዚያም ዝንጀሮውን ጠርቶ “አዳምጥ አያ ዝንጀሮ፣ ታዲያ ምን ትላለህ?” አለው፡፡
ዝንጀሮውም “ስለ ምኑ ጌታዬ?” አለው፡፡
“ላሚቷን ማታ ማታ የማልባት እንግዲህ እኔ ነኝ፡፡ እናም በማግስቱ ቀን ወተቱን ስመለከተው መጠኑ ቀድሞ ካለብኩት ያንሳል፡፡”
ዝንጀሮውም “ኧረ እኔ ስለዚህ የማውቀው ነገር የለም! ምናልባት ግን፣ እንዲያው ምናልባት ምግብ ለማብሰያ የሚሆን ውሃ ልቀዳ ወደ ወንዝ ስወርድ ጦጣው መጥቶ ትንሽ ይጠጣ ይሆናል፡፡” አለ፡፡
አንበሳውም “አንተ ቆሻሻ አስቀያሚ ባለጌ! ወተቱን ራስህ ጠጥተህ ስታበቃ ምስኪኑን ጦጣ ልትኮንነው ነው? እንግዲያውማ ልቀጣህ ይገባል፡፡ የዚህ ቤት ጌታና አለቃ አንደመሆኔ መጠን አገልጋዮቼን መቅጣት ይገባኛል፡፡” ብሎ ዝንጀሮውን ወደ ውጪ ይዞት ወጥቶ ከዛፉ ግንድ ላይ በማሰር “እንደ ቅጣት ይሆንህ ዘንድ እዚህ ዛፍ ላይ ታስረህ ትቆያለህ፡፡” አለው፡፡
እናም ምስኪኑ ዝንጀሮ በዛፉ ግንድ ላይ ታስሮ በሚያቃጥለው ፀሃይ እየተለበለበ ሲውል በሙቀቱ ንዳድ እያረረ እጅግ በጣም ተጎሳቁሎ ከዚህ ሁሉ ሴራ ጀርባ ያለው ጦጣው እንደሆነ ስላወቀ በጣም ተናደደበት፡፡ ቀን ፀሃዩ ሲያቃጥለው ይውልና ማታ ደግሞ ብርዱ እያንገበገበው በጭለማው ውስጥ ሲንቀጠቀጥ፣ ሲንቀጠቀጥ ቆይቶ በድንገት ከጭለማው ውስጥ አንድ ጅብ መጥቶ “ አያ ዝንጀሮ፣ ምን እያደረክ ነው?” አለው፡፡
ዝንጀሮውም “እባክህ እየተቀጣሁ ነው፡፡ በጣም ከባድ ነው! ቀን በጸሃዩ ሙቀት ስቃጠል ውዬ አሁን ደግሞ በሌሊቱ ብርድ እየተንዘፈዘፍኩ ነው፡፡” አለው፡፡
ጅቡም “ኧረ እባክህ? ምን ጥፋት አጥፍተህ ነው?” አለው፡፡
“በእውነት ምንም ጥፋት አላጠፋሁም፡፡”
“ነገር ግን ጌታህ ምንም ሳታጠፋ አይቀጣህም፡፡”
ዝንጀሮውም “ምንም አላጠፋሁም፡፡ እንደምታውቀው ጌታችን በጣም ደግና ቸር ስለሆነ ብዙ ምግብ እንድበላ ቢፈልግም መብላት አልቻልኩም፡፡” አለው፡፡
ጅቡም “አንተ ሞኝ! መብላት ነበረብህ፡፡” አለው፡፡ ዝንጀሮውም “አልቻልኩማ! በቃ ከዚያ በላይ መብላት አልቻልኩም፡፡” አለ፡፡
በዚህ ጊዜ ጅቡ “እንግዲያው እንዲህ ከሆነ እኔ ባንተ ቦታ ተተክቼ የፈለከውን ልበላልህ እችላለሁ፡፡” አለው፡፡
እንደሚታወቀው ጅብ የሆዱ ነገር አይሆንለትምና ዝንጀሮውን ከታሰረበት ፈቶ እራሱን ከዛፉ ላይ አሰረ፡፡ በማግስቱ ጠዋት አንበሳው የዝንጀሮው ቅጣት ይበቃል ብሎ ሊፈታው ወደ ዛፉ ሲመጣ በዝንጀሮው ቦታ ጅቡን አገኘው፡፡
አንበሳውም “እዚህ ምን እያደረክ ነው?” ብሎ ጅቡን ጠየቀው፡፡ ጅቡም “እዚህ የመጣሁት ልበላና ልጠጣ ነው፡፡” አለው፡፡
“ምን?!”
“አያ ዝንጀሮ መብላትና መጠጣት ስላልቻለ እየተቀጣ መሆኑን ሲነግረኝ በርሱ ምትክ ልበላና ልጠጣ መጣሁ፡፡”
አንበሳውም “የዝንጀሮውን ቦታ ተክተኸው ነው ማለት ነው?” ብሎ ሲጠይቀው ጅቡም “አዎ” ብሎ መለሰ፡፡
ከዚያም አንበሳው “አይመስለኝም፣ እውነታው ግን ይህ አይመስለኝም፡፡ የመጣኸው ልትበላና ልትጠጣ ነው አይደል? ነገር ግን ልትበላና ልትጠጣ የፈለከው ላሜን ነው፡፡ እንዴት ብትደፍረኝ ነው፡፡ እባክህ!” ብሎ ጅቡን ገደለው፡፡
ከዚህ በኋላ ዝንጀሮው ወደቤት ተመልሶ በጣም ታዛዥ በመሆን የአንበሳውን እምነት ለማግኘት ይጥር ጀመር፡፡ አንበሳውንም ከወትሮው በበለጠ እየተንከባከበና በላቀ የሃላፊነት መንፈስ ብዙ ስራዎችን እየሰራ መልካምነቱን ለአንበሳው ማሳየት ጀመረ፡፡
ከተወሰነ ጌዜም በኋላ ዝንጀሮው ጦጣውን መበቀል በመፈለግ አንበሳውን “አለቃዬ ሆይ! አንተ በጣም፣በጣም ጠንካራ በመሆንህ ጥንድ የቆዳ ጫማ ቢኖርህ ጥሩ ይመስለኛል፡፡” አለው፡፡
አንበሳውም “ለእኔ ጫማ?” ብሎ ሲጠይቀው “አዎ፣ አንተ ከጌቶች ሁሉ ሃያል ጌታ ነህና ጥንድ ጫማዎች ሊኖሩህ ይገባል፡፡” አለው፡፡
አንበሳውም “እንግዲያው ይህ መልካም ሃሳብ ነውና እስኪ ላስብበት፡፡” አለው፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን ጦጣው ከቤት ውጪ ቢሆንም ዝንጀሮው ምን እንዳሰበ በትክክል ያውቅ ነበር፡፡
እናም አንበሳው የጦጣውን አስተያየት ሊጠይቅ ሲሄድ ጦጣው “ጌታዬ ሆይ፣ ከመስኩ በወዲያኛው በኩል ያለውን አንበሳ ስመለከተው ነበር፡፡ ግዙፍ አንበሳ ሲሆን ቆንጆ ጫማዎችንም አድርጓል፡፡ እንዳንተ ሃያልና ትልቅ ባይሆንም ቆንጆ ጫማዎች አሉትና አንተም ቢኖርህ መልካም ነው፡፡” አለው፡፡
አንበሳም “እውነት? ምን አይነት ጫማዎች ነው ያደረገው?” አለው፡፡
ጦጣውም “ያደረገው ጫማ ከምርጥ ቆዳ የተሰራ ሲሆን ይህም ቆዳ ከዝንጀሮ ቆዳ የተገኘ ነው፡፡” አለው፡፡
አንበሳውም “እንደዚያማ ከሆነ እኛ ዝንጀሮ ስላለን ዝንጀሮውን ገድለን ቆዳውን መጠቀም እንችላለን፡፡” አለ፡፡
ጦጣውም “ይህ መልካም ሃሳብ ነው፡፡” አለ፡፡
ከዚያም አንበሳው ሄዶ ዝንጀሮውን ከገደለው በኋላ ጦጣው ቆዳውን ገፎ ሲያበቃ አንበሳው ጦጣውን “በል ና ጫማዎቹን ስፋልኝ፡፡” አለው፡፡
ሆኖም ጦጣው “ቆዳው መለስለስ ስላለበት በቅድሚያ ወደ ወንዝ ወስጄው ውሃ ውስጥ ከዘፈዘፍኩት በኋላ ቆንጆ ሆኖ ሲለሰልስ ያን ግዜ ነው ጥሩ ጥንድ ጫማዎች ልሰፋልህ የምችለው፡፡” አለው፡፡
ከዚያም ጦጣው የዝንጀሮውን ቆዳ ይዞ ወደ ወንዙ ወርዶ በጣም ጥልቅ የሆነውን የወንዙን አካል አግኝቶ የዝንጀሮውን ቆዳ ወደዚያው ጥልቅ ውሃ ውስጥ ከተተው፡፡ ከዚያም ቅርብ ወደሆነው የወንዙ ክፍል በመሄድ ራሱን ውሃው ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ከዘፈዘፈ በኋላ ወደ አንበሳው ሮጦ በመሄድ ትንፋሽ አጥሮት እያለከለከ “ጃንሆይ! ጃንሆይ!” ሲለው አንበሳውም “ምነው? ምን ሆንክ?” አለው፡፡
“ኧረ ጉድ ነው!”
“ምንድነው ጉዱ? አንተም ሙሉ ለሙሉ በውሃ ረጥበሃል፡፡ ምን ሆንክ?”
“ኧረ አስቤውም አላውቅ ነበር፡፡ ካንተ የበለጠ ጠንካራና ግዙፍ እንስሳ ያለ አይመስለኝም ነበር፡፡ ካንተ የበለጠ ግዙፍና ጠንካራ እንስሳ ሊኖር አይችልም፡፡”
አንበሳውም “ታዲያ ሌላ አለ እንዴ?” ብሎ ጠየቀ፡፡
ጦጣውም “አዎ! እንዲያውም ወንዙ ጋ ይዞኝ የዝንጀሮውን ቆዳ ወሰደብኝ፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው በጣም ተናዶ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገብቶት በመጨረሻ ሄዶ የወንዙን አንበሳ አጥቅቶ ቆዳውን ይዞ ሊመለስ ወሰነ፡፡ ከዚያም ከጦጣው ጋር ሆኖ ወደ ወንዙ ሮጦ ሲሄድ በአካባቢው ሌላ አንበሳ የለም፡፡
ቢያይ፣ ቢያይ ምንም አጥቶ ጦጣው ግን ወደታች ወርዶ ጠቆር ብሎ በጥራት ከሚያሳየውና ጥርት ካለው ውሃ ዘንድ ሄዶ አንበሳውን “ና ተመልከት ጃንሆይ! የነገርኩህ አንበሳ ያውና!” አለው፡፡
አንበሳውም ሄዶ ጥርት ብሎ የሚታየውን ውሃ ሲመለከት የራሱን ምስል ውሃው ውስጥ አየው፡፡ ጎፈሩን አንዴ በትኖ ውሃው ውስጥ ያለውን አንበሳ ለመያዝ ዘሎ ሲገባ ተደፍቆ ሞተ፡፡
በዚህ አይነት ጦጣው ሁለቱንም እንስሳት አስወግዶ ወደ ቤት በመመለስ ከላሟ ጋር በሰላም መኖር ጀመረ፡፡
ይህ የሚያሳየው ብልጥ ሰዎች ከሌሎች ያነሰ ጉልበት ቢኖራቸወም የሚፈልጉትን ነገር ማድረግ እንደሚችሉ ነው፡፡
< ወደኋላ |
---|