አንበሳውና ዝንጀሮው
በኦይታ አሮ የተተረከ
አንድ አንበሳና አንድ ዝንጀሮ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ አንበሳውም ለዝንጀሮው እንደ አባት ሆኖ አብረው ሲኖሩ ከእለታት አንድ ቀን አንበሳው ዝንጀሮውን ስጋ እንዲያመጣ ሲያዘው ዝንጀሮው ስጋ ሳይሆን በቆሎ ይዞ መጣ፡፡
አንበሳውም “እኔ ጥራጥሬ አልበላም፡፡ እኔ የምበላው ስጋ ስለሆነ ይህንን አልበላም፡፡” አለው፡፡
ዝንጀሮውም “እኔ እንዳንተ ጠንካራ አይደለሁም፡፡ እንዴት እንስሳ ላመጣልህ እችላለሁ?” ሲለው አንበሳውም “እንደምንም ብለህ አሁን ስጋ ስለሚያስፈልገኝ ስጋ አምጣልኝ፡፡” አለው፡፡ ቀጥሎም ዝንጀሮው ገብስ ይዞለት መጣ፡፡
አንበሳውም “ጥራጥሬ እንደማልበላ ነግሬሃለሁ፡፡” ብሎ ሲጮህበት ዝንጀሮው “ጌታዬ፣ ሌላ ምንም ላገኝ አልቻልኩም፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው ዝንጀሮው እንደማይታዘዝለት ስለገባው መርዝ የተቀባበት የእንስሳ ቆዳ አዘጋጅቶ ዝንጀሮውን “በል እዚህ ላይ ተኛ፡፡ ይህ እንደ እኔ እንድትጠነክር ይረዳሃል፡፡ እኔም በልጅነቴ እዚህ ላይ ተኝቼ ነው ያደኩትና አንተም እዚህ ላይ ተኛና እንደእኔ ጠንካራ ሁን፡፡” አለው፡፡
ዝንጀሮውም እውነት መስሎት ቆዳው ላይ ሲተኛ ሞተ፡፡ አንበሳውም ለአደን ወደ ጫካ ሄደ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|