የቤና ህዝብ አመጣጥ
በእያሱ ኦሪጎ የተተረከ
ሶስት ጡቶች ያሏት አንዲት ንግስት ነበረች፡፡ ታዲያ በአንድ ወቅት ድርቅ ለሰባት ዓመታት በአካባቢው ተከስቶ ህዝቡ ሁሉ በረሃብ ሲያልቅ ሁለት ሰዎች ብቻ ቀሩ፡፡ ሁለቱም ሰዎች የንግስቲቱ የልጅ ልጆች ነበሩ፡፡ ብዙ ሰው ሲሞት የቀሩትም ስለተሰደዱ በአካባቢው የቀሩት እነዚህ ሶስቱ ብቻ ነበሩ፡፡
የህዝቡም ቁጥር እንደገና ያንሰራራ ዘንድ ከንግስቲቱ የሚወለድ ሰው አልነበረም፡፡ ከልጅ ልጆቹ ጋር ግብረ ስጋ መፈፀም ስለማይቻል ንግስቲቱ አንድ በግ አርዳ ቆዳውን አይኖቿ ላይ ከሸፈነች በኋላ የልጅ ልጆቿን “ኑና በየተራ አብራችሁኝ ተኙ፡፡ የወር አበባዬም በቀረ ጊዜ አላያችሁም፡፡” አለቻቸው፡፡
ከዚያም ንግስቲቱ አርግዛ መጀመሪያ ሴት ልጅ፣ ከዚያም ሌላ ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ከዚያ በኋላ ልጇን ለአንደኛው የልጅ ልጇ ድራት እነርሱም ተጋብተው አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅ ወለዱ፡፡
ነገር ግን አንድ ግዙፍ ጎልጃ የተባለ ሰዎችን የሚበላ እንስሳ ስለነበረ የህዝቡን ዝርያ እንዳያጠፋ በመስጋት ንግስቲቱ ይህንን እንስሳ መግደል ፈለገች፡፡ አንድ ጉድጓድ በወጥመድነት በማዘጋጀት ያላገባችውን ልጇን ጉድጓዱ ውስጥ አስቀምጣት ጎልጃው ወደ ልጅቷ ተስቦ ጉድጓዱ ውስጥ ሲወድቅ ጉድጓዱ ውስጥ ከነበሩት ጦሮች ላይ ወድቆ ከልጅቱ ጋር ተያይዘው ሞቱ፡፡
እናም እስከ አሁን ድረስ የአካባቢው አዛውንቶች የቤና ህዝብ ከዚያ ትንሽ ቤተሰብ ቀስ በቀስ እየተባዛ እዚህ መደረሱን ይናገራሉ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|