ብልጧ ፍየል
በመተኪያ ሊብሪ የተተረከ
ፍልፈሉ የነብሩ የወንድም ልጅ ስለሆነ ሁልጊዜ ነብሩን አጎቴ እያለ ይጠራው ነበር፡፡ ነብሩም ብዙ ላሞች፣ ፍየሎችና በጎች ስለነበረው ፍልፈሉ የነብሩን ከብቶች ይጠብቅ ነበር፡፡ የፍልፈሉ እናት ደግሞ ከዛፍ ላይ የተቦረቦረ ግንድ ውስጥ ትኖር ነበር፡፡ ታዲያ ፍልፈሉ እናቱ ከዛፉ ላይ የምታረግፍለትን ፍራፍሬ እየበላ ሲኖር ነብሩ ግን እናቱ በብዙ ድካም የምታዘጋጅለትን ምግብ ነበር የሚበላው፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ ፍልፈሉ ነብሩ እናቱን እንዲገድላት እንዲህ ብሎ መከረው “እኔ የራሴን እናት ስለበላኋት አንተም እናትህን ብትበላት አብረን መኖር እንችላለን፡፡”
ነብሩም “እንግዲያው እሺ፡፡” ብሎ የፍልፈሉን ምክር በመስማት እናቱን በላት፡፡ ፍልፈሉ ግን በብልጠት እናቱን ዛፍ ላይ ደብቆ ፍራፍሬ እያራገፈች መመገቡን ሲቀጥል ነብሩ ግን እናቱን ስለገደላት በረሃብ መሰቃየት ጀመረ፡፡
በኋላም ነብሩ ፍልፈሉን “አንተ እንዴት ነው እንደዚህ ወፍረህ የተስማማህ?” ብሎ ሲጠይቀው ፍልፈሉም “እኔ አንተ ከብቶች ላይ የሚኖሩትን ዝንቦች ከመብላት በስተቀር ሌላ የተለየ ነገር አላገኝም፡፡” አለው፡፡
ነብሩ ታዲያ የሚበላው ነገር ስላልነበረው አቅሙ እየደከመ ሄደ፡፡ ሆኖም ነብሩ በፍልፈሉ መታለሉን ስለጠረጠረ ፍልፈሉ ከብቶቹን እየጠበቀ ሳለ ወደ ፍለፈሉ እናት በመሄድ የፍልፈሉን ድምፅ አስመስሎ ፍራፍሬ እንድታረግፍለት ሲጠይቃት ፍራፍሬዎችን አወረደችለት፡፡ በዚህ ጊዜ ነብሩ የፍልፈሉን እናት ገደላት፡፡ በሚቀጥለው ቀን ነብሩ ፍልፈሉ ሲያለቅስ ባየው ጊዜ “ምን ሆነህ ነው የምታለቅሰው?” ሲለው “ከአንዷ ላምህ ላይ ዝንብ ለቅሜ ልበላ ስሞክር ላሟ ረገጠችኝ፡፡” አለው፡፡ ይህንንም ያለው ፍልፈሉ ሌላ ብልሃት ዘይዶ ነበርና “ከዚያም አልፎ፣አጎቴ፣ላሟ ብትረግጠኝ ምንም አልነበረም፡፡ ነገር ግን አንበሳው ሁልጊዜ ከብቶችህን ለመብላት እየመጣ ስለሆነ በጣም ተጨንቄያለሁ፡፡” አለው፡፡
ነብሩም “ታዲያ ምን ባደርግ ይሻላል?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ፍልፈሉም “እኔ ብቻዬን ስለሆንኩ ጦር ይዘህ መጥተህ አጥቃቸው፡፡” አለው፡፡
እናም ፍልፈሉ ከብቶቹን በሙሉ በቀለም አዥጎርጉሮ አንበሳ እንዲመስሉ ካደረገ በኋላ ቀኑ በመሸ ጊዜ ከብቶቹ ወደ ቤታቸው በሚመለሱበት ሰአት ነብሩ ፍልፈሉን “አንበሶቹ ከብቶቹን በያዛቸው ጊዜ እኔ መጥቼ በጦር እወጋቸው ዘንድ ጩኸት አሰማ፡፡” አለው፡፡
እናም አንድ ቀን ምሽት ላይ ፍልፈሉ “አንበሶች መጡ!” የሚል ድምፅ ሲያሰማ ነብሩ የራሱን ከብቶች አንበሶች ስለመሰሉት በጦር ወግቶ ገደላቸው፡፡ ከዚያም ፍልፈሉ ነብሩ ተጨማሪ ከብቶችን አርዶ ስጋውን ከአንድ ዋሻ ውስጥ ወስዶ እንዲሸጥና አብረውም ወደ ስጋ ንግድ እንደሚገቡ ነገረው፡፡ በዚህ ዓይነት ፍልፈሉ ሌሎች ላሞች ካረደ በኋላ ለራሱ መግቢያ ያህል ብቻ በር ወዳለው ዋሻ ወስዶ ስጋውን አስቀመጠው፡፡ ነብሩም በሃሳቡ ስለተስማማ ስጋውን ወደዚያው ወስደው ፍልፈሉ ከዋሻው ውስጥ በመሆን ስጋውን መሸጥ ጀመረ፡፡ ይህንንም ያየው ነብሩ በፍልፈሉ ስለቀናበት እርሱም እንደፍልፈሉ ዋሻው ውስጥ መግባት ፈልጎ በሩ አላስገባ ስላለው ፍልፈሉን “በእንዲህ አይነት ጠባብ መግቢያ እንዴት ወደ ውስጥ መግባት ቻልክ?” ብሎ ሲጠይቀው ፍልፈሉም “ትንሽ ወደ ኋላህ መለስ በልና በሃይል ተንደርድረሀ በጭንቅላትህ በበሩ ለመግባት ሞክር፡፡” አለው፡፡
ነብሩም ይህንን ለማድረግ በሞከረ ጊዜ ጭንቅላቱ ለሁለት ተከፍሎ ሞተ፡፡
ከዚያም ፍልፈሉ ነብሩን ከገፈፈው በኋላ ቀበሮዎችና ጅቦች ስጋ ለመግዛት የመጡ በመምሰል ፍልፈሉን ገድለው ስጋውን ለመውሰድ እንደመጡ ባወቀ ጊዜ የገፈፈውን የነብሩን ቆዳ አድርቆ ከላዩ ላይ ቃጭል በማሰር የሚያስፈራ ድምፅ እንዲያወጣ አደረገው፡፡ ከዚያም ቀበሮና ጅብ ወዳጅ መስለው ከመጡ በኋላ “ንግዱ እንዴት ነው? ስጋውንስ እንዴት እየሸጥክ ነው?” ብለው ጠየቁት፡፡
ፍልፈሉም “ንግዱ በጣም ጥሩ ነው፡፡ እናንተም ጥሩ ወዳጆቼ ስለሆናችሁ ከደጃፉ ላይ ቁጭ በሉና ልጋብዛችሁ፡፡” አላቸው፡፡
ከዚያም የነብሩን ቆዳ እያሳያቸው “ታዲያ ድምፅ እንዳታሰሙ፡፡ አለበለዚያ አጎቴን ታስቆጡታላችሁ፡፡ ጀርባችሁን ብቻ ወደ እኔ አዙራችሁ በመቀመጥ ጠላቶቼ ይመጡብኛል ብዬ ስለምስጋ እያያችሁልኝ ስጋውን ብሉ፡፡” አላቸው፡፡
እናም ጀርባቸውን ወደ ዋሻው አዙረው ሲቀመጡ ፍልፈሉ ቀስ ብሎ የነብሩን ቆዳ ከሁለቱ እንስሳት ጅራት ላይ ካሰረው በኋላ “አጎቴ እያሳደዳችሁ ነው!” ብሎ በመጮህ ቆዳውን ሲደበድበው ቃጭሉ የሚረብሽ ድምፅ ስላሰማ ቀበሮውና ጅቡ ነብሩ እያሳደዳቸው መስሏቸው ከዚያ ስፍራ ሮጠው ጠፉ፡፡
በዚህ አይነት ካታለላቸው በኋላ የቀሩትን ከብቶች በሙሉ ለራሱ አድርጎ ሃብታም ፍልፈል ሆነ፡፡ የፍልፈሉም ብልሃት የሚናቅ አይደለም፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|