ጦጣና ነብር
በመተኪያ ሊብሪ የተተረከ
አንዲት ጦጣ ልጇን ዛፍ ላይ ስትወልድ አንዲት ነብር ደግሞ ከዛፉ ስር ወለደች፡፡ ልጆቹም እያደጉ ሲሄዱ የጦጣዋ ልጅ ዛፍ ላይ ሆና የነብሯ ልጅ ደግሞ መሬት ሆነው መጨዋወት ጀመሩ፡፡
ታዲያ አንድ ቀን የነብሯ ልጅ የጦጣዋን ልጅ ለምን ከዛፉ ላይ ወርደሽ አብረሺኝ አትጫወቺም?” ብላ ስትጠራት ጦጣዋም “እሺ” ብላ ከዛፉ ላይ በመውረድ ሁለቱ ልጆች እንደ ጓደኛ አብረው መጫወት ጀመሩ፡፡ ቀኑ በመሸም ጊዜ የጦጣዋ ልጅ ወደ እናቷ ተመልሳ ዛፍ ላይ ወጣች፡፡
የጦጣዋም እናት ልጇን “የት ነበርሽ?” ብላ ስትጠይቃት ልጅቷ “አንዲት እንደእኔ ቆንጆ ልጅ ከዛፉ እንድወርድ ጠርታኝ ከእርሷ ጋር ስጫወት ዋልኩ፡፡” ብላ መለሰችላት፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የነብሯም ልጅ በእናቷ “ቀንሽን እንዴት አሳለፍሽ?” ተብላ ስትጠየቅ “አንዲት ቆንጆ ልጅ ከዛፉ ላይ ትኖራለችና ከራሷ ላይ ነጭ ፀጉር አላት፡፡” ብላ መለሰች፡፡ የነብሯም እናት “አሁን ታዲያ የት አለች? ወደቤት ሄደች ነው ያልሺኝ?” አለቻት፡፡
ልጅቷም “አዎ፣ አሁን ወደ እናቷ ተመልሳ ሄዳለች፡፡” ስትል መለሰች፡፡ ከዚያም እናቲቱ ነብር “ተመልሳ እንደምትመጣ አልነገረችሽም?” ብላ ጠየቀቻት፡፡
“አዎ! ነገ በርግጠኝነት ተመልሳ ትመጣለች፤ ልክ እንደዛሬው ስንጫወት እንውላለን፡፡”
“ለመሆኑ አንቺ የተፈጠርሺው እሷን እየበላሽ እንድትኖሪ መሆኑን አታውቂም?” ካለቻት በኋላ “ነገ ተመልሳ ስትመጣ ጥቂት ቀልዶችን ንገሪያትና ከዚያ በኋላ አንገቷ ላይ ንከሻት፡፡” አለቻት፡፡
የነብሯም ልጅ “እሺ እናቴ! ነገ ጦጣዋን እበላታለሁ፡፡” አለቻት፡፡
የጦጣዋም እናት ልጇን “ለምንድነው እዚያ ሄደሽ ከነብሯ ልጅ ጋር የተጫወትሽው? አንቺን ዛፍ ላይ ወጥቼ እንድወልድሽ የተገደድኩት እነርሱ የእኛ ጠላቶች ስለሆኑና ስለሚገድሉን አይደለም? ከዚህ በኋላ በፍፁም ወደእርሷ ተመልሰሽ እንዳትሄጂ! ነገር ግን ወርደሽ ካልተጫወትን ብላ ከወተወተችሽ እርሷን እናቷ እንደመከረቻት ሁሉ ያንቺም እናት እንደመከረችሽ ንገሪያት፡፡” አለቻት፡፡
በማግስቱም የነብሯ ልጅ የጦጣዋን ልጅ ስትጠራት የጦጣዋ ልጅ እናቷ የነገረቻትን ነገር ነገረቻት፡፡ በዚህ ዓይነት ህይወቷ ተረፈ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|