የጅብ ጭካኔ
በመተኪያ ሊብሪ የተተረከ
በታሪኩ መጀመሪያ ላይ ተራኪው የተጠቀመበት በአሪ ቋንቋ የተረት መክፈቻ “ኤሪ ኤርቶቴ” ማለትም “የድሮ ተረቶችን እንተርክ” የሚል ነበር፡፡
ባልና ሚስት አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጆች ነበሯቸው፡፡ ባልና ሚስቱ ሃብታም ቢሆኑም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስለሞቱ ልጆቹ ወላጅ አልባ ሆኑ፡፡ ልጆቹም ከብቶቻቸውን እየተንከባከቡና ያገኙትን ነገር እየበሉ መኖር ጀመሩ፡፡
ታዲያ አንዲት ጅብ በየቀኑ እየመጣች የእንሰት ምግብ ሰርታ አስቀምጣላቸው ትሄዳለች፡፡ ልጆቹም ወደቤት ሲመለሱ ጅቧ ያዘጋጀችውን ምግብ አግኝተው ራታቸውን ይበላሉ፡፡
እነርሱም “ይህንን ሊያደርግልን የሚችለው ማነው?” ብለው ጠየቁ፡፡ ወንድ ልጁም “ምግቡን የሚያዘጋጅልን ማን እንደሆነ ማየት አለብን፡፡ ለምን አንቺ ከብቶቹን ይዘሽ ስትሄጂ እኔ እንሰቱ ውስጥ ተደብቄ ማንነቱን አላጣራም?” በማለት በዚህ ተስማምተው ተለያዩ፡፡
ጅቧም በተለመደው ሰአት ስትመጣ ልጁ ያልተለመደ ነገርና እንግዳ ድምጽ አስተዋለ፡፡ ጅቧ አስማተኛ ነበረችና የማድቤት እቃ ቢላዋ ወይም ማንኪያ ስትፈልግ ትጠራቸውና እቃዎቹም “አቤት! መጣሁ፡፡” እያሉ ወደጅቧ ይመጣሉ፡፡
“ሺሊም (በአሪኛ ቢላዋ ማለት ነው) የት ነው ያለኸው?” እያለች ትጣራለች፡፡
እቃዎቹም “ይኸው፣ አለሁ፣ መጥቻለሁ፡፡” እያሉ ይመጣሉ፡፡ መክተፊያው፣ ጭልፋው፣ የቅቤው ጮጮ በየተራ ሁሉም ስለሚመጡ ምግቡን ለማዘጋጀት ብዙ ጊዜ አይወስድባትም፡፡
ይህንን ባየ ጊዜ ልጁ የጠበቀው ሰው ሊሆን ይችላል ብሎ ስለነበረ በጣም ተገረመ፡፡ በፍራቻም ሽንቱን በላዩ ላይ ለቀቀው፡፡ ጅቧም ቀና ብላ ስታይ ልጁን ተመለከተችው፡፡
“ከዛፉ ላይ ወርደህ ና፡፡” ስትለው በፍራቻ ተሞልቶ ከዛፉ ወረደ፡፡ ልጅቷም ወደቤት ስትመለስ ጅቧ በሌላኛው ክፍል ውስጥ ተደብቃ ነበር፡፡ ልጅቷም ከብቶቹን ይዛ መጥታ ምግቡን ስትመለከት ወንድሟን ምግቡን ማን እንዳዘጋጀው ስትጠይቀው ልጁም ጅቧን ከሚቀጥለው ክፍል ውስጥ ጠርቶ “እርሷ ናት” ብሎ ነገራት፡፡
ከዚያም ጅቧ ልጁን “እንጋባና አብረን እንኑር፡፡ እንደዚህ እየመገብኳችሁ እንኖራለን፡፡” አለችው፡፡ በዚያም እለት አብራው ተኝታ በማግስቱ ወንድምና እህት የቀረበውን የጅቧን የጋብቻ ጥያቄ ተወያዩበት፡፡ ልጁም “ጅቧ እንዳገባት ጠይቃኛለች ከጅብ ጋር ደግሞ ጅቧ እየመገበችን እንዴት ልንኖር እንችላለን? ይህ እንዲሆን አንፈልግም፡፡” አለ፡፡
ይህን ከተነጋገሩ በኋላ ከአካባቢው ለመጥፋት ወሰኑ፡፡
“ወደ ጫካው ሄደን ለአምላክ እየፀለይን ከብቶቻችንን እዚያው እየጠበቅን እንኑር፡፡” ተባባሉ፡፡
ከዚያም በኋላ ከብቶቹን ለግጦሽ ሊያሰማሩ የሄዱ መስለው ጅቧን እቤት ትተዋት ወደጫካው ከብቶቹን እየነዱ ሄዱ፡፡ ከብቶቹንም ጫካው ውስጥ ከደበቋቸው በኋላ ወደ ጓደኞቻቸው ዘንድ ሄዱ፡፡
በዚህ ጊዜ ጅቧ ራሷን ወደ ሴት ሰውነት በመቀየር ወደጓደኞቻቸው ቤት መጣች፡፡ በእጇም ረጅምና ቀጭን ዘንግ ይዛ ነበር፡፡
ከዚያም “ይህንን የእንጨት ዘንግ የሚሰብር እኔን ማግባት ይችላል፡፡” አለች፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም ዘንጉን ሊሰብሩ ቢሞክሩም አልቻሉም፡፡ ከዚያም ልጁ ሲሞክር ዘንጉን ሰበረው፡፡ ጅቧም “ስለዚህ አንተን ነው የማገባው፡፡” ስትለው ጅብ መሆኗን ሳያውቅ ተጋብተው ከእህቱ ጋር አብረው መኖር ጀመሩ፡፡
ከእለታት አንድ ቀን የልጁ እህት ወደ ጎረቤት ሄዳ ልታድር ስትሄድ ልጁ ተኝቶ ነበር፡፡ የልጁ ሚስት (ጅቧ) የተሳለ የብረት መቆስቆሻ የከሰል እሳት ውስጥ በማጋል ሰውየውን ወግታ ልትገድለው እያዘጋጀች ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ አንዲት አይጥ ከጉድጓዷ ወጥታ “ቀዩ የጋለ መቆስቆሻ! ቀዩ የጋለ መቆስቆሻ! እየተዘጋጀልህ ነው! ተነስ! ተነስ ልትገድልህ ነው!” ብላ የተኛው ልጅ ላይ ስትጮህበት ባልየው ነቃ፡፡ ጨካኟም ጅብ “አይጧን ግደላት! አይጧን ግደላት!” አለችው፡፡ ባልየውም አይጧ ያለችውን ስላልሰማ ገደላት፡፡
ከዚያም አንዲት ዶሮ መጥታ “ቀዩ የጋለ መቆስቆሻ! ቀዩ የጋለ መቆስቆሻ! እየተዘጋጀልህ ነው! ልትገድልህ ነው!” አለችው፡፡ ጅቧም “ይህችን ዶሮ እረዳት! ይህችን ዶሮ እረዳት!” ስትለው ዶሮዋን አረዳት፡፡ አሁንም አልገባውም ነበር፡፡
በመጨረሻም ጅቧ እሱን በጋለው መቆስቆሻ ገድላው አስከሬኑን እንሰት ውስጥ ደበቀችው፡፡ እህቱም ተመልሳ ስትመጣ ጅቧ የታመመች መስላ በመተኛት “ወንድምሽ ወደ ገበያ ስለሄደ ይህንን ምግብ አንቺ ብይው፡፡” ብላ የእንሰቱን ምግብ ሰጠቻት፡፡ እህቱም ምግቡን ተቀብላ ብትበላም ጅቧን ትፈራት ስለነበረ መርዛው ሊሆን ይችላል ብላ ጠረጠረች፡፡ ሆኖም ምግቡን በላችው፡፡ ችግርም አልነበረውም፡፡
ከዚያም አሁንም የታመመች በመምሰል ጅቧ ሴት መድኃኒት ፍለጋ እንደምትሄድ ተናገረች፡፡ ነገር ግን የምትሄደው ቤተሰቧን ጠርታ እነርሱ መጥተው የልጁን አስከሬን እንዲበሉት ለማድረግ ነበር፡፡ እናም “እስክመለስ ድረስ ይህንን ጤፍ ፍጪ፡፡ ከዚህ ቤት የትም እንዳትወጪ፣ እህሉን ብቻ ፍጪ፡፡” ብላት ሄደች፡፡ ከቤቱ ውስጥ ስትወጣም ከራሷ ብልት ፀጉር ወስዳ እንደቁልፍ በማዘጋጀት መቀርቀሪያውን ስለቋጠረችው ልጅቷ በሩን ከፍታ መውጣት እልቻለችም፡፡
ከዚያ በኋላ አንዲት አይጥ መጥታ “ወንድምሽን ገድላዋለችና አሁን የሄደችው ዘመዶቿ መጥተው እንዲበሉት ልትጠራቸው ነው፡፡” ብላ ነገረቻት፡፡ “አንቺንም ልትገድልሽ ነውና ጉሎ የተባለውን የተቦረቦረ እንጨት አምጥተሽ የወንድምሽን ደም ጨምሪበት፡፡” ብላ አስጠንቅቃ በሩን ከፈተችላት፡፡ ልጅቷም የወንድሟን ደም በቅል ይዛ አመለጠች፡፡ ከዚያም ሌሎቹ ጅቦች በሙሉ ሲመጡ ልጅቷ የለችም፡፡ ጅቧም ቤቱን ሁሉ ብታስስም ልጅቷን ማግኘት ስላልቻለች ዘመዶቿን እዚያው ትታ ልጅቷን መከታተል ጀመረች፡፡
ልጅቷም አንዲት ጦጣ መንገዷ ላይ አጋጥማት ጦጣዋ “ፈርተሻል?” ብላ ስትጠይቃት ልጅቷም “አዎ አንዲት ጅብ ልትበላኝ እያሳደደችኝ ነው፡፡” አለቻት፡፡
ጦጣዋም “አታስቢ እኔ እመልሳታለሁ፡፡ አንቺ ዝም ብለሽ መንገድሽን ቀጥይ፡፡” አለቻት፡፡ ሆኖም ጦጣዋ ጅቧን ስታያት በጣም ስለፈራቻት ዘላ ዛፍ ላይ ወጥታ አመለጠች፡፡ ሌሎቹም ጅቦች በጦጣዋ ፍራቻ መሳቅ ጀመሩ፡፡
ልጅቷ መንገዷን ቀጥላ ስትሄድ ፈጣሪን አንድ ብልቱን በቢላዋ የሰነጠቀ አለት ላይ ቁጭ ብሎ አገኘችውና እርሱም የት እየሄደች እንደነበር ጠየቃት፡፡
እርሷም እንደበፊቱ “አንዲት ጅብ ልትበላኝ እየተከታተለችኝ ነው፡፡” ብላ መለሰች፡፡
ፈጣሪም ሙሉ ታሪኩን ከሰማ በኋላ “እንግዲያው ወንድምሽን እንደገና ሰው አደርገዋለሁ፡፡ ወደ ህይወትም እንደገና እመልሰዋለሁ፡፡ አይጧ በቅል አድርጋ የሰጠችሽን ደም ብቻ ስጪኝ፡፡” አላት፡፡
እርሷም ደሙን ሰጠችው፡፡ ፈጣሪም እርሷ ቁጥቋጦው ውስጥ እንድትደበቅ ነግሯት “ጅቦች ሲመጡ ምን እንደማደርግ አውቃለሁ፡፡” አላት፡፡
ጅቦቹም መጥተው “አንዲት በዚህ ያለፈች ልጅ አይተሃል?” ብለው ፈጣሪን ጠየቁት፡፡
ፈጣሪም “እዚያ ታገኙዋታላችሁ፡፡” ብሎ ወደ ጉድባው ጠርዝ አመላከታቸው፡፡ እርሷም ጌታ እንዳዘዛት ስትሄድ “ዝለይ!” ሲላት ዘላ ጉድባው ውስጥ ገባች፡፡
ከዚያም ፈጣሪ ደሙን ጎተራ ውስጥ ጨምሮ ደሙ ሰው ሆነ፡፡ እናም ልጁ ከጎተራው ውስጥ ወጥቶ እህቱን በማግኘት አብረው በደስታ መኖር ጀመሩ፡፡
ስለዚህ ፈጣሪ ብዙ ነገር ማድረግ ይችላል፡፡ ሰብሉንም የፈጠረልን እርሱ ነው፡፡ በአሪ ቋንቋ የተረት መዝጊያው ሃረግ “ኤሪና ኮሴማክሴ” ይባላል፡፡
ይህም ማለት ተረቴን ጨርሻለሁ ማለት ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|