የነብሯ ልጅ
በመተኪያ ሊብሪ የተተረከ
አንዲት ልጅ ያላት ነብርና ልጅ ያላት ሴት ነበሩ፡፡ ነብሯም ያገኘችውን እንስሳ ሁሉ በመግደል ስጋውን ለልጇ ታመጣ ነበር፡፡ ሰውም ቢሆን እየገደለች ታመጣ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ልጇን የምትመግበውን እንስሳ እያደነች ሳለ የሴትየዋ ቤት ውስጥ ስትገባ ህፃኑ ልጅ ብቻውን አልጋው ላይ ተኝቶ እናቱ አጠገቡ እንደሌለች አየች፡፡ ነብሯም ልጁን ወስዳ ለልጇ ልትመግበው በመፈለግ ወደ ጫካው ይዛው ሄደች፡፡
ሴትየዋም ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇ አለመኖሩን ስታይ ብታለቅስ፣ ብታለቅስ ምንም አላገኘችም፡፡ ነብሯ ልጁን ወስዳ ለልጇ ልትሰጠው ስትል ልጁ አይን አይኗን ሲያያት የልጁን አይኖች ማማር በማየት “እንደ ራሴ ልጆች ባሳድገው ይሻለኛል፡፡” ብላ ለራሷ ወሰነች፡፡ ከዚህም በኋላ ልጁን ልክ እንደራሷ ልጆች እየተንከባከበችና እየመገበች አሳደገችው፡፡
የነብሯም ልጆች በባህላቸው መሰረት ምግባቸውን ራሳቸው እያደኑ ነበር የሚመገቡት፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ የሆነው ህፃን ይህንን ማድረግ ስለማይችል በነብሯ ላይ ጥገኛ በመሆን ነብሯ እያደነች ምግብ ማምጣቷን ቀጠለች፡፡ ይህ ታዲያ ለነብሯ ሸክም ከመሆኑም በላይ ነብሯ ራሷን እየበደለች ያላትን ሁሉ ለልጁ ትሰጠው ነበር፡፡ ልጁንም እንዲህ አለችው፣ “አንተ እንደእኔ ልጆች ለራስህ ማደን አትችልምና ሁልጊዜ እኔን መጠበቅ ግድ ሆኖብሃል፡፡ እኔም ጊዜዬን ሁሉ ለአንተ ምግብ በመፈለግ ስለማጠፋ ሸክም እየሆንክብኝ ነውና ከወሰድኩህ ወላጆችህ ቤት እመልስህና እዚያ እንደሌሎቹ ሰዎች መኖር ትችላለህ፡፡”
ልጁም መሄድ ስለፈለገ ነብሯ ወደ ወላጆቹ ቤት ወስዳው ከበራፉ ላይ ካደረሰችው በኋላ ወደ ጫካው ተመልሳ ሄደች፡፡ ወላጆቹም ከሄዱበት ሲመለሱ ልጁ አድጎና በመልክ ልክ አባቱን መስሎ አገኙት፡፡
ምግብም በሰጡት ጊዜ የእነርሱን ምግብ ስላለመደ አልበላም በማለቱ ወላጆቹ አንዳች ነገር ሆኖ ይሆናል ብለው ገመቱ፡፡
“ምን ሊሆን ይችላል? ምን ነክቶት ይሆን?” ብለው አሰቡ፡፡
ከዚያም ስጋ ሲሰጡት ልክ እንደእንስሳ እየዘነጠለ ይበላ ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ “አሃ! ልጃችን ተወስዶ የነበረው በነብር መሆን አለበት፡፡ ስጋ የሚወደው ልክ እንደነብሮች ነው፡፡” አሉ፡፡
ነብሯ ግን ልቧ ከልጁ ዘንድ ስለቀረ ማታ ተመልሳ ድኩላ ገድላ በየቀኑ ከደጃፉ ላይ ትተውለት ጀመር፡፡
ልጁም የኋላ ኋላ የወላጆቹን ቋንቋ ስለለመደ በሴት ነብር ተወስዶ ማደጉን ነገራቸው፡፡
ታዲያ የልጁ አባት “እንግዲያው ያሳደገችህ ነብር እንዴት ነበረች? ትወዳት ነበር?” ብሎ ሲጠይቀው “አዎን” ብሎ መለሰለት፡፡
በመቀጠልም አባትየው “እንዴት ነው ያሳደገችህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ በዚህ ጊዜ እንደወትሮው ነብሯ ድኩላውን ይዛ መጥታ ከደጃፉ ላይ ልትተውለት ቆማ ነበር፡፡
ልጁም “ጥሩ ኑሮ ነበር የምኖረው፡፡ ስራ አልሰራም፡፡ ብዙ ስጋ ነበረኝ፡፡ ሁሉ ነገሯ ጥሩ ነበር፡፡ ትወደኝም ነበረ፡፡ ነገር ግን መጥፎ ጠረን ነበራት፡፡” ብሎ ለአባትየው ሲነግረው ነብሯ ሰምታ ተናደደች፣ አዘነችም፡፡ “ይህንን ልጅ በእውነት እወደው ነበር፡፡” ብላ አሰበች፡፡
ልጁም ወሬውን በመቀጠል “መጥፎ ጠረን ነበራት፣ በጣም መጥፎና የማይቻል ጠረን ነበራት፡፡” እያለ ይናገር ጀመር፡፡
ነብሯም ለራሷ “ይህንን መጥፎ ስም የሰጡኝ ወላጆቹ እንጂ ልጁ አይደለም፡፡ ለምንድነው ይህንን ሁሉ ጥያቄ የሚጠይቁት?” ብላ በማሰብ ቂም ይዛ ልትበቀላቸው ወሰነች፡፡
በማግስቱ ጠዋትም አባትየውን ነክሳ ከገደለችው በኋላ በቀል መሆኑን ለማሳየት ሳትበላው እዚያው በሩ ላይ ትታው ሄደች፡፡ አባትየው ከተቀበረም በኋላ በዚያው ቀን መጥታ እናትየውን ነክሳ ከገደለቻት በኋላ እርሷንም በቀል መሆኑን ለማሳየት ሳትበላት ትታት ሄደች፡፡ ነብሯ መሰደቧን ሰዎች እንዲያውቁ ፈልጋ ነው፡፡
ልጁም በሃዘን ተቆራምዶ እያለቀሰ ከበሩ ደጃፍ ላይ ተቀመጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ነብሯ መጥታ “ያንን መጥፎ ስም የሰጠኸኝ አንተ አይደለህም፡፡ ወላጆችህ ናቸው፡፡ አንተን መልሼ ስላመጣሁህ እነርሱ ሰደቡኝ፤ ይህ በጣም ያሳዝናል፡፡ የገደልኳቸውም በበቀል ተነሳስቼ ነው፡፡ አንተን ልገድልህ ይቅርና ልነካህም አልደፍርም፡፡ ምክንያቱም ስላሳደኩህ አንተን መጉዳት ልቤ አይችልም፡፡ ምንም ብትለኝም አንተ አሁንም ልጄ ነህ” አለችወ፡፡
ልጁንም አቅፋ ዳበሰችው፡፡ ነበሯም “የሌላ ሰው፣ ዘመድህ ያልሆነን ሰው ስታሳድግ በምስጋና ቢስነታቸው ሊያስቀይሙህ ይችላሉ፡፡” አለችው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|