የበሬው ጥጃ
በመተኪያ ሊብሪ የተተረከ
አንበሳና ነበር አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ታዲያ አንበሳው በሬ ሲገዛ ነብሩ ላም ይገዛና ከጊዜ በኋላ የነብሩ ላም ጥጃ ወለደች፡፡ ሆኖም አንበሳው ጥጃው የእኔ በሬ ጥጃ ነው በማለት ሲከራከር ነብሩ ጥጃው የእርሱ ላም የወለደችው መሆኑንና በሬ ጥጃ መውለድ እንደማይችል ሊያስረዳው ቢሞክርም አሻፈረኝ አለ፡፡
በመቀጠልም አንበሳው በጉልበቱ ተማምኖ “ጥጃው የእኔ በሬ ጥጃ ነው፡፡ ይህንን ማንም የሚስማማበት ነው፡፡ በሬ ጥጃ ሊወልድ ይችላል፡፡” በማለት መከራከር ያዘ፡፡
ነብሩም “እንግዲያው እነዚህ ምስክር የሚሆኑትን ሰዎች ልሰማቸው እፈልጋለሁና እነርሱም በሬ ጥጃ ይወልዳል ብለው ከመሰከሩ ጥጃውን ልትወስደው ትችላለህ፡፡” አለው፡፡
እናም የዱር እንስሳቱ ሁሉ ተሰበሰቡ፡፡ ጥንቸል ግን በጣም ጠንካራ፣ ሹልና እንደጦር የሰላ ሆኖ ከስሩ ጥንቸል ሊደብቅ እንዲችል ተደርጎ የተቦረቦረ ችካል ስታዘጋጅ ስለነበረ ከስፍራው አልገተኘችም ነበር፡፡ ይህንን የሚያዘጋጅላት ጓደኛዋ ስለነበረ ይህ ተዘጋጀቶ እስኪያልቅ መጠበቅ ነበረባት፡፡
በመጨረሻም ከስብሰባው ቦታ ስትደርስ “ይህን ሁሉ ጊዜ የት ነበርሽ?” ብሎ አንበሳው አፈጠጠባት፡፡ “ለምንድነው ያረፈድሽው?” ብሎም ጮኸባት፡፡
ጥንቸሏም “የአባቴ ረግረግ ቦታ ላይ የተነሳውን እሳት ሳጠፋ ቆይቼ ነው፡፡” ብላ መለሰች፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው “ደም ያስቀምጥሽና! አባትሽ ምንም መሬት የለውም፤ ቢኖረውም እንኳ ረግረጋማ ቦታ ላይ እሳት ሊነሳ አይችልም፡፡ ለምንድነው የምትዋሺው?” አላት፡፡
እርሷም “እንግዲያውማ በሬ እንዴት ጥጃ ይወልዳል? አንተ ራስህ አጭበርባሪ ነህ፣ በጉልበትህ ብቻ የምትመካ!” አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው በጣም ተበሳጭቶ በመዳፉ ጥንቸሏን ሊመታት ሲሞከር ጥንቸሏ ከችካሉ ስር ወዳለው ጉድጓድ ዘላ ገብታ ተደበቀች፡፡ የአንበሳው መዳፍ ከጉድጓዱ ውስጥ ሲገባ እንደሚታወቀው የአንበሳ ጉልበት ያለው ከመዳፉ ላይ ነውና ጥንቸሏን ያገኛት መስሎት መዳፉ ችካሉ ላይ ስለተቀረቀረ ደሙ በየቦታው መፍሰስ ጀመረ፡፡
ደሙንም ከመዳፉ ላይ ይልስ ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ የዱር እንስሳቱ በሙሉ አምላክ በአንበሳው ላይ እንደፈረደበት አወቁ፡፡ ፍርዱም የአንበሳ የጥንካሬ ተምሳሌት የሆነው መዳፉ ላይ ስላረፈ ጥጃው የነብሩ እንደሆነ ተስማሙ፡፡
እንስሳቱም “ሙሉ ቀን በአንበሳው ጥንካሬና ኃይል ፍራቻ ምክንያት በሃሰት ለመመስከር እዚህ ዋልን፡፡ ነገር ግን ጥንቸሏ መልካም ነገርን አደረገች፡፡ እውነቱንም ነገረችን፡፡ አሁን በነፃነት ወደየመጣንበት መመለስ የምንችል ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ አንበሳው ሳይሆን የእንስሳት ሁሉ ንግስት ጥንቸሏ ናት፡፡” ብለው ተስማሙ፡፡
በባህላችንም የእንስሳት ንጉስ ጥንቸል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|