ዝንጀሮና ጦጣዋ
በዛርኬ ጎይቴ የተተረከ
በድሮ ጊዜ ዝንጀሮና ጦጣ አብረው ይኖሩ ነበረ፡፡ ፊታቸውም ይመሳሰል ነበር፡፡ ሆኖም ፊታቸው ቢመሳሰልም ዝንጀሮ በአካል ግዙፍ ሲሆን ጦጣ ግን አነስ ያለች ነበረች፡፡
ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን ሁለቱ ስብሰባ ከተቀመጡ በኋላ ብዙ ተወያይተው ሲያበቁ በመጨረሻ አንዱ በሌላው ላይ ቢደራረቡ ሰማይ ላይ እንደሚደርሱ ተስማሙ፡፡
ጦጣም ዝንጀሮዎችን “እናንተ በአካል ግዙፍ ስለሆናችሁ እናንተ ከስር ሆናችሁ እኛ ከላያችሁ ላይ በመሆን ወደላይ መደራረብ እንችላለን፡፡” አለች፡፡
በዚህ ዓይነት ዝንጀሮዎቹ ከስር ሆነው አንዱ በሌላው ላይ ሲደራረቡ ጦጣዎቹ አጠገባቸው መሬት ላይ ሆነው ይመለከቷቸው ነበር፡፡ እርስ በርስ ላይ ተከማምረው ሲጨርሱም አንዲቷ ጦጣ ከስር መሬት ላይ ያለውን ዝንጀሮ ፊንጢጣውን በጣቷ ብትደነቁለው ከስር ያለው ዝንጀሮ በድንጋጤ ሲዘል ክምሩ ፈረሰ፡፡
በዚህ ጊዜ ጦጣዎቹ የዝንጀሮዎቹን የበቀል እርምጃ ፈርተው ሮጠው በመሸሽ ተደብድበው ከመሞት አመለጡ፡፡ ከአንድ ጫካ አጠገብ በደረሱም ጊዜ “ጌታ ሆይ የምንሸሸግበት ቦታ የለንም፡፡ ዝንጀሮዎቹ ደብድበው ሊገድሉን ነውና አድነን፡፡” ብለው ለአምላክ ፀለዩ፡፡
ፈጣሪም “ለምን ትጨነቃላችሁ? ፊታችሁን እቀይረውና ከችግሩ ታመልጣላችሁ፡፡” ብሎ አምላክ የዝንጀሮዎቹን መቀመጫ ፀጉር እንዳያበቅል ሲመልጠው ጦጣዎቹ ቅንድብ ላይ ደግሞ ነጭ ፀጉር አደረገበት፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ አንዱ የሌላኛውን የቀድሞ መልክ ስለማያውቅ እስካሁን ድረስ በሰላም አብረው ይኖራሉ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|