የውሻው ጅራት
በኦዬሻ ቱሽክሎ የተተረከ
በጌታቸው በጣም ይበደሉ የነበሩ አንድ አህያና አንድ ውሻ ጠፍተው ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ለመኖር በማሰብ ከቤታቸው ወጥተው ሄዱ፡፡ ከአንድ ለምለም ስፍራ በደረሱም ጊዜ አህያው እስኪጠግብ ስለበላ ማናፋት አማረውና ውሻውን “ማናፋት እችላለሁ?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ውሻውም “ተው! ጅብ የሰማ እንደሆን መጥቶ ይበላሃል፡፡” ቢለውም አህያው ከጥጋቡ የተነሳ ራሱን መግዛት ተስኖት ሶስት ወይም አራት ጊዜያት አናፋ፡፡
በዚህ ጊዜ ውሻው “እንግዲያው አንተ ማናፋት ካማረህ እኔ ተደብቄ የሚሆነውን አያለሁ፡፡” ብሎ ከአንድ አለት ላይ ወጥቶ ምን እንደሚከሰት መከታተል ጀመረ፡፡ ጅቡም የአህያውን ማናፋት ሰምቶ በመምጣት ገድሎት ስጋውን ከአለቱ ስር አስቀመጠ፡፡
ትኩሱን ስጋ ያየውም ውሻ ምራቁን ማዝረክረክ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ የውሻው ምራቅ ጠብ ያለበት ጅብ ቀና ብሎ ሲመለከት ውሻውን አየው፡፡ ከዚያም ጅቡ ውሻው ከተደበቀበት ወርዶ የአህያውን ቆዳ እንዲገፍ አዘዘው፡፡
ውሻውም ካለበት ቦታ ወርዶ አህያውን ከገፈፈው በኋላ የአህያውን ልብ ሲያይ መታገስ ስላልቻለና በመጎምዠት አፉን ምራቅ ስለሞላው የአህያውን ልብ ለቀም አድርጎ ዋጠው፡፡ ጅቡም የአህያው ሙሉ አካላት እንዳለ ሊፈትሽ ሲመጣ ልቡን ያጣውና ውሻውን “ልቡ የታለ?” ብሎ ሲጠይቀው ውሻውም “አህያው ልብ የለውም፡፡ ልብማ ቢኖረው ኖሮ እያናፋ አንተን ባልጠራህ ነበር፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
በዚህ ጊዜ ውሻው ጅቡ ሊገድለው እንደፈለገ ስለገባው መሮጥ ጀመረ፡፡ ጅቡም ውሻውን እያሳደደው ሲከተለው ውሻው አንድ እሾሃማ አጥር አጠገብ ሲደርስ እሾሁን ጠምዞ ወደ አጥሩ ውስጥ ገባ፡፡ ሰውነቱ በሙሉ ወደ አጥሩ ውስጥ ሲገባ ጅራቱ ብቻ ውጪ ስለቀረ ጅቡ ለቀም አድርጎ ቆረጠው፡፡ እሾሃማው አጥር የውሻው ጌታ ግቢ ነበር፡፡ ጅቡም በኩራት “ብታመልጠኝም ጅራትህን ቆርጨዋለሁ፡፡” አለው፡፡ ውሻው ግን በጅቡ ስቆበት “ጌታዬ የሚተኛው በቁርበት ላይ በመሆኑ እኔም አጠገቡ ነው የምተኛውና እኛ ውሾች እንደተለመደው በጅራታችን አመድ ስለምናቦን እኔም ጌታዬ ላይ አመድ እንዳላቦንበት ሰሞኑን ጅራቴን ልቆርጥ አቅጄ ስለነበረ ብዙም የጀግንነት ስሜት አይሰማህ፡፡ እኔም ልቆርጠው ነበርና፡፡” አለው ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|