የአህያዋ ጆሮ
በዛርኬ ጎይቴ የተተረከ
በአንድ ወቅት ከከብቶች ጋር የምትኖር አህያ ነበረች፡፡ ከከብቶቹም ጋር ትበላና ትተኛ ስለነበረ ቀንዶቻቸውን ስታይ ትቀናባቸው ጀመር፡፡
“ቀንዶች ቢኖሩኝ ጅቦችን እከላከልባቸው ነበር፡፡” ብላም አሰበች፡፡ “እናም ወደ ገጠር ወይም ወደ ሌሎች መንደሮች ሄጄ ቀንዶች የማገኝበትን መንገድ መፈለግ አለብኝ፡፡” ብላ በማሰብ ረጅም ጉዞ ላይ እንዳለች ጀርባው ላይ ትልቅ ሸክም ተሸክሞ ይጓዝ የነበረ ነጋዴ አገኘች፡፡
ነጋዴውም “አሃ! አምላክ በጣም ስላሰበልኝ ይህንን ከባድ ሸክም ሊያቀልልኝ ይህችን አህያ ላከልኝ፡፡” ብሎ በማሰብ ሸክሙን አህያዋ ላይ ጫነው፡፡ ሸክሙም ለአህያዋ ከባድ ቢሆንም አብረው ብዙ መንገድ ከተጓዙ በኋላ አህያዋ ማረፍ ስለፈለገች ቀስ ብላ መራመድ ጀመረች፡፡ በዚህ ጊዜ ሰውየው በያዘው ዱላ ደጋግሞ ይመታት ጀመር፡፡ ሸክሙ አሁንም እንደከበዳት ነበርና በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስላልቻለች በመጨረሻ በጉልበቷ ተንበርክካ አልሄደም አለች፡፡ ነጋዴው ቢደበድባትም ተነስታ መራመድ አልቻለችም፡፡ በዚህ ጊዜ ነጋዴው አንደኛውን ጆሮዋን ቆረጠው፡፡ አሁንም በጣም ስለደከማት መንቀሳቀስ አቃታት፡፡
ከዚያም ነጋዴው ሸክሙን አውርዶላት አህያዋን እዚያው የተኛችበት ትቷት መንገዱን ቀጠለ፡፡ አህያዋም ሸክሙ ከወረደላት በኋላ ወደቀድሞው ቦታዋ ወደከብቶቹ ተመልሳ ስትሄድ የምትፈልገውን ቀንድ ለምን እንዳላገኘች ጠየቋት፡፡
“አይይ! እናንተ ቀንድ ስለማግኘቴ ነው የምታወሩት? እንኳን ቀንድ ላገኝ የነበረኝንም ጆሮ አጥቼ መጣሁ፡፡ ዋጋዬንም አግኝቻለሁ፡፡” አለቻቸው፡፡
ከዚያን እለት በኋላ አጉል ምኞት ያላቸው ሰዎች “ቦታችሁን እወቁ፡፡ ካለበለዚያ ቀንድ እፈልግ ብላ ጆሮዋን እንዳጣችው አህያ እንዳትሆኑ፡፡” እየተባባሉ ይመከሩ ጀመር፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|