ድቡና ሴትየዋ
በአብዲሳ ላቤ የተተረከ
በአንድ ወቅት ድቦችና ሰዎች ጓደኞች ስለነበሩ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ታዲያ አንዲት ሴት ርቧት ነበርና ገንፎ አዘጋጅታ እቤቷ ውስጥ አስቀምጣ ውሃ ለማምጣት ወደ ወንዝ ስትወርድ መንገዷ ላይ አንድ ድብ ታገኛለች፡፡ ድቡንም “በጣም ርቦኛል፡፡ ሆኖም ያዘጋጀሁት ገንፎ ለእኔ ብቻ የሚበቃና ትንሽ ስለሆነ እባክህ ቤት ስትደርስ ከላዩ ላይ እንዳትጎርስ፡፡ ሁሉንም እፈልገዋለሁና እንዳትነካብኝ እማፀንሃለሁ፡፡” አለችው፡፡
በዚህ ዓይነት ለምናው ወደ ወንዙ መንገዷን ቀጠለች፡፡ ድቡ ግን ቤት እንደደረሰ ሁሉንም ገንፎ በልቶ ሴትየዋ ወደቤት ስትመለስ የመጨረሻዋን ጉርሻ ሲጎርስ ደረሰች፡፡
“ገንፎዬን እየበላህ ነው ማለት ነው?” ብላ በንዴት ስትጠይቀው
“አዎ፣ እኔም ርቦኝ ነበር፡፡” አላት፡፡ በዚህ ጊዜ በዱላ አናቱ ላይ በጣም መታችው፡፡ ድቡም ደንግጦ ሲሸሽ አንድ አህያ ከዛፍ ጋር የታሰረበት ገመድ ስለጠለፈው ገመዱ ተበጠሰ፡፡ አህያውም ገመዱ ሲበጠስ ደንግጦ ሲሸሽ ከንቦች ቀፎ ጋር ስለተጋጨ ንቦቹ በሙሉ ከቀፎው ወጥተው በመብረር ዶሮውን ሲነድፉት ዶሮው ክንፎቹን ሲያራግብ ከአገረ ገዢው ደጃፍ ተሰጥቶ የነበረው እህል ተበትኖ መሬቱን ሞላው፡፡
የአገረ ገዢው ሚስት በሁኔታው በጣም ተናደደች፡፡ ውሻው ይጮህ ስለነበረ ምን እንደሆነ ለማየት ስትወጣ የሆነውን ሁሉ ተመለክታ በጣም ስለተናደደች ዶሮውን “እንዲደርቅልኝ ብዬ ያሰጣሁትን እህል ለምንደነው የበታተንከው?” ብላ ጠየቀችው፡፡
ዶሮውም “ጥፋቱ የእኔ አይደለም፡፡ ንቦቹ መጥተው ሲነድፉኝ በህመምና በድንጋጤ ክንፎቼን ሳራግፍ ነው፡፡ የእኔ ጥፋት አይደለም፡፡” አለ፡፡
ከዚያም ሚስትየው ንቦቹን ስትጠይቃቸው እነርሱም “የእኛ ጥፋት አይደለም፡፡ አህያው መጥቶ ቀፎአችንን ሲረግጠው ማሩ በሙሉ ስለተበተነ ዶሮውን ነደፍነው፡፡ ስለዚህ የአህያው ጥፋት ነው፡፡” አሉ፡፡
አህያውንም ስትጠይቀው እርሱም “እኔ አይደለሁም፤ ድቡ ሊበላኝ ሲያሳድደኝ በድንጋጤ ስሮጥ ነው፡፡ የእኔ ጥፋት አይደለም፡፡” አለ፡፡
ምክንያቱ የሴትየዋ ቤት መሆኑ ስለተደረሰበት አገረ ገዢው ከዚያን ጊዜ በኋላ ሴትየዋና ድቡ እንዲለያዩ፣ አብረው እንዳይኖሩና ጓደኛ መሆን እንደማይችሉ ፈረደ፡፡
ከዚያ እለት ጀምሮ ድቡ ብቻውን ጫካ ውስጥ መኖር ጀመረ፡፡ ሰዎችንም በያዛቸው ጊዜ ይበላቸው ጀመር፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|